መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ማርቆስ 16

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሰንበት ካለፈ በኋላም መጥተው ይቀቡት ዘንድ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሽቶ ገዙ፡፡
2ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ጎህ በቀደደ ጊዜ ወደ መቃብሩ መጡ፡፡
3እርስ በርሳቸውም ድንጋዩን ከመቃብሩ መግቢያ ማን ያንከባልልናል ይባባሉ ነበር፡፡
4አሻግረው ሲመለከቱም ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና ተንከባሎ አዩት፡፡
5ወደ መቃብሩም ገብተው የሚያንጸባርቅ ነጭ ልብስ የለበሰ አንድ ወጣት በስተቀኝ ተቀምጦ አዩና ተገረሙ፡፡
6እርሱም አትገረሙ፣ የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፡፡ ያኖሩበትን ቦታ ተመልከቱ፤ እርሱ በዚህ የለም፣ ተነሥቷል፡፡
7ነገር ግን ሂዱ፣ ለጴጥሮስና ለደቀመዛሙርቱም እንደነገራችሁ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፣ በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሯቸው አላቸው፡፡
8እነርሱም መገረምና ፍርሃት ወድቆባቸው ነበርና ከዚያ ወጥተው ከመቃብሩ ሸሹ፡፡ ፈርተውም ነበርና ለማንም አንዳች አልተናገሩም፡፡
9ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን በማለዳ በተነሳ ጊዜ ሰባት አጋንንት አውጥቶላት ለነበረችው ለመግደላዊት ማርያም አስቀድሞ ታያት፡፡
10እርሷም ከኢየሱስ ጋር የነበሩት እያዘኑና እያለቀሱ ሳሉ ሄዳ ነገረቻቸው፡፡
11እነርሱም ሕያው እንደሆነና ለእርሷም እንደታያት በሰሙ ጊዜ አላመኑም፡፡
12ከእነዚህ ነገሮች በኋላም ከእነርሱ ሁለቱ ወደ ገጠር በመሄድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ በሌላ ሰው መልክ ተገለጠላቸው፡፡
13እነርሱም ሄደው ለተቀሩት ነገሯቸው፤ እነርሱንም አላመኗቸውም፡፡
14ከዚያም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ለራሳቸው ኢየሱስ ተገለጠላቸውና ስለ ልባቸው ጥንካሬና ከትንሳኤው በኋላ ያዩትን ስላላመኗቸው ወቀሳቸው፡፡
15እንዲህም አላቸው፣ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፣ ወንጌልንም ለፍጥረት በሙሉ ስበኩ አላቸው፡፡
16ያመነና የተጠመቀም ይድናል፣ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡
17ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፣ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፣
18እባቦችን ይይዛሉ፣ የሚገድል ነገር እንኳን ቢጠጡ አይጎዳቸውም፣ እጆቻቸውን በህሙማን ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይፈወሳሉ፡፡
19ጌታ ኢየሱስ ይህንን ካላቸው በኋላ ወደ ሰማይ ወጥቶም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡
20እነርሱም ወጥተው በየቦታው ሰበኩ፡፡ ጌታም ቃሉን ተከትለው በሚመጡ ምልክቶች እያጸና ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፡፡ አሜን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።