1ኢየሱስም እውነት እላችኋለሁ፣ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶቹ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል መምጣቷን ሳያዩ የማይሞቱ አሉ አላቸው፡፡
2ከስድስት ቀን በኋላም ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ለብቻቸው ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ላይ አመጣቸው፡፡
3በፊታቸውም ተለወጠባቸው፤ ልብሱም አጣቢ በምድር ላይ ሊያነጻው እስከማይችል ድረስ ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ፡፡
4ሙሴና ኤልያስ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስ ጋርም ይነጋገሩ ነበር፡፡
5ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ረቡኒ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶችን እንሥራ አለው፡፡
6እጅግ ፈርተው ስለነበረ የሚመልሰውን አያውቅም ነበር፡፡
7ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ፡፡
8ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ከእነርሱ ጋር ሌላ ማንንም አላዩም፡፡
9ከተራራው ሲወርዱ ሳሉም ይህንን ያዩትን ነገር ሁሉ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሳ ድረስ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፡፡
10እነርሱም ቃሉን ይዘው ከሙታን መነሳት ማለት ምን ማለት ነው ተባባሉ፡፡
11እነርሱም ጸሐፍት አስቀድሞ ኤልያስ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድነው ብለው ጠየቁት፡፡
12ኢየሱስም ኤልያስማ በርግጥ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፡፡ ስለ ሰው ልጅ ብዙ መከራ እንዲቀበልና እንዲጣል የተጻፈው ታዲያ እንዴት ይሆናል?
13እኔ ግን እላችኋለሁ! ኤልያስ መጥቷል፤ ስለ እርሱም አንደተጻፈው የወደዱትን አደረጉበት፡፡
14ወደ ደቀመዛሙርቱ በመጡ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው ጸሓፍትም ሲጠይቋቸው ተመለከቱ፡፡
15ወዲያው ሕዝቡ ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ እጅግ ተገርመው ወደ እርሱ በመሮጥ ሰላምታ ሰጡት፡፡
16እርሱም ስለምንድነው የምትጠይቋቸው? ብሎ ጠየቃቸው፡፡
17ከሕዝቡም መሐል አንዱ መምህር ሆይ! ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወዳንተ አመጣሁት፡፡
18በሚወስደው ቦታ ሁሉ ይጥለውና አረፋ ያስደፍቀዋል፣ ጥርሱን ያንቀጫቅጭና ያደርቀዋል፡፡ እንዲያወጡት ደቀመዛሙርትህን ጠየቅኳቸው፣ እነርሱም አልቻሉም፡፡
19ኢየሱስም መልሶ እናንተ የማታምኑ ትውልዶች እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሳችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው፡፡
20ወደ እርሱም አመጡለት፤ ባየውም ጊዜ ወዲያው መንፈሱ በምድር ላይ በኃይል ጥሎ እያንፈራገጠ አረፋ አስደፈቀው፡፡
21ኢየሱስም የልጁን አባት ይህ ከያዘው ምን ያህል ጊዜ ሆነው? ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም ከሕጻንነቱ ጀምሮ ነው፡፡
22ብዙ ጊዜ ሊያጠፋው በውሃና በእሳት ላይ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ እዘንልንና እርዳን አለው፡፡
23ኢየሱስም የሚቻልህ ከሆነ አልክን ለሚያምን ሁሉም ነገር ይቻላል አለው፡፡
24ወዲያው የልጁ አባት ጮኸና አምናለሁ፣ እንዳምንም እርዳኝ አለው፡፡
25ኢየሱስ ሕዝቡ እየሮጠ ሲመጣ ተመልክቶ እርኩሱን መንፈስ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ ከእርሱ እንድትወጣ ተመልሰህም እንዳትገባበት አዝሃለሁ ብሎ ገሰጸው፡፡
26መንፈሱም ካንፈራገጠው በኋላ ጮኾ ወጣ፡፡ ብዙዎች ሞተ እስኪሉ ድረስም እንደ ሞተ ሰው ሆነ፡፡
27ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሳው፤ እርሱም ተነሣ፡፡
28ወደ ቤት በገቡ ጊዜም ደቀመዛሙርቱ እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድነው? ብለው ለብቻው ጠየቁት፡፡
29ኢየሱስም እንዲህ ዓይነቱ ወገን በጸሎት ካልሆነ በስተቀር አይወጣም አላቸው፡፡
30ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ በዚያ መሆኑን ማንም እንዲያውቅ አይፈልግም ነበር፡፡
31ደቀመዛሙርቱንም እንዲህ ሲል አስተማራቸው፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ታልፎ ይሰጣል፣ ይገድሉታልም፣ ከተገደለ ከሶስት ቀን በኋላም ይነሣል አላቸው፡፡
32ነገር ግን የተናገራቸውን አላስተዋሉም፤ እንዳይጠይቁትም ፈርተው ነበር፡፡
33ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ በቤት ሳሉም መንገድ ላይ ስለምን ጉዳይ ነበር የምትነጋገሩት ብሎ ደቀመዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡
34ከእነርሱ ማን ይበልጥ እንደሆነ ተከራክረው ነበርና ዝም አሉ፡፡
35ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠራቸው፣ እንዲህም አላቸው፣ ከእናንተ የመጀመሪያ ሊሆን የሚወድ የሁሉ መጨረሻና አገልጋይ ይሁን፤
36ትንሽ ልጅ በመካከላቸው አቁሞና አቅፎት እንዲህ አላቸው፤
37ማንም እንደዚህ ካሉት ታናናሽ ልጆች አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔንም የሚቀበል የሚቀበለው የላከኝን ነው እንጂ እኔን አይደለም፡፡
38ዮሐንስም መምህር ሆይ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያስወጣ አየነው፤ ስለማይከተለንም ከለከልነው አለው፡፡
39ኢየሱስ ግን በስሜ ተአምራትን አድርጎ ፈጥኖ በእኔ ላይ ክፉ ሊናገር የሚችል የለምና አትከልክሉት፤
40የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው አለው፡፡
41እውነት እላችኋለሁ የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ብርጭቆ ውሃ እንድትጠጡ የሚሰጣችሁ ዋጋውን አያጣም፡፡
42በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከእምነቱ የሚያስት ሰው ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታሥሮ በጥልቅ ባህር ላይ ቢጣል ይሻለው ነበር፡፡
43እጅህ ለመሰናከልህ ምክንያት የምትሆን ከሆነ ቆርጠህ ጣላት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት ወደ ሲዖል ከምትሔድ አካልህ ጎሎ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና፡፡
45እግርህ ለመሰናከልህ ምክንያት የሚሆን ከሆነ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ሲዖል ወደ እሳቱ ከምትጣል አንድ እግር ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል፡፡
47ዐይንህ ለመሰናከልህ ምክንያት የምትሆን ከሆነ አውጥተህ ጣላት፤
48ሁለት ዐይን ኖሮህ ትሉ ወደማይሞትበት፣ እሳቱ ወደማይጠፋበት ከምትገባ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፡፡
49እያንዳንዱ ሰው በእሳት ይቀመማል፡፡
50ጨው መልካም ነው፤ የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ግን ምን ታደርጉታላችሁ? በእያንዳንዳችሁ ሕይወት የጨውነት ጣዕም ይኑርባችሁ! እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ፡፡