መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንዲህም ሆነ፤ ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ገሊላን ትቶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ ጠረፍ መጣ፡፡
2ብዙ ሕዝብ ተከተሉት፤ እዚያም ፈወሳቸው፡፡
3ፈሪሳውያን እንዲህ በማለት ሊፈትኑት ወደ እርሱ መጡ፤ "በማንኛውም ምክንያት ሰው ሚስቱን ቢፈታ ሕጋዊ ነውን?"
4ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፣ "ከመጀመሪያው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸውና
5ደግሞም፣ 'በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ አንድ ሥጋም ይሆናሉ' የተባለውን አላነበባችሁምን?
6ስለዚህ እነርሱ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ እንጂ ሁለት አይደሉም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ላይ ያጣመረውን፣ ማንም አይለየው፡፡››
7እነርሱ፣ "ታዲያ የፍቺ የምስክር ወረቀት ሰጥተን ከዚያ በኋላ እንድናባርራት ሙሴ ለምን አዘዘን?" አሉት፡፡
8ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፣ "ከልባችሁ ድንዳኔ የተነሣ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ሙሴ ፈቀደላችሁ፤ ነገር ግን ከመጀመሪያው እንደዚያ አልነበረም፡፡
9እኔ እላችኋለሁ፣ ከዝሙት በቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ፣ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል፡፡"
10ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፣ "የባልና የሚስት ጉዳይ እንዲህ ከሆነ ማግባት ጥሩ አይደለም" አሉት፡፡
11ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ "እንዲቀበሉት የተፈቀደላቸው እንጂ፣ ሁሉም ሰው ይህን ትምህርት አይቀበለውም፡፡
12በተፈጥሮ ከእናታቸው ማኅፀን ስልብ ሆነው የተወለዱ አሉና፡፡ ሰዎች የሰለቧቸውም ይገኛሉ፡፡ ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉም ራሳቸውን ስልብ ያደረጉ አሉ፡፡ ይህን ትምህርት መቀበል የሚችል፣ ይቀበለው፡፡››
13በዚያን ጊዜ እጁን ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሰዎች ልጆችን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው፡፡
14ኢየሱስ ግን፣ "ልጆቹን ተዉአቸው፤ ወደ እኔም እንዲመጡ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ናትና" አለ፡፡
1515 እጁንም በልጆቹ ላይ ጫነባቸው፤ ከዚያም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፡፡
16እነሆ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ ‹‹መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ማድረግ አለብኝ?›› አለ፡፡
17ኢየሱስ፣ ‹‹ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም አንድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ወደ ሕይወት ለመግባት ብትፈልግ ትእዛዛትን ጠብቅ›› አለው፡፡
18ሰውዬው፣ ‹‹የትኞቹን ትእዛዛት? አለ፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለው፤ "አትግደል፤" "አታመንዝር" "አትስረቅ፤" "በሐሰት አትመስክር፤"
19"አባትህንና እናትህን አክብር፤" እንዲሁም፣ "ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡፡"
20ወጣቱ፣ "እነዚህን ነገሮች ሁሉ ፈጽሜአለሁ፣ ሌላስ ምን ያስፈልገኛል?" አለው፡፡
21ኢየሱስ እንዲህ አለው፤ "ፍጹም ለመሆን ብትፈልግ፣ ሂድና ያለህን ሽጠህ ለድኾችም ስጠው፤ በሰማይም ሀብት ይኖርሃል፡፡ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ፡፡››
22ነገር ግን ወጣቱ ኢየሱስ የተናገረውን በሰማ ጊዜ፣ ብዙ ንብረት ነበረውና ዐዝኖ ሄደ፡፡
23ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ "እውነት እላችኋለሁ፤ ለባለ ጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ከባድ ነው፡፡
24ደግሜ እላችኋለሁ፤ ለባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከመግባት፣ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፡፡"
25ደቀ መዛሙርቱ ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተደነቁና፣ "ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?" አሉ፡፡
26ኢየሱስ ወደ እነርሱ ተመልክቶ፣ "ይህ ለሰዎች የማይቻል ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል" አለ፡፡
27ከዚያም ጴጥሮስ መልሶ፣ "ተመልከት፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ ታዲያ ምን እናገኛለን?" አለ፡፡
28ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ "እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ እኔን የተከተላችሁኝ፣ በዐዲሱ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶችም ላይ ትፈርዳላችሁ፡፡
29ስለ ስሜ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን፣ ወይም ርስትን የተወ ሁሉ፣ መቶ እጥፍ ይቀበላል፣ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል፡፡
30ነገር ግን አሁን ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፤ ኋለኞች የሆኑ ብዙዎችም ፊተኞች ይሆናሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።