መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ሰዎች ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ እንደዚህም በማለት ጠየቁ፤
2‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው? የእርሱን ኮከብ በምሥራቅ አየን፣ ልንሰግድለትም መጥተናል፡፡››
3ንጉሡ ሄሮድስ ይህን ሲሰማ ተረበሸ፤ መላው ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር ታወከ፡፡
4ሄሮድስ የካህናቱን አለቆችና የሕዝቡን የሕግ መምህራን ሰብስቦ፣ ‹‹ክርስቶስ የሚወለደው የት ነው?›› በማለት ጠየቀ፡፡
5‹‹በቤተ ልሔም ይሁዳ›› አሉት፤ በነቢዩ የተጻፈው ይህ ነውና፡
6በይሁዳ ምድር የምትገኚ አንቺ ቤተ ልሔም፣ ከይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፣ ሕዝቡን እስራኤልን የሚጠብቅ ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልና፡፡
7ከዚያም በኋላ ሄሮድስ ኮከቡ በትክክል በምን ሰዓት ታይቶ እንደ ነበር ሊጠይቃቸው ጠቢባኑን በምስጢር ጠራቸው፡፡
8ወደ ቤተ ልሔምም ላካቸው፤ ‹‹ሂዱና ሕፃኑን በጥንቃቄ ፈልጉ፡፡ ስታገኙት እኔም ደግሞ እንድመጣና እንድሰግድለት ንገሩኝ›› አላቸው፡፡
9ንጉሡ የተናገረውን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ በምሥራቅ አይተውት የነበረውም ኮከብ ሕፃኑ በነበረበት ላይ እስኪደርስና እስኪቆም ድረስ በፊታቸው ይሄድ ነበር፡፡
10ጠቢባኑ ኮከቡን ባዩት ጊዜ፣ እጅግ በጣም ተደሰቱ፡፡
11ወደ ቤት ገብተው ሕፃኑንም ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት፡፡ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው የወርቅ፣ የዕጣንና የከርቤ ስጦታ አቀረቡለት፡፡
12እግዚአብሔር ጠቢባኑን ወደ ሄሮድስ ተመልሰው እንዳይሄዱ በሕልም አስጠነቀቃቸው፤ ስለዚህም በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡
13ጠበባኑ ከሄዱ በኋላ፣ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለትና፣ "ተነሥ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፡፡ እኔ እስክነግርም ድረስ እዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና" አለው፡፡
14በዚያ ሌሊት ዮሴፍ ተነሣ፣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ፡፡
15ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ እዚያው ቈየ፡፡ በዚህም ጌታ፣ ‹‹ልጄን ከግብፅ ጠራሁት›› ብሎ በነቢዩ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡
16ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑ እንደ ተሣለቁበት ሲገነዘብ በጣም ተናደደ፡፡ በቤተ ልሔምና በዚያ አውራጃ የነበሩ ወንድ ሕፃናትን፣ እንደዚሁም ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን ሁሉ ከጠቢባኑ በትክክል በተረዳው ጊዜ መሠረት ልኮ አስፈጀ፡፡
17በዚያም በነቢዩ ኤርምያስ ተነግሮ የነበረው፡-
18‹‹ድምፅ በራማ ተሰማ፣ ልቅሶና መሪር ዋይታ፣ ራሔል ስለ ልጆቿ በማልቀስ፣ ለመጽናናትም እምቢ አለች፣ በሕይወት የተረፈ የለምና›› የሚለው ተፈጸመ፡፡
19ሄሮድስ ሲሞት፣ እነሆ፣ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለትና፣
20‹‹ሕፃኑን ሊገድሉት የፈለጉት ስለ ሞቱ፣ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ›› አለው፡፡
21ዮሴፍ ተነሣ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል አገር ሄደ፡፡
22አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ስፍራ ተተክቶ ይሁዳን ይገዛ እንደ ነበረ ሲሰማ ግን ወደዚያ ለመሄድ ፈራ፡፡ እግዚአብሔር በሕልም ካስጠነቀቀው በኋላ፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤
23ናዝሬት በምትባል ከተማ ውስጥም ኖረ፡፡ ይህ በነቢዩ ተነግሮ የነበረውን፣ ናዝራዊ ተብሎ ይጠራል የሚለውን እንዲፈጸም አደረገ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።