1ሰንበት እንዳለፈ፣ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ማለዳ፣ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም ወደ መቃብሩ መጡ።
2የጌታ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ነበርና ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ መጥቶም ድንጋዩን አንከባልሎ በላዩ ተቀመጠ።
3መልኩ እንደ መብረቅ፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።
4ጠባቂዎቹ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ እንደ ሞተ ሰውም ሆኑ።
5መልአኩም እንዲህ በማለት ተናገረ፤ "አትፍሩ፤ ተሰቅሎ የነበረውን ክርስቶስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ።
6እንደ ተናገረ ተነሥቷል እንጂ፣ እዚህ የለም፤ ኑና የነበረበትን ቦታ እዩ።
7በፍጥነት ሄዳችሁ፣ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ በማለት ንገሩ፤ 'እርሱ ከሞት ተነሥቷል፤ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። እዚያ ታዩታላችሁ።' እንግዲህ ነግሬአችኋለሁ።”
8ሴቶቹ ፈጥነው በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር ከመቃብሩ እየሮጡ ሄዱ።
9እነሆ ኢየሱስ አገኛቸውና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ሴቶቹም እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት።
10ከዚያም ኢየሱስ፣ "አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩ፤ እዚያ ያዩኛል" አላቸው።
11ሴቶቹ እየሄዱ እያሉ፣ ከጠባቂዎች ጥቂቱ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሩ።
12ካህናቱ ከሽማግሌዎቹ ጋር ተገናኝተው የሆነውን ሁሉ ሲናገሩ፣ ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ በመስጠት፣
13“እኛ ተኝተን እያለ ፣ ሌሊት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መጥተው አስክሬኑን ሰረቁ” ብለው እንዲናገሩ ነገሩዋቸው።
14ይህ ወሬ ወደ አገረ ገዢው ከደረሰ፤ እኛ እናሳምነዋለን፣ እናንተም ከሥጋት ነጻ ትሆናላችሁ" አሏቸው።
15ወታደሮቹ ገንዘቡን ተቀብለው ፣ እንደ ተነገራቸው አደረጉ። ይህ ወሬ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ መሐል በሰፊው ተሰራጭቷል።
16ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ወደ ገሊላ ኢየሱስ ወደ ነገራቸው ተራራ ሄዱ።
17ባዩት ጊዜ ሰገዱለት፤ አንዳንዶቹ ግን ተጠራጥረው ነበር።
18ኢየሱስ ወደ እነርሱ መጥቶ፣ “በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠኝ።
19ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ፣ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስም ስም እያጠመቃችኋቸው፤
20እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲያደርጉ እያስተማራችኋቸው፤ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”