መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 23

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያም ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤
2"የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡
3ስለዚህ የሚያዝዙአችሁን ሁሉ አድርጉ፤ አክብሩትም፡፡ እነርሱ የሚያደርጉትን ግን አታደርጉ፤ ምክንያቱም እነርሱ ራሳቸው የሚናገሩትን አያደርጉትም፡፡
4ለመሸከም የሚያስቸግር ከባድ ሸክም አንሥተው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ግን መሸከም ቀርቶ በጣታቸው ሊያነሡት እንኳ አይፈልጉም፡፡
5ሥራቸውን ሁሉ የሚያደርጉት በሰዎች ለመታየት ነው፤ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ፡፡
6ግብዣ ላይ የከበሬታ ቦታዎችንና በምኵራብ ውስጥ የተለየ መቀመጫ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤
7በገበያ ቦታ ሰዎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸውና፣ 'መምህር ሆይ› በማለት እንዲጠሩአቸው ይፈልጋሉ፡፡
8እናንተ ግን ያላችሁ አንድ መምህር ብቻ ስለሆነና ሁላችሁም ወንድማማች ስለሆናችሁ ‹መምህር› ተብላችሁ አትጠሩ፡፡
9በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ፤ ምክንያቱም በሰማይ የሚኖር አንድ አባት ብቻ አላችሁ፡፡
10‹ሊቅም› ተብላችሁ አትጠሩ፤ ምክንያቱም ያላችሁ አንድ ሊቅ ብቻ ነው፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡
11ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነው አገልጋያችሁ ይሁን፡፡
12ራሱን ከፍ የሚያደርግ ዝቅ ይላል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል፡፡
13እናንተ፣ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ! በሰዎች ፊት መንግሥተ ሰማይን ትዘጋላችሁ፡፡ እናንተ ራሳችሁ አትገቡበትም፤ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ፡፡
14እናንተ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ለታይታ ረጅም ጸሎታችሁን በማድረግ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ! ስለዚህ የበለጠውን ፍርድ ትቀበላላችሁ፡፡ እናንተ ግብዞች የአይሁድ ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ!
15አንድን ሰው ተከታያችሁ ለማድረግ በባሕርና በምድር ትሄዳላችሁ፤ ተከታያችሁ ካደረጋችሁት በኋላ፣ ከእናንተ እጥፍ የሚከፋ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ፡፡
16እናንተ ዐይነ ስውራን መሪዎች ወዮላችሁ፤ አንድ ሰው 'በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም ማለት አይደለም፤ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን፣ በመሐላው ይጠመዳል' ትላላችሁ፡፡
17እናንተ የታወራችሁ ሞኞች፣ ለመሆኑ የትኛው ይበልጣል ወርቁ ወይስ ወርቁን የሚቀድሰው ቤተ መቅደሱ?
18አንድ ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም ማለት አይደለም፤ መሠዊያው ላይ ባለው ስጦታ ቢምል ግን በመሐላው ይጠመዳል ትላላችሁ፡፡
19እናንተ ዕውሮች፤ ለመሆኑ የትኛው ይበልጣል ስጦታው ወይስ ስጦታውን የሚቀድሰው መሠዊያ?
20ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል በመሠዊያውና እርሱ ላይ ባሉ ነገሮች ሁሉ ይምላል፡፡
21በቤተ መቅደሱ የሚምል በቤተ መቅደስና እርሱ ውስጥ በሚኖረው ይምላል፡፡
22በሰማይ የሚምል በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል፡፡
23እናንተ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ፣ ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት ብታወጡም፣ የሕጉን ዋና ዋና ነገሮች ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና እምነትን ሥራ ላይ አታውሉም፡፡ ሌላውን ችላ ሳትሉ እነዚህን መፈጸም ነበረባችሁ፡፡
24እናንተ ዐይነ ስውራን መሪዎች፣ ትንኝን አውጥታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!
25እናንተ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! የጽዋውንና የሳሕኑን ውጫዊ ክፍል ታጠራላችህ፤ ውስጡ ግን ቅሚያና ስስት ሞልቶበታል፡፡
26አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ ውጫዊ አካሉም ንጹሕ እንዲሆን በመጀመሪያ የጽዋውንና የሳሕኑን ውስጥ አጽዳ፡፡
27እናንተ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከውጭ ሲያዩት እንደሚያምር፣ ውስጡ ግን የሞቱ ሰዎች አጥንትና ርኵሰት እንደ ሞላበት መቃብር ናችሁ፡፡
28በተመሳሳይ መንገድ እናንተም ከውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ርኲሰት ሞልቶበታል፡፡
29እናንተ ግብዞች የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፣ የጻድቃንን መቃብር ስለምታስጌጡ፣
30በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር ትላላችሁ፡፡
31ስለሆነም የነቢያት ገዳይ ልጆች መሆናችሁን እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ፡፡
32እናንተ ራሳችሁም አባቶቻችሁ የጀመሩትን ኃጢአት ትፈጽማላችሁ፡፡
33እናንተ እባቦች፣ እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?
34ስለዚህ ነቢያትን፣ አስተዋይ ሰዎችንና የአይሁድ ሕግ መምህራንን ወደ እናንተ እልካለሁ፡፡ አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፣ ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹን በምኵራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፣ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፡፡
35ከጻድቁ ከአቤል አንሥቶ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካካል እስከ ገደላችሁት የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ደም ድረስ፣ በምድር ላይ በፈሰሰው ጻድቃን ደም ሁሉ ትጠየቃላችሁ፡፡
36እውነት እላችኋለሁ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይሆናሉ፡፡
37ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ ወደ አንቺ የተላኩትን በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን መሰብሰበ ብዙ ጊዜ ፈልጌ ነበር፤ እናንተ ግን አልፈለጋችሁም!
38ስለሆነም ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል፡፡
39'በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው' እስክትሉ ድረስ ከአሁን ጀምሮ አታዩኝም እላችኋለሁ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።