1ኢየሱስ ከቤተመቅደስ ሲወጣ ሳለ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ መምህር ሆይ፤ እንዴት ያሉ ድንጋዮችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎቹ እንደሆኑ ተመልከት! አለው፡፡
2እርሱም እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ እንደዚህ አይቀርም አለው፡፡
3ኢየሱስ በደብረዘይት ተራራ ላይ በቤተመቅደሱ ትይዩ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ
4ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚፈጸሙበት ምልክቱስ ምንድነው? ብለው ለብቻው ጠየቁት፤
5ኢየሱስም ማንም እንዳያስታችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ አላቸው፡፡
6ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ! እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡
7ጦርነትንና የጦርነትን ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትታወኩ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡
8ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የምድር መንቀጥቀጥ፣ ረሃብም ይሆናል፡፡ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡
9እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ወደ ሸንጎዎቻቸው ያቀርቧችኋል፣ በምኩራቦች ውስጥ ትደበደባላችሁ፡፡ ለእነርሱ ምስክር እንዲሆን በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ፡፡
10አስቀድሞ ወንጌል ለሕዝቦች ሁሉ ይሰበካል፡፡
11ወደ ፍርድ በሚያቀርቧችሁና አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ አስቀድማችሁ ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ ነገር ግን በዚያች ሰዓት የምትናገሩት ይሰጣችኋልና፤ የሚናገረውም መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም፡፡
12ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ አባትም ልጁን፤ ልጆችም ወላጆቻቸውን በመቃወም ተነስተው ይገድሏቸዋል፡፡
13ስለስሜም በሰዎች ሁሉ ትጠላላችሁ፡፡ ነገር ግን እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል፡፡
14የጥፋትን እርኩሰት በማይገባው ቦታ ቆሙ ስታዩት (አንባቢው ያስተውል) በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤
15በቤቱ ጣሪያ ላይ ያለም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይውረድ፣ ወደ ቤትም አይግባ፤
16በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመልከት፡፡
17ነገር ግን በእነዚያ ወራት ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!
18በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡
19እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያልሆነ ወደፊትም የማይሆን ታላቅ መከራ በእነዚያ ቀናት ይሆናልና፡፡
20ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥር ኖሮ ሥጋን የለበሰ ሁሉ አይድንም ነበር፡፡ ነገር ግን ስለመረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ቀኖቹን አሳጠረ፡፡
21አንድ ሰው እነሆ ክርስቶስ በዚህ ነው ወይም እነሆ በዚያ ነው ቢላችሁ አትመኑት፡፡
22ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነብያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸው የተመረጡትን ለማሳት ድንቆችንና ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡
23ነገር ግን አስተውሉ፤ እነሆ አስቀድሜ ሁሉንም ነገር ነግሬአችኋለሁ፡፡
24ከመከራው በኋላ በእነዚያ ቀናት ፀሐይ ትጨልማለች፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣
25ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ በሰማያት ውስጥ ያሉ ኃይላትም ይናወጣሉ፡፡
26እነርሱም የሰው ልጅ በደመና ውስጥ በታላቅ ኃይልና ክብር ሲመጣ ያዩታል፡፡
27ከምድር ጫፍ እስከ ጫፍ ለእርሱ የተመረጡትን ከአራቱም ነፋሳት በአንድ ላይ እንዲሰበስቡለት መላዕክትን ይልካቸዋል፡፡
28ምሳሌውን ከበለስ ዛፍ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለሰልስ፣ ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ መቃረቡን ታውቃላችሁ፡፡
29እናንተም ደግሞ እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ በምታዩበት ጊዜ የሰው ልጅ በበር ላይ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡
30እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፡፡
31ሰማይና ምድር ያልፋል፣ ቃሌ ግን አያልፍም፡፡
32ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት በስተቀር የሰማይ መላዕክትም ቢሆኑ፣ ልጅም ቢሆን ማንም አያውቅም፡፡
33ጊዜው መቼ እንደሆነ አታውቁምና አስተውሉ፣ ንቁና ጸልዩ፡፡
34ነገሩ ለአገልጋዮቹ ሥልጣን፣ ለእያንዳንዳቸውም የሥራ ድርሻ በመስጠት ዘበኛውም ደግሞ እንዲጠብቅ አዝዞት ቤቱን ትቶ ወደ ሩቅ ሀገር የሚሔድን ሰው ይመስላል፡፡
3535የቤቱ ጌታ በምሽት፣ ወይም በእኩለ ሌሊት፣ ወይም ዶሮ ሲጮህ፣ ወይም ጠዋት ላይ ምን ጊዜ እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ!
36በድንገት ሲመጣ እንቅልፍ ላይ ሆናችሁ እንዳያገኛችሁ፡፡
37ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፣ንቁ!