መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 26

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ እነዚህን ቃሎች ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤
2"ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፣ የሰው ልጅም ተሰቅሎ እንዲገደል ተላልፎ ይሰጣል፡፡"
3ከዚያ የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚሉት ሊቀ ካህናት ግቢ ውስጥ ተሰበሰቡ፤
4ኢየሱስን በረቀቀ ዘዴ ለማሰርና ለመግደል ተማከሩ፡፡
5ምክንያቱም፣ በሕዝቡ መሓል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም እያሉ ነበር፡፡
6ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት
7ማዕድ ላይ ተቀምጦ እያለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ ያለበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣችና ራሱ ላይ አፈሰሰች፡፡
8ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲያዩ በጣም ተቈጥተው፣ "ይህ ብክነት ምንድን ነው?
9ይህ እኮ ከፍ ባለ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር" አሉ፡፡
10ኢየሱስም ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፣ "ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፡፡
11ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልሆንም፡፡
12ይህን ሽቱ እኔ ላይ ባፈሰሰች ጊዜ ለቀብሬ አድርጋዋለች፡፡
13እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌል በመላው ዓለም ሲሰበክ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይህች ሴት ያደረገችውም ይነገርላታል።"
14ከዚያም የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆቹ ሄዶ፣
15"እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ ለእኔ ምን ትሰጡኛላችሁ?" አላቸው፡፡ እነርሱም ሠላሣ ጥሬ ብር ተመኑለት፡፡
16ከዚያ ጊዜ ወዲህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ጀመር፡፡
17በቂጣ በዓል በመጀመሪያው ግን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ "የፋሲካን እራት እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?" አሉት፡፡
18እርሱም፣ "ከተማው ውስጥ ወዳለ አንድ ሰው ሂዱና፣ 'መምህሩ "ጊዜዬ ደርሷል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት ማክበር እፈልጋለሁ' ይልሃል በሉት'" አላቸው፡፡
19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንደ ነገራቸው አደረጉ፤ የፋሲካንም እራት አዘጋጁለት፡
20ምሽት ላይ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ለመብላት ተቀመጠ፡፡
21በመብላት ላይ እያሉ፣ "እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል" አላቸው፡፡
22እነርሱ በጣም ዐዘኑ፤ እያንዳንዱም፣ "እኔ እሆንን?" በማለት ይጠያየቁ ጀመር፡፡
23እርሱም፣ "አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ወደ ሳሕኑ የሚሰደው ነው፡፡
24የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ግን ወዮለት! ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር" በማለት መለሰላቸው፡፡
25አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ፣ "መምህር ሆይ፣ እኔ ነኝ እንዴ?" አለው፤ እርሱም፣ "አንተው ራስህ ብለኸዋል" አለው፡፡
26በመብላት ላይ እያሉ፣ ኢየሱስ እንጀራ አንሥቶ ባርኮ ቈረሰ፡፡ "እንካችሁ ውሰዱ፣ ብሉት፤ ይህ ሥጋዬ ነው" ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡
27ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነና ሰጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ "ሁላችሁም ጠጡት
28ይህ ለብዙዎች ኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳኑ ደሜ ነው፡፡
29እንደ ገና በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር እስክጠጣው ድረስ ከእንግዲህ ከዚህ ወይን ፍሬ እንደማልጠጣ ግን እነግራችኋለሁ፡፡"
30መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ፡፡
31ያኔ ኢየሱስ፣ "በዚህ ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ምክንያት ትሰናከላላችሁ፤ ምክንያቱም፣ 'እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ' ተብሎ ተጽፎአል፡፡
32ከተነሣሁ በኋላ ግን ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ" አላቸው፡፡
33ጴጥሮስ ግን፣ "ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም" አለው፡፡
34ኢየሱስም፣ "እውነት እልሃለሁ ፣ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ" አለው፡፡
35ጴጥሮስም፣ "ከአንተ ጋር መሞት ቢኖርብኝ እንኳ አልክድህም" አለ፡፡ ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደዚያው አሉ፡፡
36ከዚያም ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚሉት ቦታ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም፣ "ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ ድረስ እዚህ ሁኑ" አላቸው፡፡
37ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመር፡፡ ከዚያም፣
38"ነፍሴ፣ እስከ ሞት ድረስ በጣም ዐዝናለች፡፡ እዚህ ሆናችሁ ከእኔ ጋር ትጉ" አላቸው፡፡
39ጥቂት ራቅ ብሎ በመሄድ በግንባሩ ወድቆ ጸለየ፤ "አባት ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ይሁን እንጂ፣ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን" አለ፡፡
40ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም፣ "ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት ያህል እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን?
41ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፡፡ መንፈስ በእርግጥ ፈቃደኛ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው" አለው፡፡
42ለሁለተኛ ጊዜ ጥቂት ፈቀቅ ብሎ ጸለየ፤ "አባት ሆይ፣ እኔ ካልጠጣሁት በቀር ይህ የማያልፍ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይሁን" አለ፡፡
43እንደ ገና ሲመጣ ዐይኖቻቸው ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፡፡
44እንደ ገና ትቶአቸው ሄዶ ለሦስተኛ ጊዜ ያንኑ ቃል ጸለየ፡፡
45ከዚያም ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ፣ "አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? ጊዜው ደርሷል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፡፡
46እንግዲህ ተነሡ እንሂድ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል" አላቸው፡፡
47ገና እየተናገረ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፣ ከእርሱም ጋር ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች የመጡ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡
48በዚህ ጊዜ አሳልፎ የሚሰጠው፣ "እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት" የሚል ምልክት ሰጣቸው፡፡
49ወዲያውኑ ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ "መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!" ብሎ ሳመው፡፡
50ኢየሱስም፣ "ወዳጄ፣ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም" አለው፡፡ ከዚያም መጡ ኢየሱስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፣ ያዙትም።
51ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፍ አወጣ፤ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ መትቶ ቈረጠ፡፡
52ያኔ ኢየሱስ፣ "ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ፡፡
53አባቴን ብጠይቅ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ መላእክት የማይልክልኝ ይመስልሃል?
54እንደዚያ ከሆነ ይህ እንደሚሆን የሚናገረው መጽሐፉ ቃል እንዴት ይፈጸማል?" አለው፡፡
55በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡ፣ "ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁ? በየቀኑ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ እያስተማርሁ ነበርሁ፡፡ እናንተም አልያዛችሁኝም ነበር፡፡
56የነቢያት መጽሐፍ እንዲፈጸም ይህ ሆኗል" አላቸው፡፡ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ፡፡
57ኢየሱስን የያዙ ሰዎች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎቹ ተሰብስበው ወደ ነበሩበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ቤት ወሰዱት፡፡
58ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሚሆነውን ለማየት ከጠባቂዎቹ ጋር ተቀመጠ፡፡
59እርሱን ለማስገደል የካህናት አለቆቹና ሸንጎው ሁሉ በኢየሱስ ላይ በሐሰት የሚመሰክሩበትን ሰዎች እየፈለጉ ነበር፡፡
60ምንም እንኳ ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም፤ በቂ ማስረጃ አላገኙም፡፡ በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ወደ ፊት መጥተው፣
61"ይህ ሰው፣ 'የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ እንደ ገና ልሠራው እችላለሁ' ብሏል" አሉ፡፡
62ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ፣ "መልስ የለህም? በአንተ ላይ እየመሰከሩብህ ያለው ምንድን ነው?" አለው፡፡
63ኢየሱስ ግን ዝም አለ፡፡ ሊቀ ካህናቱም፣ "በሕያው እግዚአብሔር አዝሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን አለመሆንህን ንገረን" አለው፡፡
64ኢየሱስም፣ "አንተው ራስህ አልህ፤ ግን ልንገርህ፣ ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያለህ" በማለት መለሰለት፡፡
65ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀደደና፣ "እግዚአብሔርን ተሳድቧል፤ ታዲያ፣ ምስክር የምንፈልገው ለምንድን ነው? አሁን ስድቡን ሰምታችኋል
66ለመሆኑ፣ ምን ታስባላችሁ?" አለ፡፡ እነርሱም መልሰው፣ "ሞት ይገባዋል" አሉ፡፡
67ከዚያም ፊቱ ላይ ተፉበት፣ በጡጫና በጥፊ መቱት፤
68"አንተ ክርስቶስ እስቲ ትንቢት ተናገር፡፡ ለመሆኑ፣ በጥፊ የመታህ ማን ነው?" አሉት፡፡
69በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እደጅ ግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት አገልጋይ ልጅ ወደ እርሱ መጥታ፣ "አንተም ደግሞ ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርህ" አለችው፡፡
70እርሱ ግን፣ "ምን እየተናገርሽ እንደ ሆነ አላውቅም" በማለት በሁሉም ፊት ካደ፡፡
71ከግቢው ወደሚያስወጣው በር እየሄደ እያለ፣ ሌላ አገልጋይ ልጅ አየችውና እዚያ ለነበሩት፣ "ይህኛውም ሰውየ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበረ" አለች፡፡
72እርሱም፣ "ሰውየውን አላውቀወም" በማለት በመሐላ ጭምር በድጋሚ ካደ፡፡
73ጥቂት ቆየት ብሎ እዚያ ቆመው የነበሩት መጥተው ጴጥሮስን፣ "በርግጥ አንተም ብትሆን ከእነርሱ አንዱ ነህ፤ አነጋገርህ ራሱ ያጋልጥሃል" አሉት፡፡
74ከዚያም፣ "ሰውየውን ጨርሶ አላውቀውም" በማለት ይራገምና ይምል ጀመር፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ፡፡
75ጴጥሮስ "ዶሮ ሳይጮኽ ሦስቴ ትክደኛለህ" በማለት ኢየሱስ የተናገረውን አስታወሰ፡፡ ከዚያ ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።