1ሁለቱን ደቀ መዛሙርት በአንድ ላይ ጠርቶ፣ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ሁሉንም ዐይነት በሽታና ደዌ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡
2የዐስራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ የመጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣
3ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፣
4ቀነናዊው ስምዖን፣አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
5ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን "አሕዛብ ወደሚኖሩበት የትኛውም ቦታ አትሂዱ፤ ወደ የትኛውም የሳምራውያን ከተማ አትግቡ።
6ከዚያ ይልቅ ወደ ጠፉት የእስራኤል ቤት በጐች ሂዱ።
7መንግሥተ ሰማይ ቀርባለች፣ ብላችሁ ስበኩ" ብሎ አስተምሮ ላካቸው።
8ሕሙማንን ፈውሱ፣ ሙታንን አስነሡ፣ ለምጻሞችን አንጹ፣ አጋንንትንም አስወጡ፣ በነጻ ተቀብላችኋል በነጻ ስጡ።
9በቦርሳችሁ ወርቅ ብር ወይም ናስ አትያዙ፤
10ለሠራተኛ ቀለቡ የሚገባው ስለ ሆነ፣ ለመንገዳችሁ ሻንጣ ወይም ትርፍ ልብስ፣ ወይም ጫማ፣ ወይም በትር አትያዙ።
11ወደ የትኛውም ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ፣ በዚያ ተገቢ የሆነው ሰው ማን እንደሆን እወቁ፤ ለቃችሁ እስከምትሄዱ ድረስ በዚያው ቆዩ።
12ወደ ቤት ስትገቡ፣ ሰላምታ ስጡ።
13ቤቱ የሚገባው ከሆነ ሰላማችሁ ይደርሰዋል፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ይመለስላችኋል።
14እናንተን የማይቀበላችሁን፣ ወይም ቃላችሁን የማይሰማውን በተመለከተ ግን፣ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።
15እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ይቀልላቸዋል።
16ተመልከቱ፣ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ስለዚህ፣ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
17ከሰዎች ተጠበቁ፣ ወደ ፍርድ ሸንጎ ያቅርቧችኋል፣ በምኲራባቸውም ይገርፏችኋል።
18ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን፣ በእኔም ምክንያት ወደ ገዥዎችና ነገሥታት ፊት ትቀርባላችሁ።
19ለፍርድም ሲያቀርቧችሁ፣ በዚያች ሰዓት የምትናገሩት ስለሚሰጣችሁ፣ ምን ወይም እንዴት እንደምትናገሩ አትጨነቁ።
20በእናንተ ውስጥ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩት እናንተ አይደላችሁም።
21ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን፣ ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ተነሥተው ያስገድሏቸዋል።
22ከስሜ የተነሣ በሰው ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ነገር ግን ማንም እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።
23በዚህች ከተማ በሚያሳድዷችሁ ጊዜ ወደሚቀጥለው ከተማ ሽሹ። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ ከመምጣቱ በፊት፣ የእስራኤልን ከተሞች አታዳርሱም።
24ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ወይም አገልጋይ ከጌታው በላይ አይደለም።
25ለደቀ መዝሙር ልክ እንደ መምህሩ፣ ለአገልጋይም ልክ እንደ ጌታው መሆን ይበቃዋል።
26እንግዲህ አትፍሯቸው፤ የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ የተደበቀ ምንም የለም።
27በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን፣ በሹክሹክታ የምትሰሙትንም በአደባባይ ተናገሩት፡፡
28ሥጋን እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ከዚያ ይልቅ ነፍስንም፣ ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ፡፡
29ሁለት ድንቢጦች በትንሽ ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ሆኖም አንዷም ብትሆን አባታችሁ ሳያውቅ በመሬት ላይ አትወድቅም፡፡
30የእናንተ ግን የራሳችሁ ጠጉር እንኳን ሳይቀር የተቈጠረ ነው፡፡
31አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ፡፡
32ስለዚህ በሰዎች ፊት ለሚመሰክርልኝ፣ እኔም በሰማይ ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡
33በሰው ፊት የሚክደኝን ግን፣ እኔም ደግሞ በሰማይ ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡
34በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ፣ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም፡፡
35ሰውን በአባቱ ላይ፣ ሴት ልጅን በእናቷ ላይ፣ ምራትን በአማቷ ላይ ለማነሣሣት መጥቻለሁ፡፡
36የሰውም ጠላቶቹ የገዛ ቤተ ሰቦቹ ይሆናሉ፡፡
37አባትን ወይም እናትን ከእኔ የበለጠ የሚወድ ለእኔ የተገባ አይደለም፤ እንዲሁም ወንድ ልጅን፣ ወይም ሴት ልጅን ከእኔ የበለጠ የሚወድ ለእኔ የተገባ አይደለም።
38መስቀሉን ተሸክሞ፣ ከኋላዬ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡
39ሕይወቱን የሚያገኛት ያጣታል፤ ስለ እኔ ብሎ ሕይወቱን የሚያጣት ግን ያገኛታል፡፡
40እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡
41ነቢይ ስለ ሆነ ነቢይን የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅ ስለ ሆነ ጻድቅን የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል፡፡
42እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ ታናናሾች ለአንዱ፣ ደቀ መዝሙሬ ስለ ሆነ፣ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሚሰጥ ማንም፣ በምንም ዐይነት ዋጋውን አያጣም፡፡