1በዚያው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ "በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?" አሉ
2ኢየሱስ አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው፤
3እንዲህም አለ፡- "እውነት እላችኋለሁ፤ ንስሐ ካልገባችሁና እንደ ልጆች ካልሆናችሁ በምንም መንገድ ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም፡፡
4ስለዚህ እንደዚህ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው ሁሉ፣ እንዲሁ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ይበልጣል፡፡
5እንደዚህ ያለውን ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፡፡
6ነገር ግን በእኔ ከሚያምነው ከእነዚህ ልጆች አንዱን ኀጢአት እንዲሠራ የሚያደርግ ማንም፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቁ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል፡፡
7የመሰናክል ምክንያት በመሆኗ ለዓለም ወዮላት! መሰናክል መምጣቱ ግድ ነው፤ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣ ሰው ወዮለት!
8እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ፣ ቈርጠህ ከአንተ ጣለው፡፡ ሁለት እጆች ወይም እግሮች ኖረውህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል የአካል ጉዳተኛ ወይም አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል፡፡
9ዐይንህ እንድትሰናከል ቢያደርግህ፣ አውጥተህ ከአንተ ጣለው፡፡ ሁለት ዐይኖች ኖረውህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻላል፡፡
10ከእነዚህ ከታናናሾች ማንኛውንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፡፡ በሰማይ ያሉ መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁልጊዜ ያያሉና፡፡ 11 (2) ብዙ ምንጮች፣ አንዳንድ የጥንት የሆኑ ቊ. 11ን ያስገባሉ፡፡
12ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት፣ ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፣ ዘጠና ዘጠኙን በኮረብታው ጥግ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ አይሄድምን?
13በሚያገኘውም ጊዜ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል፡፡
14በተመሳሳይ መንገድ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ የሰማዩ አባታችሁ ፈቃድ አይደለም፡፡
15ወንድምህ ቢበድልህ፣ ሂድና አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁም ጥፋቱን አሳየው፡፡ ቢሰማህ፣ ወንድምህን የራስህ ታደርገዋለህ፡፡
16ባይሰማህ ግን፣ ቃል ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ይጸናልና፣ ከአንተ ጋር አንድ ወይም ሁለት ተጨማሪ ወንድሞችን ይዘህ ሂድ፡፡
17እነርሱንም አልሰማም ቢል፣ ጉዳዩን ለቤተ ክርስቲያን ንገር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ አልሰማም ቢል፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ቊጠረው፡፡
18እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም ነገር ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡
19በተጨማሪም እላችኋለሁ፣ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ስለሚለምኑት ስለ ማንኛውም ነገር ቢስማሙ፣ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላቸዋል፡፡
20ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት ቦታ እዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና፡፡
21ከዚያም ጴጥሮስ መጥቶ ኢየሱስን፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?›› አለው፡፡
22ኢየሱስም፣ ‹‹ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ፣ ሰባት ጊዜ አልልህም›› አለው፡፡
23ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከአገልጋዮቹ ጋር ሒሳብ ሊተሳሰብ የፈለገ ንጉሥን ትመስላለች፡፡
24መተሳሰቡን እንደ ጀመረ፣ የዐሥር ሺህ መክሊት ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ወደ እርሱ አመጡ፡፡
25ነገር ግን የሚከፍልበት መንገድ ስላልነበረው፣ ጌታው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ያለውም ሁሉ ተሸጦ ክፍያው እንዲፈጸም አዘዘው፡፡
26ስለዚህ አገልጋዩ ወድቆ በፊቱ ተንበረከከ እንዲህም አለ፤ ‹ጌታዬ ሆይ፣ ታገሠኝ፣ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፡፡›
27ስለዚህ የዚያ አገልጋይ ጌታ ስለ ራራለት፣ ተወው፤ ዕዳውንም ሠረዘለት፡፡
28ነገር ግን ያ አገልጋይ ወጥቶ አብረውት ከሚሠሩት አገልጋዮች መቶ ዲናር ያበደረውን አንዱን አገልጋይ አግኝቶ ያዘው፤ ጕሮሮውን አነቀውና፣ ‹‹ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ›› አለው፡፡
29ነገር ግን የሥራ ባልደረባው፣ ‹‹ታገሠኝ፣ እከፍልሃለሁ›› በማለት ወድቆ ለመነው፡፡
30የመጀመሪያው አገልጋይ ግን አሻፈረኝ አለ፤ በዚህ ፈንታ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ በእስር ቤት ጣለው፡፡
31የሥራ ጓደኞቹ የሆኑት አገልጋዮች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ በጣም ተበሳጩ፤ መጥተውም ለጌታቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡
32ከዚያም የዚያ አገልጋይ ጌታ ጠራው፣ እንዲህም አለው፤ 'አንተ ክፉ አገልጋይ፣ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፡፡
33እኔ አንተን እንደማርሁህ፣ የሥራ ባልደረባህ የሆነውን አገልጋይ ልትምረው አይገባህም ነበርን?'
34ጌታው ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለሚያሠቃዩት አሳልፎ ሰጠው፡፡
35ስለዚህም ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልብ ይቅር ባይል የሰማዩ አባቴ እንዲሁ ያደርግበታል፡፡"