1ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ባሕሩንም አቋርጦ ወደ ገዛ ከተማው መጣ።
2እነሆ፣ በምንጣፍ የተኛ አንድ ሽባ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት ሽባውን፣ “አንተ ልጅ፣ አይዞህ፤ ኅጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው፡፡
3አንዳንድ ጸሐፍት ግን እርስ በርሳቸው፣ "ይህ ሰው እኮ እየተሳደበ ነው" ተባባሉ ።
4ኢየሱስም ዐሳባቸውን ዐውቆ፣ “ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?”
5ለመሆኑ የሚቀለው፣'ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል' ነው፣ ወይስ 'ተነሣና ሂድ ማለት ነው?'
6ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ዕወቁ" አለ፡፡ ሽባውንም፣ "ተነሣና፣ምንጣፍህን ይዘህ ወደ ቤት ሂድ" አለው፡፡
7ከዚያም ሰውየው ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ።
8ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተገርመው፣ ለሰው እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
9ኢየሱስም ከዚያ አለፍ እንዳለ፣ ማቴዎስ የሚባለውን ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያ ቦታ ላይ ተቀምጦ አየውና "ተከተለኝ" አለው።እርሱም ተነሥቶ ተከተለው፡፡
10ኢየሱስም በቤቱ ውስጥ ለመመገብ በተቀመጠ ጊዜ፣ ቀረጥ የሚሰበስቡ ብዙ ሰዎችና ኃጢአተኞች መጥተው፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርት ጋር አብረው ተመገቡ።
11ፈሪሳውያንም ይህን ሲያዩ፣ደቀ መዛሙርቱን "ለምንድን ነው መምህራችሁ፣ ከግብር ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው?" አሏቸው፡፡
12ኢየሱስም ይህንን ሲሰማ ፣"ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፡፡
13'ሂዱና' ምሕረት እንጂ መሥዋዕትን አልፈልግም' የሚለውን ተማሩ፣ እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኅጥአንን ወደ ንስሓ ለመጥራት" ነው አለ።
14ከዚያም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጥተው፣" እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ እንጾማለን ፣የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?" አሉት።
15ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፣ “ሰርገኞች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሆኖም ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፣በእነዚያ ቀናት ይጾማሉ።
16ማንም ሰው በአሮጌ ልብስ ላይ ዐዲስ ቊራጭ ጨርቅ አይለጥፍም፤ ምክንያቱም አሮጌውን ልብስ ይቦጭቀዋል፣ ልብሱም የባሰ ይጐዳል።
17ሰዎች ዐዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ አያስቀምጡም፤ እንደዚያ ካደረጉ አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁ ይፈሳል፣ አቁማዳውም ይቀደዳል። ይልቁንም ዐዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ውስጥ ያስቀምጡታል፣ ሁለቱም ይጠበቃሉ፡፡"
18ኢየሱስ ይህን እየተናገራቸው እያለ፣ አንድ ሹም እየሰገደ ወደ እርሱ መጣ። “ልጄ አሁን ገና ሞተች፣ ነገር ግን ና ና እጅህን ጫንባት በሕይወትም ትኖራለች አለው”።
19ኢየሱስም ተነሥቶ ተከትሎት ሄደ፤ ደቀ ዛሙርቱም ደግሞ አብረውት ሄዱ።
20አንዲት ለዐሥራ ሁለት ዓመት ከባድ የደም መፍሰስ የነበረባት ሴት፣ ከኢየሱስ ኋላ መጥታ የልብሱን ጠርዝ ነካች፤
21"የልብሱን ጫፍ ብቻ ብነካ ደኅና እሆናለሁ" ብላ ነበርና።
22ኢየሱስም ዞር ብሎ አያትና፣ “ልጄ ሆይ፣ አይዞሽ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ደኅና ሆነች።
23ኢየሱስም ወደ ሹሙ ቤት በገባ ጊዜ፣ዋሽንት የሚነፉትንና የሚንጫጩትን አይቶ፣
24"ወደዚያ ዞር በሉ፣ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም"አላቸው። እነርሱ ግን በማፌዝ ሳቁበት።
25ሕዝቡን ወደ ውጭ ባስወጡ ጊዜ፥ ኢየሱስ ወደ ክፍሉ ገብቶ እጅዋን ያዘ፤ልጅቱም ተነሣች።
26ወሬውም በዚያ አካባቢ ሁሉ ተዳረሰ።
27ኢየሱስም በዚያ ሲያልፍ፣ ሁለት ዐይነ ስውሮች ተከተሉት፣ ያለ ማቋረጥም፣ "የዳዊት ልጅ ማረን!" እያሉ ይጮኹ ነበር።
28ኢየሱስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ፣ ዐይነ ስውሮቹ ወደ እርሱ መጡ። ኢየሱስም፣ "ይህን ለማድረግ እንደምችል ታምናላችሁ?" አላቸው። እነርሱም "አዎን፣ ጌታ ሆይ" አሉት፡፡
29ከዚያም ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን ዳስሶ፣ "እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ" አላቸው።
30ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ። ከዚያም ኢየሱስ፣"ይህንን ማንም እንዳያውቅ" ብሎ በጥብቅ አዘዛቸው።
31ሁለቱ ሰዎች ግን ሄደው ወሬውን በየቦታው አዳረሱት።
32ሁለቱ ሰዎች እየሄዱ እያሉ እነሆ፣ በጋኔን የተያዘ ዲዳ ወደ ኢየሱስ አመጡ።
33ጋኔኑም ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም ተገርመው፣ "እንዲህ ያለ ከዚህ በፊት በእስራኤል አልታየም" አሉ።
34ፈሪሳውያን ግን "አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው" ይሉ ነበር።
35ኢየሱስ ወደ ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ሄደ፣ በየምኩኲራቦቻቸውም ማስተማሩን፣ የመንግሥትን ወንጌል መስበኩንና፣ ማንኛውንም ዐይነት በሽታና ደዌ መፈወሱን ቀጠለ።
36ሕዝቡንም ሲያይ፣ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ነበርና ራራላቸው።
37ለደቀ መዛሙርቱም፣ "መከሩ ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው።
38ስለዚህ፣ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ፣ ወደ መከሩ ጌታ አጥብቃችሁ ጸልዩ" አላቸው።