1ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሓፍት በአንድ ላይ ተሰብስበው ወደ ኢየሱስ መጡ፡፡
2ከደቀመዛሙርቱ አንዳንዶቹ በረከሰ እጅ ማለትም ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፡፡
3(ፈሪሳውያንና ሁሉም አይሁድ የአባቶችን ወግ ስለሚጠብቁ እጆቻቸውን ካልታጠቡ በቀር አይበሉም ነበር)
4ከገበያ ስፍራ ሲመጡ እጃቸውን ካልታጠቡ በቀር አይበሉም ነበር ፤እንዲሁም ዋንጫዎችን፣ ማሰሮዎችንና የናስ እቃዎችን ማጠብን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ወጎችን ይጠብቁ ነበር፡፡
5ፈሪሳውያንና ጸሓፍት "ደቀመዛሙርትህ በአባቶች ወግ መሰረት የማይጓዙት፣ ነገር ግን ባልታጠበ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?" ብለው ጠየቁት ፡፡
6እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡፡ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች በተናገረው ትንቢት፣ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ብቻ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
7ሰው ሠራሽ ሥርዐት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል˝ ተብሎ የተጻፈው ትክክል ነው፡፡
8እናንተ የእግዚአብሔርን ሕግ ትታችሁ የሰዎችን ወግ ታጠብቃላችሁ፡፡
9እንዲህም አላቸው፡፡ ወጋችሁን ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ትሽራላችሁ፡፡
10ሙሴ፣ «አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ሞትን ይሙት» ብሏልና፡፡
11እናንተ ግን አንድ ሰው እናቱን ወይም አባቱን፣ «ከእኔ ልታገኙ የሚገባችሁን እርዳታ ቁርባን አድርጌዋለሁ፤ ማለትም ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ» ቢላቸው፣
12ከዚህ በኋላ ለአባቱና ለእናቱ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም፡፡ ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፡፡
13ይህን የመሳሰሉ ብዙ ነገሮችንም ታደርጋላችሁ፡፡
14ደግሞም ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፣ ሁላችሁም ስሙኝ ፤ አስተውሉም፡፡
15ከውጭ ወደ ውስጡ ገብቶ ሰውን የሚያረክስ ምንም ነገር የለም፡፡
16ነገር ግን ከውስጡ የሚወጡ ነገሮች እነርሱ ሰውን ያረክሱታል፡፡
17ከሕዝቡ ተለይቶ ወደ ቤት እንደ ገባም ደቀመዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት፡፡
18እርሱም፣ «እናንተም አልተረዳችሁምን? ከውጭ ወደ ውስጡ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው ምንም ነገር እንደሌለ አታስተውሉምን?» አላቸው፡፡
19ምክንያቱም ፣ወደ ውስጡ (ዐፉ) የሚገባው ነገር ወደ ሆዱ እንጂ ወደ ልቡ የሚገባ ስላልሆነ ከሰውነቱ የሚወጣ አይደለምን? ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ተናገረ፡፡
2020እንዲህም አለ፤ ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፡፡
21ከውስጥ ከሰው ልብ ክፉ ሐሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣
22ምንዝር፣ ስግብግብነት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትእቢት፣ ስንፍና ይወጣሉ፡፡
23እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ ይወጣሉ፡ ሰውንም ያረክሱታል፡፡
24ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና አካባቢ ሄደ፡፡ ያለበትን ማንም እንዳያውቅም ወደ አንድ ቤት ገባ ፤ሆኖም ሊደበቅ አልቻለም፡፡
25ወዲያውኑም ስለ እርሱ የሰማችና ትንሽ ልጅዋ በእርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ወደ እርሱ መጥታ በእግሩ ሥር ተደፋች፡፡
26ሴቲቱ ዝርያዋ ከሲሮፊኒቃዊት ወገን የሆነ ግሪካዊት ነበረች፡፡ እርስዋም ኢየሱስ በልጅዋ ውስጥ ያለውን ጋኔን እንዲያወጣላት ለመነቸው፡፡
27እርሱም «በመጀመሪያ ልጆች ይጥገቡ፤ የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መስጠት ተገቢ አይደለምና» አላት፡፡
28እርስዋ ግን «አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከገበታ ሥር የሚወዳድቀውን የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ፡፡» ብላ መለሰችለት፡፡
29ኢየሱስም ፣ እንዲህ በማለትሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል አላት፡፡
30ወደ ቤትዋም ሄደች፤ልጅዋም አጋንንቱ ለቅቋት ዐልጋው ላይ ተኝታ አገኘቻት፡፡
31ደግሞም ከጢሮስ አካባቢ ተነሥቶ በሲዶና በኩል አድርጎ በዐሥሩ ከተሞች ዐልፎ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ፡፡
32እጁን እንዲጭንበትና እንዲፈውሰው አንድ መስማት የተሳነውና ኮልታፋ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡
33እርሱም ከሕዝቡ ለይቶ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወሰደው፤ጣቶቹን በጆሮዎቹ ውስጥ አስገብቶ እንትፍ አለበት፤ምላሱንም ነካው፡፡
34ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ተመለከተና በረጅሙ ተንፍሶ «ኤፍታህ» አለው፡፡ ይህም ተከፈት ማለት ነው፡፡
35ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ የታሰረውም ምላሱ ተፈታ፡፡ ጥርት አድርጎም ተናገረ፡፡
36ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም አጥብቆ ባዘዛቸው መጠን አብልጠው አሰራጩት ፡፡
37እነርሱም ከልክ በላይ ተደንቀው ፣ ሁሉንም ነገር ደኅና አድርጓል፤እርሱ መስማት የተሣነው እንዲሰማ ኮልታፋውም እንኳ እንዲናገር ያደርጋል አሉ፡፡