1ኢየሱስ ከተራራው በወረደ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
2እነሆ፣ አንድ ለምጻም ወደ እርሱ መጣ፣ “ጌታ ሆይ፣ ፈቃደኛ ከሆንህ፣ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት በፊቱ ሰገደለት።
3ኢየሱስም፣ “ፈቃደኛ ነኝ ንጻ” በማለት እፉን ዘርግቶ ዳሰሰው። ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ።
4ኢየሱስ፣ “ተጠንቀቅ! ለማንም አትናገር። ዝም ብለህ ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ፣ምስክር እንዲሆናቸውም ሙሴ ያዘዘውን ስጦታ አቅርብ”አለው።
5ኢየሱስ ወደቅፍርናሆም በገባ ጊዜ፣ አንድ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ መጥቶ፣
6ጌታ ሆይ፣ "አገልጋዬ በከባድ ሕመም ሽባ ሆኖ ቤቴ ተኝቷል" በማለት ለመነው።
7ኢየሱስ፣ "መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።
8የመቶ አለቃውም መልሶ፣“ጌታ ሆይ፣ አንተ ወደ ቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፣ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር አገልጋዬም ይፈወሳል” አለው፡፡
9እኔ ደግሞ ከሌላው ሥልጣን ሥር ያለሁና በእኔም ሥልጣን ሥር ወታደሮች ያሉኝ ሰው ነኝ። አንዱን “ሂድ” ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም “ና” ብለው ይመጣል፣ አገልጋዬንም 'ይህን አድርግ' ብለው ያደርጋል"፡፡
10ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በጣም ተደነቀ፣ ይከተሉት ለነበሩት ሰዎችም “እውነት ነው የምነግራችሁ፣ በእስራኤል እንኳ እንደዚህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም” አላቸው፡፡
11እነግራችኋለሁ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፣ በእግዚአብሔር መንግሥትም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በማዕድ ይቀመጣሉ።
12የመንግሥት ልጆች ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪው ጨለማ ይጣላሉ፡፡
13ኢየሱስም የመቶ አለቃውን፣ “ሂድ! እንደ እምነትህ ይሁንልህ" አለው። አገልጋዩም በዚያው ሰዓት ተፈወሰ ፡፡
14ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስን አማት በትኩሳት ታማ ተኝታ አገኛት።
15ኢየሱስ እጅዋን ነካት፣ ትኩሳቱም ለቀቃት፣ ተነሥታም ታገለግለው ጀመር።
16በመሸ ጊዜ፣ ሕዝቡ አጋንንት የያዙአቸውን ብዙዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፣ እርሱም በቃሉ፣ መናፍስቱን አስወጣቸው፤ ታመው የነበሩትንም ሁሉ ፈወሳቸው።
17በዚህ ዐይነት፣ በነቢዩ ኢሳይያስ፣ “እርሱ ሕመማችንን ተቀበለ ደዌዎቻችንን ተሸከመ” ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ።
18ኢየሱስም በዙሪያው ያሉትን ሕዝብ ባየ ጊዜ፣ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።
19ከዚያም አንድ ጸሐፊ ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
20ኢየሱስም "ቀበሮዎች ጉድጓድ የሰማይ ወፎችም ጎጆዎች አሏቸው። የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያሳርፍበት ምንም ስፍራ የለውም"አለው።
21ከደቀመዛሙርቱም ሌላው፣ "ጌታ ሆይ፣ በመጀመሪያ እንድሄድና አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።"
22ኢየሱስ ግን፣ “ተከተለኝ፣ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው” አለው።
23ኢየሱስ ወደ ጀልባ በገባ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገቡ።
24እነሆም፣ በባሕሩ ላይ ታላቅ ማዕበል ተነሥቶ ጀልባዋ በማዕበል ተሸፈነች። ኢየሱስ ግን ተኝቶ ነበር።
25ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ መጥተው፣ "ጌታ ሆ፣ እድነን ልንጠፋ ነው" በማለት ቀሰቀሱት።
26ኢየሱስ፣ "እናንተ እምነት የጐደላችሁ ስለምን ፈራችሁ?”አላቸው። ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠፀ፣ ከዚያ በኋላ ታላቅ ጸጥታ ሆነ።
27ሰዎቹም ተገርመው፣ "ይህ ምን ዓይነት ሰው ነው? ነፋሳትና ባሕሩም እንኳ ይታዘዙለታል" አሉ።
28ኢየሱስም ወደ ማዶ ወደ ጌርጌሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፣ አጋንንት የተቆጣጠራቸው ሁለት ሰዎች ተገናኙት። የመጡትም ከመቃብር ነበርና በዚያ ማንም ማለፍ እስከማይችል ድረስ በጣም ኅይለኞች ነበሩ።
29እነሆም፣ እየጮኹ፣ "አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፣ እኛ ከአንተ ምን ጉዳይ አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?" አሉ።
30ከዚያ አካባቢ ብዙ ሳይርቅ በግጦሽ ላይ ያሉ ብዙ ዐሳማዎች ነበሩ።
31አጋንንቱም ኢየሱስን፣ "የምታወጣን ከሆነ ወደዚያ የዐሳማዎች መንጋ ስደደን" ብለው መለመናቸውን ቀጠሉ።
32ኢየሱስም፣ "ሂዱ!"አላቸው። አጋንንቱም ወጥተው ዐሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ እነሆም፣ የዐሳማዎቹ መንጋ ሁሉ ወደ ታች ቁልቁለቱን እየተጣደፉ ወደ ባሕሩ ወርደው ውሃው ውስጥ ገብተው ጠፉ፡፡
33እነዚያም ዐሳማዎቹን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች ሸሽተው ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ሁሉ ፣ በአጋንንት ተይዘው ስለ ነበሩት ሰለ ሁሉቱ ሰዎችም አወሩ።
34የከተማውም ሕዝብ ሁሉ ኢየሱስን ለማየት መጡ። ባዩትም ጊዜ አካባቢያቸውን ለቆ አንዲሄድ ለመኑት።