1መንግሥተ ሰማይ ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤትን ትመስላለች።
2በቀን አንዳንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከሠራተኞቹ ጋር ከተስማማ በኋላ፣ ወደ ወይኑ አትክልት ስፍራ ላካቸው።
3ደግሞም በሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎች ሠራተኞችን አየና፣
4'እናንተ ደግሞ ወደ ወይኑ አትክልት ስፍራ ሂዱ፤ የሚገባችሁንም እከፍላችኋለሁ' አላቸው። ስለዚህ እነርሱም ሊሠሩ ሄዱ።
5ደግሞ በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንደዚሁ አደረገ።
6አሁንም በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ገደማ ወጥቶ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አገኘ። እነርሱንም፣ 'ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ቆማችኋል?' አላቸው።
7'ማንም ስላልቀጠረን ነው' አሉት። 'እናንተም ደግሞ ወደ ወይኑ አትክልት ስፍራ ሂዱ' አላቸው።
8ቀኑ በመሸ ጊዜ፣ የወይኑ አትክልት ባለቤት ሥራ አስኪያጁን፣ 'ሠራተኞቹን ጥራ ከኋለኞቹ አንሥተህ እስከ ፊተኞቹ የሠሩበትን ገንዘብ ክፈላቸው' አለው።
9በዐሥራ አንደኛው ሰዓት የተቀጠሩት ሠራተኞች በመጡ ጊዜ፣ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ።
10ፊተኞቹ ሠራተኞች በመጡ ጊዜ፣ የበለጠ የሚቀበሉ መሰላቸው፤ ነገር ግን እነርሱም ደግም እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ።
11ገንዘባቸውን በተቀበሉ ጊዜ፣ በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ አጕረመረሙ።
12እንዲህም አሉ፤ 'እነዚህ በመጨረሻ የመጡ ሠራተኞች በሥራ ላይ አንድ ሰዓት ብቻ አሳልፈዋል፤ ነገር ግን አንተ የዕለቱን ሸክምና የሚለበልበውን ሙቀት ከተሸከምነው ከእኛ ጋር እኩል አድርገሃቸዋል።'
13ባለቤቱ ግን መልሶ ከእነርሱ አንዱን እንዲህ አለው፤ "ወዳጄ ሆይ፣ አልበደልኩህም። ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን?
14የሚገባህን ተቀብለህ መንገድህን ሂድ፤ ለእነዚህ በመጨረሻ ለተቀጠሩት ሠራተኞች ልክ እንደ አንተው ልሰጣቸው ደስ ይለኛል።
15በገዛ ንብረቴ የፈለግሁትን ማድረግ አይገባኝምን? ወይስ እኔ ደግ ስለ ሆንሁ ትመቀኛለህን?
16ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።"
17ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ ስለ ነበር፣ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰደ፤ በመንገድ ላይም እንዲህ አላቸው፦
18እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል። ሞትም ይፈርዱበታል፤
19እንዲዘብቱበት፣ እንዲገርፉት፣ እንዲሰቅሉትም ለአሕዛብ ይሰጡታል። ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ይነሣል።"
20በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋር ወደ ኢየሱስ መጣች፤ በፊቱ ተንበርክካም ከእርሱ አንድ ነገር ለመነች።
21ኢየሱስ፣ "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት። እርሷም፣ "በመንግሥትህ እነዚህ ሁለት ልጆቼ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱም በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ" አለችው።
22ኢየሱስ ግን መልሶ፣ "የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን?" አለ። እነርሱ፣ "እንችላለን" አሉት።
23ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ "በርግጥ ጽዋዬን ትጠጣላችሁ። በቀኜና በግራዬ መቀመጥን የምሰጥ ግን እኔ አይደለሁም፤ ነገር ግን በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ለእነርሱ ነው።"
24ሌሎቹ ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ፣ በሁለቱ ወንድማማች ላይ ተቈጡ።
25ነገር ግን ኢየሱስ ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፣ "የአሕዛብ አለቆች ሕዝባቸውን ጨቊነው ይገዛሉ፤ የበላዮቻቸውም ይሠለጥኑባቸዋል።
26በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መደረግ የለበትም። ይልቁንም፣ ከእናንተ መካከል ታላቅ ሊሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ይሁን፤
27ከእናንተም ፊተኛ ሊሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ይሁን።
28የሰው ልጅ ሊያገለግል፣ ሕይወቱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ እንጂ፣ እንዲያገለግሉት አልመጣም።"
29ከኢያሪኮ እንደ ወጡ፣ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከተሉት።
30እነሆ፣ ሁለት ዐይነ ስውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው ነበር፤ ኢየሱስ ሲያልፍ በሰሙ ጊዜ ጮኽ ብለው፣ "ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረን" አሉ።
31ሕዝቡ ግን ዝም እንዲሉ በመንገር ገሠጿቸው። ይሁን እንጂ፣ እነርሱ አብዝተው በመጮኽ፣ "ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ ማረን" አሉ።
32በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ቆም ብሎ ጠራቸውና፣ "ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?" አለ።
33እነርሱም፣ "ጌታ ሆይ፣ ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው" አሉት።
34ከዚያም ኢየሱስ ራርቶ፣ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ። እነርሱም ወዲያውኑ አይተው ተከተሉት።