መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የማቴዎስ 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያም አንዳንድ ፈሪሳውያንና የአይሁድ የሕግ መምህራን ከኢየሩሳሌም ኢየሱስን ለማነጋገር መጥተው እንዲህ አሉ፤
2"ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ የሚጥሱት ለምንድነው? ምግብ ከመብላታቸው በፊት እንደ ወጉ እጃቸውን አይታጠቡምና።"
3ኢየሱስም መለሰና፣ "እናንተስ ስለ ወጋችሁ ስትሉ ለምን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትተላለፋላችሁ?" አላቸው፡፡
4እግዚአብሔር፣ ‹አባትህንና እናትህን አክብር፣› ‹ስለ አባቱ ወይም ስለ እናቱ ክፉ የሚናገር በርግጥ ይሞታል› ብሏልና፡፡
5እናንተ ግን፣ "አባቱን ወይም እናቱን፣ 'ከእኔ የተቀበላችሁት ማንኛውም እርዳታ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው ትላላችሁ፡፡'
6ያ ሰው አባቱን ማክበር አያስፈልገውም። ስለ ወጋችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፡፡
7እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣
8'ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
9የሰዎችን ትእዛዝ እንደ ሕግ በመቊጠር የራሳቸውን ትምህርት ስለሚያስተምሩ፣ እኔን በከንቱ ያመልኩኛል›› ብሎ ትንቢት በመናገሩ መልካም አድርጓል።
10ከዚያ ሕዝቡን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ "አድምጡ አስተውሉም፡-
11ወደ አፍ የሚገባ ሰውን ምንም አያረክስም፡፡ ይልቁንም ከአፍ የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ነው" አላቸው፡፡
12ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ኢየሱስን፣ ‹‹ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሲሰሙ እንደ ተሰናከሉ ዐወቀሃል?›› አሉት፡፡
13ኢየሱስም መለሰና፣ ‹‹አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል፤
14እነርሱን ተዉአቸው፤ ዐይነ ስውር መሪዎች ናቸው፡፡ አንድ ዐይነ ስውር ሌላውን ዐይነ ስውር ቢመራው ሁለቱም ተያይዘው ጕድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡››
15ጴጥሮስ መልሶ ኢየሱስን፣ ‹‹ይህን ምሳሌ አብራራልን›› አለው፡፡
16ኢየሱስ፣ ‹‹እናንተ ደግሞ አሁንም አታስተውሉምን?
17ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚሄድና ከዚያም ዐይነ ምድር ሆኖ ወደ ውጭ እንደሚጣል አታስተውሉምን?
18ዳሩ ግን ከአፍ የሚወጣ ከልብ ይወጣል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሰውን ያረክሳሉ፡፡
19ከልብ ክፉ ዐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ምንዝርና፣ ዝሙት፣ ስርቆት፣ የሐሰት ምስክርነትና ስድብ ይወጣሉ፤
20ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባልታጠበ እጅ መብላት ሰውን አያረክስም፡፡"
21ቀጥሎም ኢየሱስ ከዚያ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች አካባቢ ሄደ፡፡
22እነሆም፣ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አካባቢ ወጣችና ጮኽ ብላ እንዲህ አለች፣ ‹‹የዳዊት ልጅ፣ ጌታ ሆይ፣ ማረኝ፡፡ ልጄ በጋኔን ተይዛ በጣም እየተሠቃየች ነው፡፡››
23ኢየሱስ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው፣ ‹‹ይህች ሴት ትጮኽብናለችና ሸኛት›› ብለው ለመኑት፡፡
24ነገር ግን ኢየሱስ መልሶ፣ ‹‹እንደ በግ ወደ ጠፉት የእስራኤል ቤት ሰዎች ካልሆነ በቀር ወደ ማንም አልተላክሁም›› አለ፡፡
25ነገር ግን ሴቲቱ "ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ" በማለት መጥታ በፊቱ ሰገደች፡፡
26ኢየሱስ መልሶ፣ "የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ትክክል አይደለም" አለ፡፡
27ሴቲቱ፣ "አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ ከሚወድቀው የተወሰነውን ትርፍራፊ ይበላሉ" አለች፡፡
28ከዚያም ኢየሱስ መልሶ፣ "አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው፤ ልክ እንደ ተመኘሽው ይሁንልሽ" አላት፡፡ ልጇም በዚያች ሰዓት ተፈወሰች፡፡
29ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ወደ ገሊላ ባሕር አቅራቢያ ሄደ፡፡ ከዚያም ወደ አንድ ኮረብታ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ፡፡
30ብዙ ሕዝብም ወደ እርሱ መጡ፤ አንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ዲዳዎችንና ጕንድሾችን፣ እንዲሁም ሌሎች ታመው የነበሩ ብዙዎችን ይዘው መጡ፡፡ በኢየሱስ እግር አጠገብም አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው፡፡
31ስለዚህ ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጕንድሾች ሲፈወሱ፣ አንካሶች ሲራመዱ፣ ዐይነ ስውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፡፡ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ፡፡
32ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ "ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ቈይተዋል፣ የሚበሉትም የላቸውም፡፡ በመንገድ ላይ ዝለው እንዳይወድቁ ሳይበሉ ዝም ብዬ አላሰናብታቸውም" አለ፡፡
33ደቀ መዛሙርቱ፣ "በዚህ በረሓ ይህን የሚያህል ብዙ ሕዝብ የሚያጠግብ እንጀራ ከየት እናገኛለን?" አሉት፡፡
34ኢየሱስ፣ "ስንት እንጀራ አላችሁ?" አላቸው፡፡ "ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዐሣ አለ" አሉት፡፡
35ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፡፡
36ኢየሱስ ሰባቱን እንጀራና ዐሣዎቹን ይዞ ካመሰገነ በኋላ እንጀራውን ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጧቸው፡፡
37ሕዝቡ ሁሉ በሉና ጠገቡ፡፡ ትርፍራፊውንም ሰበሰቡ፤ ትርፍራፊውም ሰባት ቅርጫት ሙሉ ነበር፡፡
38የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ፡፡
39ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናበተና በጀልባም ገብቶ መጌዶን ወደ ተባለ ክፍለ አገር ሄደ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።