1እንግዲህ ያህዌ የሚናገረውን አድምጡ፤ «ተነሡ፤ ያላችሁንም ቅርታ በተራሮች ፊት አቅርቡ ኮረብቶችም የምትሉትን ይስሙ፡፡
2እናንተ ተራሮች እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁ የምድር መሠረቶች ያህዌ የሚያቀርበውን ክስ አድምጡ፤ እርሱ ከእስራኤል ጋር ይፋረዳል፡፡»
3«ሕዝቤ ሆይ፣ ምን አደረግሁህ? ያታከትሁህስ በምንድነው? እስቲ መስክርብኝ!
4እኔ ከግብፅ ምድር አወጣሁህ ከባርነት ቤትም ታደግሁህ፡፡ ሙሴን፣ አሮንንና ማርያምን ወደ አንተ ላክሁ፡፡
5ሕዝቤ ሆይ፣ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያቀደብህን የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትን፣ ከሺጡም ተነሥተህ ወደ ጌልጌላ ስትሄድ፣ እኔ፣ ያህዌ ያደረግሁትን የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ አስታወስ፡፡
6ለልዑል አምላክ ለመስገድ በምመጣበት ጊዜ፣ ለያህዌ ምን ይዤ ልምጣ? የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆኑ የአንድ ዓመት ጥጃ ይዤ ልምጣን?
7በሺህ የሚቆጠሩ ዐውራ በጐችን ወይስ የአሥር ሺህ ወንዞች የሚያህል ዘይት ባቀርብለት ያህዌ ይደሰት ይሆን? ስለ መተላለፌ የበኩር ልጄን፣ ስለ ኃጢአቴስ የአካሌን ፍሬ ልስጥን?
8ሰው ሆይ፣ መልካሙን፣ ያህዌ ከአንተ የሚፈልገውን ነግሮሃል ፍትሕ አድርግ፤ ደግነትን ውደድ፤ ከአምላክህ ጋር በትሕትና ተመላለስ፡፡
9የያህዌ ድምፅ ከተማዋን ይጣራል አሁን እንኳ ጥበብ ስምህን ትገነዘባለች በትሩን አስታውስ፤ በቦታው ያደረገው ማን እንደ ሆነ አስታውስ፡፡
10ክፉው ቤት ውስጥ በግፍ የተገኘ ሀብት አስጸያፊ የሆነ ሐሰተኛ መስፈሪያ አለ፡፡
11ዐባይ ሚዛን የሚጠቀመውን ሰው፣ ሐሰተኛ መመዘኛ በከረጢት የቋጠረውን ሰው ንጹሕ ላድርገውን?
12ባለ ጠጐች በግፍ ተሞልተዋል በዚያ የሚኖሩ ሐሰት ተናግረዋል ምላሳቸው አታላይ ናት፡፡
13ስለዚህ በጽኑ ቁስል መታሁህ ከኃጢአትህ የተነሣም አፈረስሁህ፡፡
14ትበላለህ ግን አትጠግብም ሁሌም ባዶነት ውስጥህ ይኖራል፡፡ ታከማቻለህ ግን አይጠራቀምልህም ያጠራቀምኸውን ለሰይፍ እዳርጋለሁ፡፡
15ትዘራለህ ግን አታጭድም የወይራ ፍሬ ትጨምቃለህ፤ ግን ዘይት አትቀባም፤ ወይን ትጨምቃህ ግን ጠጅ አትጠጣም፡፡
16የዖምሪን ሥርዐት የአክዓብን ቤት ተግባርም አጥብቀህ ይዘሃል በምክራቸው መሠረት ኖረሃል፡፡ ስለዚህ አንተንና ከተማህን ለውድመት ሕዝብህንም ለመዘባበቻ አሳልፌ እሰጣለሁ በሕዝቤ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ ትሸከማለህ፡፡