1ኢየሱስም ደግሞ እንዲህ በማለት በምሳሌ መለሰላቸው፤
2"መንግሥተ ሰማይ ለልጁ የሰርግ ድግስ የደገሰ ንጉሥን ትመስላለች፡፡
3ወደ ሰርጉ እንዲመጡ ወደ ጋበዛቸው ሰዎች አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን መምጣት አልፈለጉም፡፡
4እንደ ገና ንጉሡ ሌሎች አገልጋዮችን እንዲህ በማለት ላከ፤ "እነሆ፣ እራት አዘጋጅቻለሁ፤ በሬዎቼንና የሰቡ ወይፈኖቼን አርጃለሁ፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአልና ወደ ሰርግ ግብዣው ኑ በሏቸው፡፡' "
5ሰዎቹ ግን ግብዣውን ከልብ አልተቀበሉትም፡፡ አንዳንዶቹ ወደ እርሻዎቻቸው፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሥራ ቦታቸው ሄዱ፡፡
6አንዳንዶቹ የንጉሡን አገልጋዮች ደበደቡአቸው፤ አዋረዱአቸው፤ ገደሉአቸው፡፡
7ንጉሡ ግን ተቈጣ፤ ወታደሮቹን ላከ፤ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ፡፡
8ከዚያም ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፤ 'ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎች ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም፡፡
9ስለዚህ ወደ ዐውራ መንገድ ማቋረጫ ሄዳችሁ የምታገኙአቸውን ያህል ሰዎች ወደ ሰርጉ ግብዣ ጥሩ፡፡
10ሰዎቹም ወደ ዐውራው መንገድ ሄደው መልካምም ሆኑ መጥፎዎች ያገኙአቸውን ሁሉ አንድ ላይ ሰበሰቡ፡፡ ስለዚህ የግብዣው አዳራሽ በተጋባዦች ተሞላ፡፡
11ንጉሡ ተጋባዦቹን ለማየት ሲመጣ ግን፣ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፡፡
12ንጉሡ እንዲህ አለው፤ ‹ወዳጄ፣' የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?› ሰውየውም ዝም አለ፡፡
13ከዚያም ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አላቸው፤ እጅና እግሩን አስራችሁ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፡፡'
14የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡"
15ከዚያም ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስን እንዴት በንግግሩ ማጥመድ እንደሚችሉ ዕቅድ አወጡ፡፡
16ከዚያም ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ደቀ መዛሙርታቸውን ወደ እርሱ ላኩ፡፡ ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፤ "መምህር ሆይ፣ አንተ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ የምታስተምር እውነተኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውን በመፍራት ዐሳብህን አትለውጥም፤ በሰዎች መካከል አድልዎ አታደርግም፡፡
17እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለቄሳር ግብር መስጠት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?"
18ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ "እናንት ግብዞች የምትፈትኑኝ ለምንድን ነው?
19እስቲ የግብሩን ገንዘብ አሳዩኝ" አላቸው፡፡ እነርሱም ዲናሩን አመጡለት፡፡
20ኢየሱስም፣ "ይህ የማን መልክና ስም ነው?›› አላቸው፡፡
21እነርሱም፣ "የቄሣር፣" አሉት፡፡ ከዚያም ኢየሱስ፣ "እንግዲያስ የቄሣር የሆነውን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔር የሆነውን ለእግዚአብሔር ስጡ" አላቸው፡፡
22ያንን ሲሰሙ ተገረሙ፡፡ ትተውትም ሄዱ፡፡
23በዚያው ቀን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ጥቂት ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጡ፡፡
24"መምህር ሆይ፣ ‹አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሞተ ሚስቱን ወንድሙ እንዲያገባና ለወንድሙ ልጅ እንዲወልድለት ሙሴ ተናግሮአል›
25ሰባት ወንድማማች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፡፡ ሚስቱ የወንድምየው ሆነች፡፡
26ሁለተኛውና ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ ያንኑ አደረጉ፡፡
27ከሁሉም በኋላ ደግሞ ሴትየዋ ሞተች፡፡
28እንግዲህ ሰባቱም ወንድማማች አግብተዋት ነበርና በትንሣኤ ቀን የማንኛው ሚስት ልትሆን ነው?" በማለት ጠየቁት፡፡
29ኢየሱስ ግን እንዲህ በማለት መለሰላቸው፤ "መጻሕፍትንም ሆነ የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታወቁ ተሳስታችኋል፡፡
30ምክንያቱም በትንሣኤ ቀን እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ፣ አያገቡም፣ ደግሞም አይጋቡም፡፡
31ትንሣኤ ሙታንን በተመለከተ፣ እግዚአብሔር
32"እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ" በማለት ለእናንተ የተናገረውን አላነበባችሁምን? እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ፣ የሙታን አምላክ አይደለም፡፡"
33ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ በትምህርቱ ተገረሙ፡፡
34ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ፈሪሳውያን ሲሰሙ፣ በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡
35ከእነርሱ መካከል ሕግ ዐዋቂ የሆነ አንዱ እርሱን ለመፈተን፣
36"መምህር ሆይ፣ ከሕጉ ሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው" ብሎ ጠየቀው፡፡
37ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ "እግዚአብሔር አምላክህን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ዐሳብህ ውደድ፡፡"
38ከሁሉም የሚበልጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው፡፡
39ሁለተኛውም ትእዛዝ ያንኑ ይመስላል፤ 'ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡፡'
40ሕግና ነቢያት ሁሉ የትመሠረቱት በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ ነው፡፡
41ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰብስበው እያለ ኢየሱስ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡
42"ስለ ክርስቶስ ምን ታስባላችሁ? ለመሆኑ የማን ልጅ ነው?" አላቸው፡፡ "የዳዊት ልጅ ነው" አሉት፡፡
43ኢየሱስም፣ "ታዲያ፣ ዳዊት፣ በመንፈስ፣
44ጌታ ጌታዬን ‹ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ' በማለት እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል?
45ዳዊት ክርስቶስን 'ጌታ' በማለት ከጠራው እንዴት የዳዊት ልጅ ሊሆን ይችላል?"
46ማንም አንዲት ቃል ሊመልስለት አልቻለም፤ ከዚያ ቀን ጀምሮ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ አልነበረም፡፡