መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ነህምያ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በንጉስ አርጤክስ፣ አገዛዝ ሃያኛ ዓመት፣ ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር፣ በክብረ በዓሉ ለንጉሱ ወይን ጠጅ የሚቀርብበት ሰዓት ነበር፡፡ ወይን ወስጄ ለንጉሱ አቀረብኩ፡፡ ከዚያ አስቀድሞ በንጉሱ ፊት እንዲህ አዝኜ ቀርቤ አላውቅም ነበር፡፡
2በዚያን ቀን ግን፣ ንጉሱ እኔን ተመልክቶ እንዲህ አለኝ፣ “ለምን እንዲህ እጅግ አዘንህ? የታመምክ አትመስልም፡፡ ምናልባት መንፈስህ ታውኮ ይሆንን?” እኔም በጣም ፈርቼ ነበር፡፡
3እንዲህ ስል መለስኩ፣ “ንጉስ ሆይ፣ ለዘለዓለም ንገስ! ያዘንኩት ያለ ምክንያት አይደለም፣ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፍርስራሽ ሆናለች፣ በከተማዋ ዙሪያ ያሉ በሮቿ በሙሉ ተቃጥለው አመድ ሆነዋል፡፡”
4ንጉሱ እንዲህ ሲል መለሰልኝ፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እናም ለእርሱ መልስ ከመስጠቴ አስቀድሞ፣ በሰማይ ወዳለው አምላክ ጸለይኩ፡፡
5ከዚያ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጠሁ፣ “ታደርገው ዘንድ ፈቃድህ ከሆነ፣ እኔም አንተን ደስ አሰኝቼ ከሆነ፣ አባቶቼ የተቀበሩባትን ከተማ ኢየሩሳሌምን መልሼ እንድገነባ ወደዚያ እንድሄድ ፈቀድልኝ፡፡”
6ንጉሱ (ንገስቲቱ አጠገቡ ተቀምጣ ሳለ) እንደህ ሲል ጠየቀኝ፣ “እንድትሄድ ብፈቅድልህ፣ ለስንት ጊዜ በዚያ ትቆያለህ? ደግሞስ መቼ ትመለሳለህ?” እርሱም፣ ወደዚያ የምሄድበትንና ተመልሼ የምመጣበትን ቀን እንዳሳወቅሁት፣ ወዲያውኑ እንድሄድ ፈቃድ ሰጠኝ፡፡
7ደግሞም ለንጉሱ እንዲህ አልኩት፣ “ለአንተ ለሰጠሁት ታማኝ አገልግሎቴ እንደ ሽልማት አድርገህ፣ ከአፍራጦስ ወንዝ ባሻገር ለሚያስተዳድሩ ገዥዎች ደብዳቤ ስጠኝ፡፡ ወደ ይሁዳ ስገባና ስወጣ በግዛቶቻቸው በደህንነት መጓዝ እችል ዘንድ እንዲፈቅዱልኝ እባክህን ትዕዛዝ ስጣቸው፡፡
8እንዲሁም፣ እባክህን ደኖችህን ለሚያስተዳድረው ለአሳፍ ደብዳቤ ፃፍልኝ፣ ደግሞም በቤተ መቅደሱ አጠገብ የሚገኘውን ግንብ በሮች አምዶቹን ለማበጀት፣ የከተማዋን ቅሮች ለመጠገን፣ እና የምኖርበትን ቤት እንዲሰጠኝ ፃፍለት፡፡” እግዚአብሔር ለዚህ ስራ የሚያስፈልገኝን እንዳገኝ እየረዳኝ ስለነበር፣ ንጉሱ እንዲያደርግ የጠየቅኩትን አደረገልኝ ፡፡
9ወደ ይሁዳ ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ ንጉሱ፣ እኔን እንዲያጅቡኝና እንዲጠብቁኝ አንዳንድ ፈረሰኛ የጦር መኮንኖችንና ወታደሮችን ላከ ፡፡ ገዥዎቹ ወደሚያስተዳድሩት ግዛት ስንደርስ፣ ከንጉሱ ዘንድ የተላከውን ደብዳቤ ሰጠኋቸው፡፡
10ነገር ግን ሁለቱ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሖሮናዊው ሰንበላጥና አሞራዊው አገልጋይ ጦቢያ፣ እኔ መድረሴን ሲሰሙ የእስራኤልን ህዝብ የሚረዳ በመምጣቱ በጣም ተቆጡ፡፡
11ስለዚህም እኔ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቼ በዚያ ለሶስት ቀናት ቆየሁ፡፡
12በምሽት ከከተማ ወጣሁ፣ ከእኔ ጋርም ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ እኛ የነበረን እኔ የተቀመጥኩበት አንድ እንስሳ ብቻ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ እግዚአብሔር በልቤ ስላስቀመጠው ነገር ለማንም ሰው ምንም አልተናገርኩም፡፡
13በሸለቆው መግቢያ አለፍኩና ከከተማው ቅጥር ውጭ ሄድኩ፡፡ ከዚያ በከተማዋ ዙሪያ ተዟዙሬ የቀበሮዎች ጉድጓድ በሚባለው ጉድጓድ በኩል አለፍኩ፡፡ ከዚያ ወደ ፋንድያ መድፊያ በር አለፍኩ፡፡ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የሚገኙ ቅጥሮችን ሁሉ ዞሬ ተመለከትኩ፣ እናም ሁሉም በሮች ተሰባብረው ቅጥሮቹ ክፍት መሆናቸውን አየሁ፣ ደግሞም በቅጥሩ ዙሪያ የነበሩ የእንጨት በሮች ሁሉ አመድ እስኪሆኑ ተቃጥለው ነበር፡፡
14ከዚያ ወደ ፏፏቴ በር እና የንጉስ ገንዳ ወደሚባለው ገንዳ ሄድኩ፣ ነገር ግን የተቀመጥኩበት አህያ በጠባቡ መተላለፊያ ማለፍ አልቻለችም፡፡
15ስለዚህ ወደ ኋላ ዞሬ ወደ በቄድሮን ሸለቆ አጠገብ እያለፍኩ ወደ ኋላ ከመመለሴና ወደ ሸለቆው በር ወደ ከተማዋ ከመግባቴ አስቀድሞ በዚያ የነበሩ ቅጥሮችን ተመለከትኩ፡፡
16የከተማዋ ባለስልጣናት እኔ ወዴት እንደሄድኩ ወይም ምን እንዳደረግኩ አላወቁም ነበር፡፡ ለአይሁድ መሪዎች ወይም ለባለስልጣናቱ ወይም ለካህናቱ ወይም በእድሳቱ ስራ ለሚሳተፉ ለማናቸው ሌሎች ሰዎች ስለዚህ ምንም ነገር አልተናገርኩም፡፡
17እንዲህ አልኩ፣ “በከተማችን ላይ የደረሰውን መጥፎ ነገሮች ሁሉ ሁላችሁም በሚገባ ታውቃላችሁ፡፡ ከተማዋ ፍርስራሽ ሆናለች፣ ሌላው ቀርቶ በሮቿ ተቃጥለው ወድቀዋል፡፡ ኑ፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ለመገንባት ስራውን እንጀምር፡፡ እኛ ያንን ብናደርግ፣ ከዚህ በኋላ በከተማችን አናፍርም፡፡”
18ከዚያ ከንጉሱ ጋር በተነጋገርኩ ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት በመልካምነቱ እንዲረዳንና ንጉሱ ምን እንዳለኝ ነገርኳቸው፡፡ እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፣ “ተነስተን የእድሳቱን ስራ እንጀምር!” ስለዚህም ይህን መልካም ሥራ ለመስራት ተነሱ፡፡
19ነገር ግን ሰንበላጥ፣ አሞናዊው አገልጋይ ጦቢያ፣ እና አረባዊው ጌሻም፣ እኛ ለመስራት ያቀድነውን ሰሙ፡፡ በእኛ ላይ ቀለዱ አፌዙብንም፡፤ እንዲህም አሉ፣ “ይህ እናንተ የምትሰሩት ስራ ምንድን ነው? በንጉሱ ላይ እያመጻችሁ ነውን?”
20እኔ ግን እንዲህ አልኳቸው፣ “በሰማይ ያለው አምላክ ስኬት ይሰጠናል፡፡ እናንተ ግን በዚህ ከተማ ላይ መብት የላችሁም፣ ተሳትፎ የላችም፣ በዚህ ላይ ህጋዊ መብት የላችሁም፣ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ምንም ታሪካዊ መታሰቢያ የላችሁም፡፡”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።