1ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ላካቸው፡፡
2እንዲህም አላቸው፣ ፊት ለፊታችን ወዳለው መንደር ሂዱ፤ወዲያው እንደ ገባችሁም ማንም ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ ውርንጫ መንገድ ዳር ታስሮ ታገኛላችሁ፡፡ ፍቱትና አምጡልኝ፤
3ማንም ለምን ይህን ታደርጋላችሁ ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፤ እርሱም ይለቅቀዋል አላቸው፡፡
4እነርሱም ሄዱ፤ አንድ ውርንጫ ከቤት ውጭ በመንገድ ዳር ታስሮ አገኙ፤ ፈቱትም፡፡
5በአካባቢው ከቆሙት አንዳንዶቹ ሰዎች ለምን ፈታችሁት? አሏቸው፡፡
6እነርሱም ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ነገሯቸው፤ ለቀቋቸውም፡፡
7ደቀመዛሙርቱም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም አለበሱት፤ ኢየሱስም ተቀመጠበት፡፡
8ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን ፣ሌሎችም ከየቦታው ቅርንጫፎችን ቆርጠው በሚሄድበት መንገድ ላይ አነጠፉ፡፡
9ከፊት የቀደሙት ከኋላውም የተከተሉት ሆሳእና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤
10የሚመጣው የአባታችን የንጉሥ ዳዊት መንግስት የተባረከ ነው፤ ሆሳእና በአርያም እያሉ ጮኹ፡፡
11ኢየሩሳሌም እንደ ደረሰ ወደ ቤተመቅደስ ገባ፡፡ በአካባቢው ያለውን ሁሉ ተመለከተ፤መሽቶም ነበርና ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ሄደ፡፡
12በማግስቱም ከቢታንያ እንደ ወጡ ተራበ፤
13አንዲት ቅጠሏ ያቆጠቆጠ በለስ ከርቀት አየ፡፡ ምናልባት አንዳች አገኝባት ይሆናል በማለት ወደ እርሷ መጣ፡፡ ሲደርስ ግን በለስ የሚያፈራበት ጊዜ ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም፡፡
14ስለዚህም ማንም ሰው ለዘላለም ምንም ፍሬ አያግኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ ደቀመዛሙርቱም ሰሙት፡፡
15ወደ ኢየሩሳሌምም እንደ መጡ ወደ ቤተመቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን አባረረ፤የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛ የርግብ ሻጮችንም መቀመጫቸውን ገለበጠባቸው፡፡
16ማንም ሰው በቤተ መቅደስ ውስጥ ዕቃ ይዞ እንዳይመላለስ ከለከለ፡፡
17አስተማራቸውም፤ ቤቴ የአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው፡፡
18ሊቀ ካህናቱና ጸሓፍትም፣ይህን ሲናገር ሲሰሙ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ተደንቀው ስለ ተከተሉት ፈርተው ነበርና እንዴት እንደሚገድሉት ማሰብ ጀመሩ፡፡
19ኢየሱስም በየምሽቱ ከከተማ ይወጣ ነበር፡፡
20በማለዳ ሲያልፉም በለሲቱ ከሥሯ ደርቃ አገኟት፡፡
21ጴጥሮስም አስታውሶ መምህር ሆይ! እነሆ፤የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው፡፡
22ኢየሱስም እንዲህ አለው፡፡ በእግዚአብሔር እመን፤
23እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም በልቡ ሳይጠራጠር ይህን ተራራ ከዚህ ተነቅለህ ወደ ባሕር ውስጥ ተወርወር ቢልና የተናገረው እንደሚፈጸም በልቡ ቢያምን ይሆንለታል፡፡
24ስለዚህ እላችኋለሁ፤የጸለያችሁትንና የለመናችሁትን ነገር ሁሉ እንደምትቀበሉ ብታምኑ ይሆንላችሁማል፡፡
25ለጸሎት ስትቆሙ፣ በማንም ላይ ቅርታ ቢኖራችሁ፣ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ ይቅር በሉ፡፡
26እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ የቅር አይላችሁም፡፡
27በድጋሚም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ኢየሱስ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባም ሊቀ ካህናት፣ጸሓፍትና ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣
28እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይም እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? አሉት፡፡
29ኢየሱስም አንድ ጥያቄ ጠይቃችኋለሁ እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ አላቸው፡፡
30መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነው? ወይስ ከሰው? አላቸው ፡፡
31እነርሱም እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ ከሰማይ ነው ብንል ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤
32ነገር ግን ከሰው ነው ብንል ደግሞ ሰዉ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ ነው ብሎ አምኖበታል ብለው ሕዝቡን ፈሩ፡፡
33ለኢየሱስም አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ ኢየሱስም እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው፡፡