1ሰንበላጥ የከተማዋን ቅጥር እንደገና እየሰራን መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ እኛ ኢየሩሳሌምን እንደ ገና መገንባታችን በውስጡ እንደ እሳት አቃጠለው፣ እናም በጣም ተቆጥቶ በአይሁዶች ላይ በጥላቻ ተሞልቶ ተናገረ፡፡
2ከሰማርያ በመጡት አማካሪዎቹና የጦር አለቆቹ ፊት እንዲህ አለ፣ “እነዚህ አይሁዶች ራሳቸውን ችለው መቆም አይችሉም፣ ምን እያደረጉ ያሉ መስሏቸዋል? ከተማዋን እንደገና ገንብተው ራሳቸው ሊኖሩባት ነውን? ቤተ መቅደሱን እንደገና ገንብተው ካህናቱ ለያህዌ የሚያቀርቡትን መስዋእት ሁሉ ሊያቀርቡ ነውን? በአንዲት ቀን እንዲህ ያለውን ታላቅ ሥራ ይጨርሳሉን? እነዚህን የተቃጠሉና ከጥቅም ውጭ የሆኑ ድንጋዮች ቅጥሩን እንደገና ለመገንባት ሊጠቀሙበትና ለከተማዋ ዳግም ሕይወት ሊሰጧት ይችላሉን?
3ጦቢያ ከሰንበላጥ አጠገብ ቆሞ ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፣ “ያ እነርሱ የሚገነቡት ቅጥር እጅግ ደካማ ነው፤ ትንሽ ቀበሮዎች ቢወጡበት እንኳን ይፈርሳል፤ የእነርሱ የድንጋይ ቅጥር ቀበሮ ቢወጣበት ይፈርሳል!”
4ከዚያ እኔ እንዲህ ስል ጸለይኩ፣ “አምላካችን ሆይ፣ ስማን፣ እነርሱ እየቀለዱብን ነው! የስድባቸውን ቃል ወደ ራሳቸው እንዲመለስ አድርግ! ጠላቶቻቸው እንዲመጡባቸውና እንዲይዟቸው ወደ ባዕድ ምድርም እንዲያሳድዷቸው አድርግ!
5እነርሱ በደለኞች ናቸው፡፡ በደላቸውን ከእነርሱ አታርቅ በፊትህ ለሰሩት ኃጢአት ዋጋ ይክፈሉ፡፡ በስድቦቻቸው፣ ቅጥሩን መልሰው የሚገነቡትን በጣም አስቆጥተዋል!”
6ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን፣ ሰራተኞቹ ከጠቅላላው በከተማይቱ ዙሪያ ከሚገኘው የቅጥሩ ከፍታ ግማሽ ያህሉን ሰሩ፡፡ ይህን ማከናወን የቻሉት ሊሰሩ የሚችሉትን በሙሉ ልባቸው ለመስራት ስለፈለጉ ነበር፡፡
7ነገር ግን ሰንበላጥ፣ ጦብያ፣ ዐረቦች፣ አሞናዊያን፣ እና አሽዶዳዊያን የቅጥሩ ስራ መሰራቱ እንደ ቀጠለና የፈረሰውን ቅጥር እየጠገንን መሆኑን ሲሰሙ በጣም ተቆጡ፡፡
8እነርሱም መጥተው የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለመውጋት እና በከተማይቱ ውስጥ ሀብት ለመፍጠር በአንድነት ዕቅድ አወጡ፡፡
9እኛ ግን ቅጥሩን መልሰን በመገንባታችን እጅግ በተቆጡት በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ወደ አምላካችን ጸለይን፣ ደግሞም ከተማዋን ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ዘንድ ወንዶችን በቅጥሮቹ ዙሪያ አቆምን፡፡
10ከዚያ የይሁዳ ሰዎች እንዲህ ማለት ጀመሩ፣ “ቅጥሩን የሚሰሩት ወንዶች መላ አቅማቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡ ልናነሳው የሚገባ እጅግ ብዙ ፍርስራሽ አለ፤ እኛ ይህን ስራ መጨረስ አልቻልንም ስራው እጅግ በዝቶብናል፡፡
11ከዚህም ባሻገር፣ ጠላቶቻችን እንዲህ እያሉ ነው! ‘አይሁዶች እኛን ከማየታቸው አስቀድሞ፣ በእነርሱ ላይ እንውጣባቸውና እንግደላቸው፣ የቅጥሩን ስራቸውንም እናስቁማቸው!”
12በጠላቶች አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ብዙ ጊዜ ወደ እኛ እየመጡ ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ሊፈጽሙ የሚያስቡትን ክፉ እቅድ ይነግሩን ነበር፡፡
13ስለዚህ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ቅጥሩን እንዲጠብቁ ሰዎችን አቆምኩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቅጥሩን በቀላሉ መሻገር በሚቻልባቸው በቅጥሩ ዝቅተኛ ስፍራዎች እንዲቆሙ ተደረገ፡፡ እነርሱም ሰይፎቻቸውን ጦሮቻቸውን፣ እና ደጋኖቻቸውንና ቀስቶቻቸውን ይዘው ይጠብቁ ነበር፡፡
14ከዚያ እያንዳንዳቸውን ከተመለከትኩ በኋላ፣ መሪዎችንና ሌሎች ሹማምንቶችን እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎችን ሰብስቤ እንዲህ አልኳቸው፣ “ጠላቶቻችንን አትፍሯቸው! እግዚአብሔር ታላቅና በክብር የተሞላ እንደሆነ አስቡ! እናም ቤተሰባችሁን፣ ወንድና ሴቶች ልጆቻችሁን፣ ሚስቶቻችሁን እና ቤቶቻችሁን ለመጠበቅ ተዋጉ!”
15ጠላቶቻችን፣ ዕቅዶቻቸውን እንደሰማን አወቁ፣ እግዚአብሔርም ስራችንን ለማስቆም ያወጡትን ዕቅድ ከንቱ አደረገባቸው፡፡ ስለዚህ እኛ ሁላችንም ወደ ፊት እንሰራበት ወደነበረው ወደዚያው ስፍራ ቅጥሩን ለመገንባት ተመለስን፡፡
16ነገር ግን ከዚያ በኋላ፣ በዚያ ከነበሩት ወንዶች ግማሾቹ ብቻ የቅጥሩን ሥራ ይሰሩ ነበር፡፡ ሌሎቹ ጦሮቻቸውን፣ ጋሻዎቻቸውን፣ ደጋኖቻቸውንና ቀስቶቻቸውን ይዘውና የጦር ልብሶቻቸውን ለብሰው ይጠብቁ ነበር፡፡ መሪዎቹ የይሁዳን ሕዝብ ይጠብቁ ነበር፡፡
17መሪዎች ቅጥሩን የሚሰሩትንና የጉልበት ሥራ የሚሰሩትን ይጠብቁ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአንድ እጁ ቅጥሩን ሲገነባ በሌላው እጁ መሳሪያ ይይዛል፡፡
18ቅጥሩን የሚገነባ ሁሉ በወገቡ ሰይፍ ይታጠቃል፡፡ ጠላቶቻችን ቢመጡ መለከት የሚነፋው ሰው ከእኔ አጠገብ ይሆናል፡፡
19ከዚያ ለባለስልጣናቱ፣ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች፣ እና ለሌሎች ሰዎች እንዲህ አልኳቸው፣ “ይህ ሥራ ታላቅ ነው፣ እኛ በቅጥሩ ዙሪያ የምንገኝ አንዳችን ከሌላችን ተራርቀን እንገኛለን፡፡
20የመለከት ድምጽ ስትሰሙ፣ መለከቱ በሚነፋበት ስፍራ ተሰብስቡ፡፡ አምላካችን ለእኛ ይዋጋልናል!”
21ስለዚህም ስራችንን መስራት ቀጠልን፡፡ ከህዝቡ እኩሌታው ቀኑን ሙሉ ጦሩን ይዞ፣ ጠዋት ጸሀይ ስትወጣ አንስቶ ምሽት ከዋክብት እስኪታዩ ድረስ ጥበቃ ያደርጋል፡፡
22በዚያን ጊዜ፣ እኔ ለህዝቡ፣ “ለእያንዳንዱ ሰራተኛ እና ለረዳቱ በምሽት ኢየሩሳሌም ውስጥ እንዲቆዩ ይነገራቸው፡፡ ያንን በማድረግ፣ በምሽት እኛን መጠበቅና በቀን ቅጥሩን መገንባት ይችላሉ” በማለት እናገራሁ፡፡
23በእነዚያ ጊዜያት፣ ልብሴን አላወልቅም፣ የጦር መሳሪያዬንም ሁልጊዜ እይዛለሁ፡፡ ወንድሞቼ፣ አገልጋዮቼ እና እኔን የሚከተሉ ወንዶች እና ዘብ ሆነው የሚያገለግሉ ሁሉ ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ ሁላችንም ውሃ ለመጠጣት ስንሄድ እንኳን የጦር መሳሪያዎችንን እንደያዝን ነበር፡፡