መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ማርቆስ 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ወዲያውኑም በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሓፍት፣ ከሸንጎም አባሎችም ሁሉ ጋር ተማከሩ፤ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።
2ጲላጦስም፣አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ሲመልስ አንተ እንዳልከው ነኝ አለው።
3የካህናት አለቆችም ብዙ ክስ አቀረቡበት።
4ጲላጦስም ስንት ክስ እንዳቀረቡብህ ተመልከት! ምንም አትመልስምን? ብሎ እንደገና ጠየቀው።
5ኢየሱስ ግን ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም መልስ አልሰጠም።
6በየበዓሉ ሕዝቡ ጲላጦስ እንዲፈታላቸው የጠየቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።
7በዚያም ኹከት ቀስቅሰው ግድያ ከፈጸሙ ሰዎች ጋር የታሰረ አንድ በርባን የሚባል ሰው ነበር።
8ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን እንዲያደርግላቸው ጠየቁት።
9ጲላጦስም "የአይሁድን ንጉሥ" እንድፈታላችሁ ትፈልጋላቸሁን? አላቸው።
10እንዲህ ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው።
11የካህናት አለቆች ግን በእርሱ ፈንታ በርባን እንዲፈታላቸው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሕዝቡን ቀሰቀሱ።
12ጲላጦስም መልሶ ታዲያ በዚህ የአይሁድ ንጉሥ ብላችሁ በምትጠሩት ሰው ላይ ምን ላድርግበት? አላቸው።
13እነርሱም "ስቀለው!" እያሉ እንደገና ጮኹ።
14ጲላጦስም "ለምን? ምን በደል ፈጽሟል?" አላቸው። እነርሱም "ስቀለው!" እያሉ አብዝተው ጮኹ።
15ጲላጦስም ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ኢየሱስን ግን አስገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።
16ወታደሮቹም ኢየሱስን ፕራይቶሪዮን ወደሚባለው ግቢ ወሰዱት፤ወታደሮቹንም ሁሉ ጠሩ፤
17ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም በራሱ ላይ ደፉበት፡፡
18"የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!" እያሉ ሰላምታ ይሰጡት ነበር።
19በመቃ ዐናቱን እየመቱ፤ ምራቃቸውን ተፉበት፤ በፊቱም ተንበርክከው ሰገዱለት።
20አላግጠውበትም ሐምራዊውን ልብስ አወለቁበት፤ የራሱንም ልብስ አልብሰው፤ሊሰቅሉ ወሰዱት።
21በመንገድ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ሲመጣ አግኝተው፤ የኢየሱስን መስቀል ተሸክሞ ከእነርሱ ጋር እንዲሄድ አስገደዱት።
22ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ጎልጎታ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ወሰዱት፤ ትርጉሙም፡- "የራስ ቅል ስፍራ" ማለት ነው።
23ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣውም።
24ከዚያም ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉ።
25ከጧቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን ሰቀሉት፡፡
26"የአይሁድ ንጉሥ" የሚል የክስ ጽሑፍ በመስቀሉ ዐናት ተጽፎ ነበር።
27ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ፣አንዱንም በግራው ሰቀሉ።
28መጽሓፍ "ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤" የሚለው ቃል ተፈጸመ።
29በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ በማለት ይሰድቡት ነበር፣ "አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ ሆይ!
30እስቲ አሁን ራስህን አድን፤ከመስቀልም ውረድ!"
31እንደዚሁም የካህናት አለቆች ከጸሓፍት ጋር ሆነው እርስበርሳቸው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ "ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ማዳን ግን አይችልም" አሉ፡፡
32"አይተን እንድናምንበት መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ" ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም ይሰድቡት ነበር።
33ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።
34ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፣ "ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማሰበቅታኒ፤" ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ትርጓሜውም "አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?" ማለት ነው።
35በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው "እነሆ! ኤልያስን ይጣራል፤" አሉ።
36ከእነርሱም አንዱ ሮጠና ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ፤ "ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ" አለ።እንዲጠጣውም በመቃ ላይ አድርጎ ለኢየሱስ ሰጠው፡፡
37ከዚያም ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም ሰጠ።
38የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ።
39በመስቀሉ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ የመቶ አለቃ ኢየሱስ እንዴት መንፈሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ፣ "ይህ ሰው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤" አለ።
40በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ሴቶችም በዚያ ነበሩ። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ሰሎሜም ነበሩ።
41እነርሱ ኢየሱስ በገሊላ በነበረበት ጊዜ ይከተሉትና ያገለግሉት ነበር። እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶችም ነበሩ።
42መሽቶ ስለ ነበርና የሰንበት ዋዜማና ለሰንበት የመዘጋጃ ጊዜ ስለ ነበር፡፡
43የተከበረ የሸንጎ አባል የነበረ ዮሴፍ የሚባል የአርማትያስ ሰው መጣ። እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚጠባበቅ ሰው ነበር። በድፍረትም ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን አስከሬን እንዲሰጠው ለመነው።
44ጲላጦስም "እንዴት እንዲህ በቶሎ ሞተ?" ብሎ ተደነቀ። የመቶ አለቃውንም ጠርቶ፣ "ከሞተ ቈይቶአልን?" ሲል ጠየቀው።
45የኢየሱስን መሞት ከመቶ አለቃው ከሰማ በኋላ አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት።
46ዮሴፍም የከፈን ልብስ ገዛ፤ የኢየሱስን አስከሬን ከመስቀል አውርዶ ገነዘው፤ ከዐለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ አስቀመጠው። ትልቅ ድንጋይም አንከባሎ የመቃብሩን መግቢያ ዘጋ።
47መግደላዊት ማርያምና የዮሳ እናት ማርያምምሰ ኢየሱስን የት እንዳኖሩት አዩ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።