1ለእኔ ወዮልኝ! የመከር ጊዜ ፍሬ ተሰብስቦ የወይኑም ቃርሚያ ካበቃ በኃላ እርሻ ውስጥ እንደ ቀረው ፍሬ ሆኛለሁ ከዚያ የሚበላ ወይን ፍሬ አይገኝም የምጓጓለትና ቶሎ ቀድሞ የሚደርሰው በለስ አይኖርም፡፡
2ከምድሩ ታማኝ ሰዎች ጠፍተዋል በሰው ልጆች መካከልም ቅን ሰው የለም፡፡ ሁሉም ደም ለማፍሰስ ያደባል እያንዳንዱም የገዛ ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል፡፡
3እጆቻቸው ሌሎችን ለመጉዳት ሠልጠነዋል፤ ገዦቻቸው ገንዘብ ይፈልጋሉ ፈራጁ ጉቦ ይጠብቃል፤ ኃይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ፡፡
4ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜኬላ እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኩርንችት ነው፡፡ ነቢያቶቻችሁ አስቀድመው የተናገሩለት ቀን እናንተ የምትቀጡበት ቀን ነው፡፡ የሚሸበሩበት ቀን ደርሶአል፡፡
5ጐረቤትህን አትመን፣ ወዳጅህም ላይ አትተማመን፡፡ በዕቅፍህ ከምትተኛዋ እንኳ ለምትናገረው ተጠንቀቅ፡፡
6ወንድ ልጅ አባቱን ያዋርዳል ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ ምራት በአማቷ ላይ ትነሣለች፡፡ የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰቦቹ ይሆናሉ፡፡
7እኔ ግን ያህዌን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የመድኃኒቴን አምላክ እጠብቃለሁ አምላኬም ይሰማኛል፡፡
8ጠላቴ፣ ሆይ ብወድቅ እንኳ በእኔ ደስ አይበልሽ፤ ከወደቅሁበት እነሣለሁ በጨለማ ብቀመጥ እንኳ ያህዌ ብርሃን ይሆንልኛል፡፡
9ያህዌን ስለ በደልሁ እርሱ እስኪፈርድልኝ ድረስ ቁጣውን እታገሣለሁ፡፡ እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል በጽድቁ ሲያድነኝም አያለሁ
10ጠላቴም ታያለች፣ «አምላክህ ያህዌ የታል?» ያለች ጠላቴ ታፍራለች፡፡ እኔም የጠላቴን ውድቀት አያለሁ፤ መንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ ትረገጣለች፡፡
11ቅጥሮቻችሁን የምትሠሩበት ቀን ይመጣል በዚያን ቀን ድንበራችሁ ይሰፋል!
12በዚያ ቀን ሕዝባችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል፤ ከአሦርና ከግብፅ ከተሞች ከግብፅ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ከባሕር እስከ ባህር፣ ከተራራ እስከ ተራራ ድረስ ሕዝባችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል፡፡
13ከሚኖሩበት ሰዎች ክፋት የተነሣ ምድሪቱ ወና ትሆናለች፡፡
14በለመለመ መስክ መካከል ብቻቸውን ዱር ውስጥ ያሉትን የርስትህ መንጋ የሆኑት ሕዝብህን በበትርህ ጠብቅ፡፡ እንደ ቀድሞው ዘመን በባሰንና በገለዓድ አሰማራቸው፡፡
15ከግብፅ እንደ ወጣችሁበት ዘመን ድንቆችን አሳያቸዋለሁ፡፡
16ኃይል ያላቸው ቢሆኑም አሕዛብ ይህን አይተው ያፍራሉ፤ እጃቸውን አፋቸው ላይ ያደርጋሉ ጆሮዋቸውም ይደነቁራል፡፡
17እንደ እባብ፣ ምድር ላይ እንደሚርመሰመሱም ፍጥረቶች ትቢያ ይልሳሉ፡፡ እየተንቀጠቀጡ ከዋሻዎቻቸው ይወጣሉ አምላካችን ያህዌ ሆይ በፍርሃት ወደ አንተ ይመጣሉ ከአንተ የተነሣ ይሸበራሉ፡፡
18ኃጢአትን ይቅር የሚል የርስቱንም ትሩፍ መተላለፍ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? የኪዳን ታማኝነትህን ለእኛ ማሳየት ደስ ስለሚልህ አንተ ለዘላለም አትቆጣም፡፡
19እንደ ገና ትራራልናለህ፤ ርኩሰታችንን በእግሮችህ ትረግጣለህ፡፡ ኃጢአታችንን ሁሉ ወደ ባሕሩ ጥልቅ ትጥላለህ፡፡
20በቀድሞ ዘመን ለአባቶቻችን በመሐላ እንደ ገባኸው ቃል ለያዕቆብ ታማኝነትን፣ ለአብርሃምም የኪዳን ታማኝነትን ትሰጣለህ፡፡