1መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡ ዐሥር ድንግሎችን ትመስላለች።
2ዐምስቱ ሞኞች፣ ዐምስቱ ልባሞች ነበሩ።
3ሞኞቹ ድንግሎች መብራታቸውን ይዘው ሲሄዱ ምንም ዘይት አልያዙም ነበር።
4ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር ዘይትም ይዘው ነበር።
5ሙሽራው በዘገየ ጊዜ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ሁሉም ተኙ።
6ዕኩለ ሌሊት ላይ ግን፣ “ሙሽራው መጥቶአልና ወጥታችሁ ተቀበሉት!” የሚል ሁካታ ሆነ።
7ያኔ እነዚያ ድንግሎች ሁሉ ተነሥተው መብራታቸውን አዘጋጁ።
8ሞኞቹም ልባሞቹን፣ “መብራታችን እየጠፋ ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ጥቂት ስጡን” አሏቸው።
9ልባሞቹ ግን፣ “ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ስለሌለን፣ ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ” በማለት መለሱአቸው።
10ለመግዛት ሲሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ግብዣው ላይ ለመገኘት ከእርሱ ጋር ሄዱ፤ በሩም ተዘጋ።
11በኋላ ሌሎቹ ድንግሎች መጥተው፣ “ጌታው፣ በሩን ክፈትልን” አሉ።
12እርሱ ግን መልሶ፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም” አላቸው።
13ስለዚህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ።
14ነገሩ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ያሰበ ሰውን ይመስላልና፤ አገልጋዮቹን ጠርቶ በሀብት በንብረቱ ሁሉ ላይ ኀላፊነት ሰጣቸው።
15እንደ ዐቅማቸው መጠን ለአንዱ ዐምስት መክሊት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸውና ሄደ።
16ዐምስት መክሊት የተቀበለው ወዲያውኑ ሄዶ ነገደበት፤ ሌላ ዐምስት አተረፈ።
17ሁለት መክሊት የተቀበለውም እንደዚያው ሌላ ሁለት መክሊት አተረፈ።
18አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን ሄዶ ጉድጓድ ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።
19ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ መጣና ተሳሰባቸው።
20ዐምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ሌላ ዐምስት መክሊት ጨምሮ አመጣና፣ “ጌታ ሆይ፣ ዐምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እኔ ግን ሌላ ዐምስት መክሊት አተረፍሁ” አለ።
21ጌታውም፣ 'አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ ደግ አደረግህ! በጥቂት ነገሮች ታምነሃል፤ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።' አለው።
22ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው አገልጋይም መጥቶ፣ ‘ጌታ ሆይ፣ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር። ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌአለሁ’ አለ።
23ጌታውም፣ 'አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ ደግ አደረግህ! በጥቂት ነገሮች ታምነሃል፤ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
24ከዚያም አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ መጥቶ፣ 'ጌታ ሆይ፣ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ።
25ስለዚህ ፈራሁ፤ መክሊትህን መሬት ውስጥ ቀበርሁት። መክሊትህ ይኸውልህ' አለው።
26ጌታው ግን መልሶ፣ 'አንተ ዐመፀኛና ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበት የምሰበስብ መሆኔን ታውቃለህ።
27ስለዚህ ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ይገባህ ነበር፤ እኔ ስመጣ ከነወለዱ እወስደው ነበር' አለው።
28ስለዚህ መክሊቱን ከእርሱ ወስዳችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት።
29ላለው የበለጠ እንዲያውም የተትረፈረፈ ይሰጠዋል። ምንም ከሌለው ግን፣ ያው ያለው ነገር እንኳ ይወሰድበታል።
30ይህን የማይረባ አገልጋይ አውጡና ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት” አለ።
31የሰው ልጅ በክብሩ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር ሲመጣ፣ በክብር ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል።
32አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ ሕዝቡን ይለያቸዋል።
33በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን በግራው ያደርጋቸዋል።
34ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ 'እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።
35ተርቤ ነበር ምግብ ሰጣችሁኝ፤ ተጠምቼ ነበር የምጠጣው ሰጣችሁኝ፤ እንግዳ ሆኜ ነበር አስተናገዳችሁኝ፤
36ተራቊቼ ነበር አለበሳችሁኝ፤ ታምሜ ነበር ተንከባከባችሁኝ፤ ታስሬ ነበር ጠየቃችሁኝ' ይላቸዋል።
37ከዚያም ጻድቃን እንዲህ ብለው ይመልሱለታል፣ ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ያገኘንህና ያበላንህ ወይስ ተጠምተህ ያጠጣንህ መቼ ነው?
3838 እንግዳ ሆነህ ያየንህና ያስተናገድንህ መቼ ነው? ወይም ተራቊተህ ያለበስንህ መቼ ነው?
39ታምመህ የተንከባከብንህ ወይስ ታስረህ የጠየቅንህ መቼ ነው?’
40ንጉሡም መልሶ እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ለእነዚህ ታናናሽ ወንድሞቼ ያደረጋችሁትን ለእኔ አድርጋችሁታል።’
41ከዚያም በግራው ያሉትን፣ ‘እናንተ ርጉማን ከእኔ ራቁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ገሃነም እሳት ሂዱ።
42ምክንያቱም ‘ተርቤ ነበር አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ ነበር አላጠጣችሁኝም፤
43እንግዳ ሆኜ ነበር አልተቀበላችሁኝም፤ ተራቊቼ ነበር አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜ፣ ታስሬ ነበር፣ እናንተ ግን አልተንከባከባችሁኝም’ ይላቸዋል።
44እነርሱም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይም ተጠምተህ ወይም እንግዳ ሆነህ ወይም ተራቊተህ ወይም ታምመህ ወይም ታስረህ ያላገለገልንህ መቼ ነው?’
45እርሱም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ አለማድረጋችሁ ለእኔ አለማድረጋችሁ ነው’ ይላቸዋል።
46እነዚህ ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።"