መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ማርቆስ 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስም በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፡፡ አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤በዙሪያው ዐጥር ሠራ፤ለወይን መጭመቂያ የሚሆን ጕድጓድ ቈፈረ፤ማማም ሠራ፡፡ ለገበሬዎችም አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ፡፡
2በወቅቱ የወይኑን ፍሬ እንዲቀበል አንድ አገልጋይ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፡፡
3እነርሱም አገልጋዩን ያዙት፤ ደብድበውም ባዶ እጁን ሰደዱት፡፡
4በድጋሚም ሌላ አገልጋይ ላከ፤እነርሱም ፈነከቱት፤ አሳፈሩትም፡፡
5ሌላም አገልጋይ ወደ እነርሱ ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፡፡ ብዙዎች ሌሎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ ሌሎቹንም ገደሉ፡፡
6የወይኑ ተክል ባለቤት አንድ ተወዳጅ ልጅ ነበረው፤ልጄን ያከብሩታል በማለት በመጨረሻ እርሱን ላከው፡፡
7ገበሬዎቹ ግን እርስበርሳቸው እንዲህ አሉ፡፡ ይህ ወራሹ ነው ኑ እንግደለው ሀብቱ ሁሉ የእኛ ይሆናል ተባባሉ፡፡
8ልጁንም ያዙት፤ ገደሉት፤ከወይኑ ቦታ ውጭም ጣሉት፡፡
9የወይኑ ተክል ባለቤት በዚህ ጊዜ ምን ያደርጋል? ይመጣና ገበሬዎቹን ያጠፋቸዋል፤የወይን ቦታውንም ለሌሎች ይሰጣቸዋል፡፡
10ይህን የመጽሓፍ ቃል አላነበባችሁምን? እነሆ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማእዘን ድንጋይ ሆነ፤
11ይህ ከጌታ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፡፡
12ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ እንደ ሆነ ስለ ተገነዘቡ እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ፤ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ፤ትተውት ሄዱ፡፡
13እነርሱም በንግግር እንዲያጠምዱት አንዳንድ ፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎችን ላኩ፡፡
14ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ አሉት፤መምህር ሆይ፣ አንተ እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንም በይሉኝታ እንደማታደርግ፣ለሰው ፊትም እንደማታዳላ ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፡፡ ለቄሳር ግብር መክፈል ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም?
15እንክፈል ወይስ አንክፈል? አሉት፡፡ ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አላቸው፡፡ እንዳየው አንደ ዲናር አምጡልኝ አላቸው፡፡
16እነርሱም አመጡለት፡፡ ኢየሱስም ይህ ምስል ቅርጹም የማን ነው? አላቸው፡፡ እነርሱም የቄሳር ነው አሉት፡፡
17ኢየሱስም እንግዲህ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ አላቸው፡፡ እጅግም ተገረሙበት፡
18ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ብለው ጠየቁት፡፡
19መምህር ሆይ፣ ሙሴ፣ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሚስቱን ትቶ ቢሞት፣ ወንድሙ እርስዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካለት ብሎ ጽፎልናል፡፡
20ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ሚስት አገባ፤ ዘር ሳይተካም ሞተ፡፡
21ሁለተኛውም አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካለት ሞተ፡፡ ሦስተኛውም እንዲሁ፡፡
22ሰባቱም ለወንድማቸው ዘር አልተኩም፡፡ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱም ደግሞ ሞተች፡፡
23ታዲያ ይህች ሴት በትንሣኤ የየትኛው ሚስት ትሆናለች? አሉት፡፡ ሰባቱም አግብተዋት ነበርና፡፡
24ኢየሱስም የምትስቱት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ አይደለምን?
25በትንሳኤ ጊዜ ሰዎች አያገቡም፤ አይጋቡም፤ ነገር ግን በሰማይ እንደ መላእክት ይሆናሉ እንጂ፡፡
26ነገር ግን ሙታን እንደሚነሡ በሚነድደው ቁጥቋጦ ውስጥ እኔ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያእቆብ አምላክ ነኝ ሲል እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን አላነበባችሁምን? እጅግ ትስታላችሁ፡፡
27እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፡፡
28ከጸሓፍት አንዱ መጣና በአንድነት ሆነው ሲጠይቁት እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንደ መላሰላቸው አይቶ፣ ከሕግ ፊተኛው የትኛው ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው፡፡
29ኢየሱስም ፊተኛው፣ እስራኤል ሆይ ስማ! አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤
30አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ፣በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹምም ኀይልህ ውደድ የምትለዋ ናት፡፡
31ሁለተኛዋም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትለዋ ናት፡፡ ከእነዚህ የሚበልጥ ምንም ሌላ ትእዛዝ የለም አለው፡፡
32ሰውዬውም መምህር ሆይ፣በእውነት መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ ነው፤ከእርሱም በቀር ሌላ የለም፤ እርሱን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ማስተዋል፣
33በፍጹም ኀይል መውደድና ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ሁሉንም ዓይነት መስዋእትና የሚቃጠል መሥዋእት ከማቅረብ ይበልጣል አለ፡፡
34ኢየሱስም ሰውዬው በማስተዋል እንደ መለሰለት ባየ ጊዜ አንተ ከእግዚአብሔር መንግስት የራቅህ አይደለህም አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ማንም ሰው ምንም ጥያቄ ሊጠይቀው አልደፈረም፡፡
35ኢየሱስም መለሰላቸው፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያስተምር፣ ጸሓፍት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው የሚሉት እንዴት ነው? አለ፡፡
36ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው፡፡
37ዳዊት ራሱ ጌታዬ ብሎ ይጠራዋል፤ ታዲያ እንዴት ልጁ ይሆናል? ሕዝቡም በደስታ ይሰማው ነበር፡፡
38ኢየሱስም እንዲህ አለ፡፡ ከጸሓፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ልብስ ለብሰው መሄድን ይወድዳሉ፤ እነርሱ በገበያ ቦታ ሰላምታን፣
39በምኩራብም የክብር ወንበር፣ በግብዣም የክብር ቦታ ላይ መቀመጥ ይወድዳሉ፡፡
40ለይምሰል ጸሎት በማስረዘም የመበለቶችን ቤት ይበዘብዛሉ፡፡ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ፡፡
41ኢየሱስም በመባ መቀበያው ፊት ለፊት ተቀመጠ፡፡ ብዙ ሰዎች በመባ መቀበያው ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ ተመለከተ፡፡ ብዙ ሃብታሞች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፡፡
42ከዚያም አንዲት ድኻ መበለት መጥታ ሁለት ናስ ጨመረች፤ይህም የብር ሩብ ነው፡፡
43እርሱም ደቀመዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ይህች መበለት በመባ መቀበያው ውስጥ ገንዘባቸውን ከጨመሩት ሁሉ አብልጣ ሰጠች፡፡
44እነርሱ ከትርፋቸው ሰጥተዋልና፡፡ እርስዋ ግን ከጉድለቷ ሰጠች፤ ያላትን ሁሉ ሰጠች፤ ኑሮዋን እንኳ ሳይቀር ሁሉንም ሰጠች፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።