1ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ይዞ ብቻቸውን ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው፡፡
2በፊታቸውም መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ፡፡
3እነሆ፣ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡
4ጴጥሮስ መልሶ ኢየሱስን፣ "ጌታ ሆይ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ብትፈልግ እኔ እዚህ ሦስት ዳሶችን፡- አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እሠራለሁ" አለው፡፡
5እርሱ ገና እየተናገረ እያለ፣ እነሆ፣ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም፣ "በእርሱ እጅግ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ ነበረ፡፡
6ደቀ መዛሙርቱ ድምፁን በሰሙ ጊዜ ፈሩ፣ በግንባራቸውም ወደቁ፡፡
7ከዚያም ኢየሱስ መጥቶ ዳሰሳቸውና፣ ‹‹ተነሡ አትፍሩ›› አላቸው፡፡
8ከዚያም እነርሱ ቀና ብለው ተመለከቱ፣ ነገር ግን ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም፡፡
9ከተራራ ሲወርዱም ኢየሱስ፣ "የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ" ብሎ አዘዛቸው፡፡
10ደቀ መዛሙርቱ፣ "እንግዲያው የአይሁድ ሕግ መምህራን መጀመሪያ ኤልያስ መምጣት አለበት ለምን ይላሉ?" በማለት ጠየቁት፡፡
11ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፤ "ኤልያስ በርግጥ ይመጣል፣ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፡፡
12ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ አስቀድሞ መጥቷል፤ ነገር ግን አላወቁትም፡፡ በዚህ ፈንታ የፈለጉትን ነገር ሁሉ አደረጉበት፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የሰው ልጅ በእነርሱ እጅ መከራ ይቀበላል፡፡››
13በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነበረ ተረዱ፡፡
14ወደ ሕዝቡ በመጡ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ በፊቱ ተንበረከከ፤ እንዲህም አለው፤
15"ጌታ ሆይ፣ ልጄን ማረው፣ የሚጥል በሽታ ይዞት በኀይል ይሠቃያል፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ወይም በውሃ ውስጥ ይጥለዋልና፡፡
16ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን እነርሱ ሊፈውሱት አልቻሉም፡፡›
17ኢየሱስ መልሶ፣ "የማታምኑና ምግባረ ብልሹ ትውልድ፣ እስከ መቼ ድረስ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ አለብኝ? እስቲ ወደ እኔ አምጡት" አለ፡፡
18ኢየሱስ ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ፡፡
19ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ "እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?" አሉ፡፡
20ኢየሱስ፣ ‹‹በእምነታችሁ ማነስ ምክንያት፤ እውነት እላችኋለሁና፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት እንኳ ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነሥተህ ወደ ማዶ ሂድ ብትሉት ይሄዳል፡፡ ማድረግ የሚሳናችሁ ምንም ነገር አይኖርም፡፡
22በገሊላ እያሉ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ "የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤
23እነርሱም ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል" አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በጣም ዐዘኑ፡፡
24ወደ ቅፍርናሆም በመጡ ጊዜ ግማሽ ሰቅል ቀረጥ የሰበሰቡ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ መጥተው፣ "መምህራችሁ ግማሽ ሰቅሉን ቀረጥ አይከፍልምን?" አሉ፡፡
25እርሱ፣ "አዎ" አለ፡፡ ጴጥሮስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ግን ኢየሱስ መጀመሪያ እርሱን ተናገረው፤ "ስምዖን ሆይ፣ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥ ወይም ግብር የሚሰበስቡት ከማን ነው? ከዜጎቻቸው ወይስ ከውጭ አገር ሰዎች?" አለው፡፡
26ጴጥሮስ፣ "ከውጭ አገር ሰዎች" ባለ ጊዜ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለው፤ "እንግዲያስ ዜጎቹ ከክፍያ ነጻ ናቸው፡፡
27ነገር ግን ቀረጥ ሰብሳቢዎቹን ኃጢአት እንዲሠሩ እንዳናደርጋቸው ወደ ባሕር ሄደህ መንጠቆ ጣል፤ በመጀመሪያ የምታጠምደውን ዐሣ አፍ ስትከፍት አንድ ሰቅል ታገኛለህ፤ ያንን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ክፈል፡፡››