መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 27

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ።
2አስረው ወሰዱትና ለአገሩ ገዢው ለጲላጦስ አስረከቡት።
3አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፣ ሠላሣውን ጥሬ ብር ለካህናት አለቆቹና ለሽማግሌዎቹ መልሶ፣
4"ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠት በድያለሁ" አለ። እነርሱ ግን፣ “ታዲያ፣ እኛን ምን አገባን? የራስህ ጉዳይ ነው” አሉት።
5ከዚያም ጥሬ ብሩን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወረወረና ወጥቶ ራሱን ሰቀለ።
6የካህናት አለቆቹ ጥሬ ብሩን ወስደው፣ “ይህ የደም ዋጋ ስለ ሆነ፣ ከቤተ መቅደሱ ገንዘብ ጋር መቀላቀል ተገቢ አይደለም” አሉ።
7እርስ በርሳቸው ተነጋግረው የእንግዶች መቀበሪያ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት።
8ከዚህ የተነሣ ያ መሬት እስከዚህ ጊዜ ድረስ፣ “የደም መሬት” ተባለ።
9በነቢዩ ኤርምያስ፣ “የእርሱ ዋጋ እንዲሆን የእስራኤል ልጆች የተመኑለትን ሠላሣ ጥሬ ብር ወሰዱ፣
10እግዚአብሔር እንደ አዘዘኝ ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት” ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ።
11ኢየሱስ በአገረ ገዢው ፊት ቆመ፤ አገረ ገዢውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህ እንዴ?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተ እንዳልኸው ነው” በማለት መለሰለት።
12የካህናት አለቆችና፣ ሽማግሌዎቹ፣ ሲከሱት ምንም አልመለሰም።
13በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “በአንተ ላይ የሚያቀርቡትን ክስ ሁሉ አትሰማምን?” አለው።
14እርሱ ግን አንድ ቃል እንኳ ስላልመለሰለት አገረ ገዡ በጣም ተደነቀ።
15በዓል ሲመጣ አገረ ገዢው ሕዝቡ የሚፈልጉትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።
16በዚያን ጊዜ በርባን የሚሉት ከባድ ወንጀለኛ በእስር ቤት ውስጥ ነበር።
17ተሰብስበው እያለ ጲላጦስ፣ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ፣ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” አላቸው።
18ምክንያቱም አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር።
19በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ እያለ ሚስቱ፣ “በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ፤ እርሱን በተመለከተ በዚህ ሌሊት በሕልሜ ብዙ መከራ ተቀብያለሁ” የሚል ቃል ላከችበት።
20የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ በርባን እንዲፈታና ኢየሱስ እንዲገደል እንዲጠይቁ ሕዝቡን ቀሰቀሱ።
21አገረ ገዢው፣ “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም፣”በርባንን” አሉ።
22ጲላጦስም፣ “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም፣ “ስቀለው” በማለት መለሱ።
23እርሱም፣ “ለምን፣ የሠራው ወንጀል ምንድንነው?” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “ስቀለው” እያሉ የበለጠ ጮኹ።
24ስለዚህ ምንም ማድረግ እንዳልቻለና እንዲያውም ዐመፅ እየተነሣ መሆኑን ጲላጦስ ባየ ጊዜ፣ በሕዝቡ ፊት እጁን በውሃ ታጥቦ፣ “እኔ ከዚህ ንጹሕ ሰው ደም ነጻ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የእናንተው ነው” አለ።
25ሕዝቡ ሁሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።
26ከዚያም በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቅሉት ሰጣቸው።
27የአገረ ገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱትና ወታደሮቹን ሁሉ ሰበሰቡ።
28ልብሱን ገፍፈው ቀይ ልብስ አለበሱት።
29ከዚያም የእሾኽ አክሊል ሠርተው በራሱ ላይ ደፉ፣ በቀኝ እጁ በትር አስያዙት፤ በፊቱ ተንበርክከውም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ አሾፉበት።
30ፊቱ ላይም ተፉበት፤ በትሩን ወስደው ራሱን መቱት።
31ካፌዙበትም በኋላ ልብሱን አውልቀው የራሱን ልብስ አለበሱትና እንዲሰቀል ወሰዱት።
32እንደወጡ ስምዖን የሚሉት የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት።
33ጎልጎታ ወደሚባል ቦታ መጡ፤ ትርጕሙም “የራስ ቅል” ማለት ነው።
34ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈለገም።
35በሰቀሉት ጊዜ ዕጣ በመጣጣል ልብሶቹን ተከፋፈሉ፤
36ተቀምጠው ይጠብቁትም ጀመር።
37ከራሱ በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሕፈት አኖሩ።
38ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ ሌላው በግራው በኩል ከእርሱ ጋር ተሰቅለው ነበር።
39የሚያልፉ ሰዎችም ሰደቡት፤ ራሳቸውን እየነቀነቁም
40“ቤተ መቅደሱን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራ ራስህን አድን። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ” ይሉት ነበር።
41በተመሳሳይ መንገድ የካህናት አለቆች፣ ከአይሁድ የሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎቹ ጋር አብረው፣
42“ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም። እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ነው፣ ከመስቀል ይውረድ፣ ከዚያም እኛ እናምንበታለን።
43በእግዚአብሔር ተማምኖአል፤ እርሱ ከወደደ ያድነው፤ ምክንያቱም፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሏል" እያሉ ያፌዙበት ነበር።
44ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንዲሁ ይሰድቡት ነበር።
45ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ምድሩን ሁሉ የሚሸፍን ጨለማ ሆነ።
46በዘጠኝ ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰባቅታኒ” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጒሙም፣ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ማለት ነው።
47እዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው” አሉ።
48ወዲያውኑ ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሄደና ስፖንጁን የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነክሮ በሸንበቆ በትር አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው።
49የተቀሩትም፣ "እስቲ ተዉት፤ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን” አሉ።
50ከዚያም ኢየሱስ በድጋሚ በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ።
51የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተከፈለ፤ ምድር ተናወጠ፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤
52መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩ ብዙ ቅዱሳን ተነሡ።
53ከትንሣኤው በኋላ ከመቃብር ወጡ፤ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ።
54የመቶ አለቃውና ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩ ሰዎች የምድር መናወጡንና የሆኑትን ነገሮች ሲያዩ በጣም ፈርተው፣ "በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነው" አሉ።
55እርሱን ለመርዳት ከገሊላ ጀምሮ ኢየሱስን ተከትለው የነበሩ ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር።
56ማርያም መግደላዊት፣ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም፣ እንዲሁም የዘብዲዎስ ልጆች እናት ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
57ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚሉት አንድ ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር።
58ወደ ጲላጦስ መጥቶ የኢየሱስን አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ።
59ዮሴፍ አስከሬኑን ወስዶ፤ በንጹሕ ናይለን ጨርቅ ጠቀለለውና
60ለራሱ ከዐለት በሠራው መቃብር ውስጥ አኖረው። ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባልሎ መቃብሩ ደጃፍ ላይ አድርጎ ሄደ።
61ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም መቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።
62በሚቀጥለው ቀን ከዝግጅት በኋላ የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያን በአንድነት ከጲላጦስ ጋር ተሰበሰቡ።
63እንዲህም አሉ፣ "ጌታ ሆይ፣ ያ አሳሳች በሕይወት በነበረ ጊዜ፣ 'ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ' ብሎ እንደ ነበር ትዝ አለን።
64ስለሆነም፣ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩ በጥንቃቄ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ አለበለዚያ ግን፣ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ሥጋውን ይሰርቁና ለሕዝቡ፣ ‘ከሞት ተነሣ’ ይላሉ፤ የኋላው ስሕተት ከመጀመሪያው የከፋ ይሆናል” አሉት።
65ጲላጦስም፣ “ጠባቂ ወስዳችሁ፣ የሚቻላችሁን ያህል በጥንቃቄ እንዲጠበቅ አድርጉ” አላቸው።
66ስለዚህ ሄደው መቃብሩ በጥንቃቄ እንዲጠበቅ አደረጉ፤ ድንጋዩን አተሙ፤ ጠባቂ አኖሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።