1አትፍረዱ፥ እናንተም አይፈረድባችሁም።
2በምትፈርዱበት ፍርድ፥ ይፈረድባችኋል፤በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ፥ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል።
3በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታስተውል፥ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ የምታየው ለምንድን ነው?
4በአንተ ዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ፣ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ማለት እንዴት ትችላለህ?
5አንተ ግብዝ! በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ በደንብ አይተህ ለማውጣት፣ በመጀመሪያ በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ አስወግድ።
6በእግራቸው እንዳይረግጡትና እናንተንም እንዳይቦጫጭቁዋችሁ፤ ቅዱስ የሆነውን ለውሾች አትስጡ፥ እንቁዎቻችሁንም ለዐሳማዎች አትጣሉ።
7ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፥ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።
8የሚለምን ሰው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግ ሰውም ያገኛል፥ ለሚያንኳኳም ሰው ይከፈትለታል።
9ከእናንተ መካከል ልጁ እንጀራ ሲለምነው፣ ድንጋይ የሚሰጠው፣
10ዐሣ ሲለምነው፣ እባብ የሚሰጠው? ምን ዐይነት ሰው ነው?
11እንግዲህ፥ እናንተ ክፉዎች የሆናችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ የሚኖር አባታችሁ ለሚለምኑት አብዝቶ መልካም ስጦታን እንዴት አይስጣቸውም?
12ስለዚህ፣ ማንኛውንም ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ፣ እናንተም ልታደርጉላቸው ይገባል፤ ምክንያቱም ሕጉም ነቢያቱም የሚያስተምሩት ይህንኑ ነው፡፡
13በጠባቡ በር ግቡ፣ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ሰፊ፣ የሚሄዱበትም ብዙዎች ናቸው፡፡
14በሩ ጠባብ፣ ወደ ሕይወት የሚወስደውም መንገድ ቀጭን ስለ ሆነ፣ የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው፡፡
15የበግ ቆዳ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፣ በትክክል ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑ፣ ከሃሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።
16በሚያፈሩት ፍሬ ታውቋቸዋላችሁ፡፡ሰው ከእሾኽ የወይን ፍሬ፣ ወይም ከኩርንችት በለስ ሊሰበስብ ይችላልን?
17እንደዚያው፥ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፣ መጥፎ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ያፈራል።
18መልካም ዛፍ ሆኖ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ፣ ወይም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ የለም።
19ማንኛውም መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፣ ወደ እሳትም ይጣላል።
20እንግዲህ በሚያፈሩት ፍሬ ታውቋቸዋላችሁ።
21በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እንጂ፣" ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣" እያለ የሚጠራኝ ሁሉ፣ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚገባ አይደለም፡፡
22በዚያ ቀን ብዙዎች፣ "ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት ተናግረን አልነበረም እንዴ፣ በስምህ አጋንንት አስወጥተን አልነበረም እንዴ፣ በስምህስ ብዙ ታላላቅ ነገሮችን አድርገን አልነበረም እንዴ?" ይሉኛል፡፡
23እኔም፣ “እናንት ክፉ አድራጊዎች፣ የት ዐውቃችሁና ነው? ከእኔ ራቁ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ”
24ስለዚህ፣ ቃሎቼን የሚሰማና የሚታዘዛቸው ልክ ቤቱን በድንጋይ ላይ የመሠረተ አስተዋይ ሰውን ይመስላል፡፡
25ዝናብ ዘነበ፣ ጎርፍም ጎረፈ፣ ነፋስም ነፈሰ ያንን ቤት መታው፤ ይሁን እንጂ ቤቱ በዐለት ላይ ስለ ተመሠረተ፣ አልወደቀም፡፡
26ሆኖም ቃሌን ሰምቶ የማይታዘዝ፣ ቤቱን በአሸዋ ላይ የመሠረተ ሞኝ ሰውን ይመስላል፡፡
27ዝናብ ዘነበ፣ ጎርፍ ጎረፈ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንንም ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም ከባድ ሆነ ።
28ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ሲጨርስ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፡፡
29ያስተማረውም እንደ ባለስሥልጣን እንጂ ፣እንደ ጽሐፍት አልነበረም።