1ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደቀረቡ፣ በደብረ ዘይት ወዳለው ወደ ቤተ ፋጌ መጡ፤
2ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ “ወደሚቀጥለው መንደር ሂዱ፤ አህያም ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ። ፈትታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው፤
3ማንም ስለዚያ አንዳች ቢናገራችሁ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ፈጥኖ ይሰዳቸዋል።”
4-5ይህ የሆነው፣ “እነሆ፣ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያና በውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሯት” ተብሎ በነቢዩ የተተነበየው ይፈጸም ዘንድ ነው።
6ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ልክ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።
7አህያይቱንና ውርንጫዋን አመጡ፤ ልብሳቸውንም አደረጉባቸውና ኢየሱስ ተቀመጠባቸው።
8ከሕዝቡ አብዛኞቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎችም የዘንባባ ዝንጣፊ እየቈረጡ በመንገድ ላይ አደረጉ።
9ከኢየሱስ ፊት ይሄዱ የነበሩትና የተከተሉትም ሕዝብ፣ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ እርሱ የተባረከ ነው። ሆሣዕና በአርያም ይሁን!” በማለት ጮኹ።
10ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ከተማይቱ በሞላ ታወከችና፣ “ይህ ማን ነው?” አለች።
11ሕዝቡ፣ “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የሆነው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” ብለው መለሱ።
12ከዚያም ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ። በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና ወንበሮች ገለበጠ።
13እንዲህም አላቸው፤ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል። እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት።"
14ከዚያም ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው።
15ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን እርሱ ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች ባዩና በቤተ መቅደስ ልጆች፣ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” በማለት ሲጮኹ በሰሙ ጊዜ፣ ተቈጡ።
16“ሕዝቡ የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት። ኢየሱስ፣ “አዎ! ነገር ግን ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው።
17ከዚያም ኢየሱስ ትቷቸው ከከተማው ወጣና ወደ ቢታንያ ሄዶ በዚያ ዐደረ።
18ኢየሱስ ጠዋት ወደ ከተማው እንደተመለሰ፣ ተራበ።
19በመንገድ ዳር አንዲት የበለስስ ተክል አየና ወደ እርሷ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። “ሁለተኛ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስ ተክሊቱም ወዲያውኑ ደረቀች።
20ደቀ መዛሙርቱ ባዩአት ጊዜ ተደንቀው፣ “የበለስ ተክሊቱ እንዴት ወዲያውኑ ደረቀች?” አሉ።
21ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፤ "እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ፣ በዚች የበለስ ተክል የሆነባትን ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ኮረብታ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት እንኳ ይሆናል።
22አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”
23ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው፣ “በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉ።
24ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ደግሞ አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። ያንን ከነገራችሁኝ እኔ ደግሞ በማን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።
25የዮሐንስ ጥምቀት ከየት መጣ ከሰማይ ነውን ወይስ ከሰዎች?” እርስ በርሳቸው እንዲህ በማለት ተነጋገሩ፤ “ከሰማይ ነው ብንለው፣ ‘ለምን አታምኑትም?’ ይለናል።
26ነገር ግን ‘ከሰው ነው ብንል፣ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ስለሚያዩት ሕዝቡን እንፈራለን።”
27ከዚያም መልሰው ኢየሱስን፣ “አናውቅም” አሉት። እርሱ ደግሞ፣ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
28ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፣ ወደ መጀመሪያው ሄዶ፣ ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ አትክልት ስፍራ ሄደህ ሥራ’ አለው።
29ልጁ መልሶ፣ ‘አልሄድም’ አለ፤ በኋላ ግን ዐሳቡን ለውጦ ሄደ።
30ሰውዬውም ወደ ሁለተኛው ልጅ ሄዶ ይህንኑ ነገረው። ይህኛው ልጅ መልሶ፣ ‘እሄዳለሁ፣ አባዬ’ አለ። ነገር ግን አልሄደም።
31ከሁለቱ ልጆች የአባቱን ትእዛዝ የፈጸመው የትኛው ነው? እነርሱ፣ "የመጀመሪያው” አሉ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ቀድመዋችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ።
32ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበርና፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። እናንተም ይህ ሲሆን አይታችሁ ታምኑት ዘንድ በኋላ እንኳ ንሰሐ አልገባችሁም።
33ሌላም ምሳሌ ስሙ። ሰፊ መሬት ያለው አንድ ሰው ነበር። የወይን አትክልት ተከለ፤ ዐጥር አጠረለት፤ የወይን መጥመቂያ ማሰለት፤ መጠበቂያ ማማ ሠራለት፤ ለወይን ገበሬዎችም አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
34የወይን ፍሬ የሚሰበሰብበት ጊዜ እንደ ደረሰ፣ ፍሬውን እንዲቀበሉ ጥቂት አገልጋዮችን ላከ።
35የወይኑ ገበሬዎች ግን አገልጋዮቹን ያዙ፤ አንዱን ደበደቡት፣ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውንም በድንጋይ ወገሩት።
36ባለቤቱ እንደ ገና ከፊተኞቹ የበዙ ሌሎች አገልጋዮችን ላከ፤ ነገር ግን የወይን ገበሬዎቹ ያንኑ አደረጉባቸው።
37ከዚያ በኋላ ባለቤቱ፣ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት የገዛ ልጁን ላከ።
38የወይን ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ 'ይህ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ።
39ስለዚህ ያዙትና ከወይኑ አትክልት ስፍራ ወደ ውጭ ጣሉት፤ ገደሉትም።
40እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት በሚመጣበት ጊዜ እነዚያን የወይን ገበሬዎች ምን ያደርጋቸዋል?”
41ሕዝቡ እንዲህ አሉት፤ “እነዚያን ክፉ ሰዎች እጅግ በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ያጠፋቸዋል፤ ከዚያም የወይኑን አትክልት ስፍራ ወይኑ በሚያፈራበት ጊዜ ገንዘቡን ለሚከፍሉ ለሌሎች የወይን ገበሬዎች ያከራየዋል።”
42ኢየሱስ እነርሱን፣ “ 'ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነ። ይህ ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው ተብሎ የተጻፈውን ፈጽሞ አላነበባችሁም?’
43ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰድና ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች።
44በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰባበራል። ድንጋዩ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል።”
45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ የተናገረው ስለ እነርሱ እንደ ሆነ ተረዱ።
46ነገር ግን ሊይዙት በፈለጉ ጊዜ ሁሉ፣ ሰዎቹ እንደ ነቢይ ይቈጥሩት ስለ ነበር ሕዝቡን ፈሩ።