መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 24

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ እየሄደ ሳለ፤ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ መጡ፡፡
2እርሱ ግን፣ "እነዚህን ሁሉ ነገሮች ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይፈርሳል እንጂ፣ አንድ ድንጋይ እንኳ በሌላ ድንጋይ ላይ እንደ ተነባበረ አይቀርም" በማለት መለሰላቸው፡፡
3በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ እያለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ መጥተው፣ "እስቲ ንገረን፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? የአንተ መምጣትና የዓለም መጨረሻስ ምልክቱ ምንድን ነው?" አሉት፡፡
4ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፣ "ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡
5ምክንያቱም ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ፤ 'እኔ ክርስቶስ ነኝ' እያሉ ብዙዎችን ያሳስታሉ
6ጦርነትንና የጦርነትን ዜና ትሰማላችሁ፤ በፍጹም እንዳትታወኩ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች እንዲሆኑ ግድ ነው፤ ቢሆንም፣ መጨረሻው ገና ነው፡፡
7ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል፡፡ በተለያየ ቦታ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል፡፡
8እነዚሀ ሁሉ ግን የምጥ ጣር መጀመሪያ ብቻ ናቸው፡፡
9ከዚያም ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሏችኋልም፡፡ ስለ ስሜ ሕዝቦች ሁሉ ይጠሏችኋል፡፡
10ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ ይካካዳሉ፤ እርስ በርስ ይጠላላሉ፡፡
11ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ብዙዎችን ያሳስታሉ፡፡
12ዐመፅ ስለሚበዛ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፡፡
13እስከ መጨረሻ የሚታገሥ ግን ይድናል፡፡
14ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን የመንግሥቱ ወንጌል ለመላው ዓለም ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል፡፡
15ስለዚህ በነቢዩ ዳንኤል የተነገረለት የጥፋት ርኲሰት በተቀደሰው ቦታ ቆሞ ስታዩ፣ (ያኔ አንባቢው ያስተውል)
16በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፣
17ጣራ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ያለውን ምንም ነገር ከቤቱ ለመውሰድ አይመለስ፣
18በእርሻ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ፡፡
19ልጆች ላሉአቸውና ለሚያጠቡ እናቶች ግን ወዮላቸው!
20ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡
21ምክንያቱም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስና ከዚያም በኋላ ፈጽሞ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል፡፡
22እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ፣ ማንም ሥጋ ለባሽ አይድንም ነበር፤ ለተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ፡፡
23ስለዚህ ማንም "እነሆ ክርስቶስ፣ እዚህ ነው" ወይም፣ 'ክርስቶስ እዚያ ነው' ቢላችሁ አትመኑ፡፡
24ምክንያቱም ብዙዎችን ለማሳሳት ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት መጥተው ታላላቅ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋሉ፤ ከተቻለም የተመረጡትን እንኳ ያሳስታሉ፡፡
25ይህ ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፡፡
26ስለዚህ፣ ‹ክርስቶስ በምድረ በዳ ነው› ቢሏችሁ ወደ ምድረ በዳ አትሂዱ ወይም ቤት ውስጥ ነው ቢሏችሁ አትመኑ፡፡
27መብረቅ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በአንዴ እንደሚታይ የሰው ልጅ ሲመጣ እንደዚያው ይሆናል፡፡
28የሞተ እንስሳ ባለበት ሁሉ፣ በዚያ አሞሮች ይሰበሰባሉ፡፡
29ከእነዚህ የመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፣ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኅይላት ይናወጣሉ፡፡
30ከዚያም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ነገዶች ሁሉ አምርረው ያለቅሳሉ፡፡ የሰው ልጅንም በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፡፡
31መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም፣ ከአንድ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ከአራቱም ነፋሳት ምርጦቹን ይሰበስቧቸዋል፡፡
32ከበለስ ዛፍ ተማሩ፡፡ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎች ብቅ ብቅ ሲሉ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ፡፡
33እናንተም እነዚህን ሁሉ ስታዩ እርሱ መቅረቡን፣ እንዲያውም በደጅ መሆኑን ዕወቁ፡፡
34እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፡፡
35ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም፡፡
36ስለዚያች ቀንና ሰዓት ግን ማንም አያውቅም፤ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ አያወቁም፤ አብ ብቻ እንጂ ወልድ እንኳ ቢሆን አያውቅም፡፡
37በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው፣ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡፡
38ከጥፋት ውሃ በፊት እንደ ነበረው ዘመን፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባ ድረስ ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር።
39ጐርፉ መጥቶ እስኪያጠፋቸው ድረስ ምንም አላወቁም፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንዲሁ ይሆናል፡፡
40በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሌላው ይቀራል፡፡
41ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች ሌላዋ ትቀራለች፡፡
42ስለዚህ ጌታችሁ በምን ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተጠንቀቁ፡፡
43ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባው በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ የቤቱ ባለቤት ቢያውቅ ኖሮ ይጠነቀቅ ነበር፤ ቤቱ አይዘረፍም ነበር፡፡
44የሰው ልጅ ባልጠበቃችሁት ሰዓት ስለሚመጣ እናንተም ብትሆኑ ተዘጋጅታችሁ መጠበቅ አለባችሁ፡፡
45በተገቢው ጊዜ ለቤተ ሰቦቹ ምግባቸውን ለመስጠት ጌታው በቤቱ ላይ ኀላፊነት የሰጠው ታማኝና አስተዋይ አገልጋይ ማን ነው?
46ጌታው ሲመጣ ያንን እያደረገ የሚያገኘው አገልጋይ የተባረከ ነው፡፡
47እውነት እላችኋለሁ የምላችሁ፣ ጌታው ባለው ነገር ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ይሾመዋል፡፡
48ይሁን እንጂ፣ አንድ ክፉ አገልጋይ በልቡ፣ ‹‹ጌታዬ ከመምጣት ዘግይቶአል ብሎ ቢያስብ፣
49አገልጋይ ጓደኞቹን መደብደብና ከሰካራሞች ጋር መብላት መጠጣት ቢጀምር
50የዚያ አገልጋይ ጌታ አገልጋዩ ባልጠበቀው ቀንና በማያውቀው ሰዓት ይመጣበታል፡፡
51ጌታው ለሁለት ይሰነጥቀዋል፤ ዕጣ ፈንታውን ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፣ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።