1ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤ «እናንተ የያዕቆብ መሪዎች የእስራኤልም ቤት ገዦች አድምጡ፤ ፍትሕን ማወቅ ይገባችሁ አልነበረምን?
2እናንተ ግን መልካሙን ጠላችሁ ክፉን ወደዳችሁ ቆዳቸውን ገፈፋችሁ ሥጋቸውን ከአጥንታቸው ጋጣችሁ የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ ቆዳቸውን ገፈፋችሁ ዐጥንቶቻቸውን ሰባበራችሁ፤ በመጥበሻ እንደሚጠበስ በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቆራረጣችኃቸው፡፡
3እናንተ መሪዎች ወደ ያህዌ ትጮኻላችሁ እርሱ ግን አይሰማችሁም፡፡ ከክፉ ሥራችሁ የተነሣ በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእናንተ ይሰውራል፡፡
4ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት ያህዌ እንዲህ ይላል፤
5«ጥቅም የሚያገኙበት ሲሆን፣ «ብልጽግና ይሆናል» ይላሉ፤ ጥቅም በማያገኙበት ጊዜ ግን፣ ‹ጦርነት ይመጣባችኃል› እያሉ በማወጅ ሕዝቡን ያስታሉ፡፡
6ስለዚህ ራእይ የማታዩበት ሌሊት ይሆንባችኃል ሌሊት ስለሚሆንባችሁ ንግርት አታደርጉም፡፡ በነቢያት ላይ ፀሐይ ትጠልቅባቸዋለች ቀኑ እነርሱ ላይ ይጨልማል፡፡
7ባለ ራእዮች ያፍራሉ ንግርተኞችም ይዋረዳሉ ከእኔ ዘንድ መልስ የለምና ሁሉም ፊታቸውን ይሸፍናሉ፡፡
8እኔ ግን፣ ለያዕቆብ በደሉን ለእስራኤል ኃጢአቱን እንድናገር በያህዌ መንፈስ ኃይል ተሞልቻለሁ ፍትሕና ብርታትንም ተሞልቻለሁ፡፡
9እናንት የያዕቆብ ቤት መሪዎች ፍትሕ የምትጠሉ፣ ቀና የሆነውን የምታጣምሙ የእስራኤል ቤት ገዦች ይህን ስሙ፡፡
10ጽዮንን ደም በማፍሰስ ኢየሩሳሌምን በርኩሰት የምትገነቡ ስሙ
11መሪዎቻችሁ በጉቦ ይፈርዳሉ ካህናቶቻችሁ በዋጋ ያስተምራሉ ነቢያቶቻችሁ በገንዘብ ንግርት ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ በያህዌ በመተማመን፣ «ያህዌ ከእኛ ጋር ስለሆነ ክፉ ነገር አይደርስብንም» ይላሉ፡፡
12ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች የቤተ መቅደሱ ኮረብታ ጥቅጥቅ ያለ ደን ይሆናል፡፡