1በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር ዳርቻ ተቀመጠ።
2በጣም ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰበሰቡ፣ ስለዚህ ጀልባ ውስጥ ገብቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ቆመው ነበር።
3ከዚያም ኢየሱስ በምሳሌ ብዙ ነገር ነገራቸው። እንዲህም አለ፤ "ዘሪ ለመዘራት ወጣ።
4ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር በመንገድ አጠገብ ወድቆ፣ ወፎች መጥተው በሉት።
5ሌላውም ዘር በቂ አፈር በሌለበት በዐለታማ መሬት ላይ ወደቀ። አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ።
6ፀሐይ ሲወጣ ግን፣ሥር ስላልነበረው ጠውልጎ ደረቀ።
7ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፣ እሾኹም አድጎ አነቀው።
8ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ ፍሬ አፈራ፤ አንዳንዱ መቶ፣ አንዳንዱ ሥልሳ፣ አንዳንዱም ሠላሳ ፍሬ አፈራ።
9ጆሮ ያለው ይሰማ።"
10ደቀ መዛሙርቱም መጡና ኢየሱስን፣ “ለምንድን ነው ለሕዝቡ በምሳሌ የምትናገረው?" አሉት።
11ኢየሱስም መልሶ፣ "ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም" አላቸው።
12ምክንያቱም ላለው ሁሉ የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለትማል። የሌለው ግን ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
13ስለዚህ ለእነርሱ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ቢያዩ እንኳ እያዩ አይደለም፣ ቢሰሙም እየሰሙ አይደለም፣ ወይም አያስተውሉም።
14በእነርሱ ላይ እንዲህ የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጸመ ፦ መስማትን ትሰማላችሁ፣ ነገር ግን በምንም መንገድ አታስተውሉም፣ ማየትን ታያላችሁ፣ ግን ምንም አትገነዘቡትም።
15በዐይናቸውም እንዳይመለከቱ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ጆሯቸው ለመስማት ተደፍኗል፣ ዐይናቸውም ተጨፍኗል። እንዳይመለሱና እኔም እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል።
16የእናንተ ዐይኖች ግን ስለሚያዩ፣ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው።
17እውነት እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ለማየት ተመኝተው አላዩም፤ የምትሰሙትን ለመስማት ተመኝተው አልሰሙም።
18እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ።
19ማንም የመንግሥትን ቃል ሰምቶ ባያስተውል፣ ክፉው ይመጣል በልቡም የተዘራውን ይነጥቃል። ይህም በመንገድ ዳር የተዘራውን ይመስላል።
20በዐለት ላይ የተዘራው ፣ቃሉን የሚሰማና ወዲያውኑ በደሰታ የሚቀበለው ነው፤
21ሆኖም በራሱ ሥር ስለሌለው፣ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሚነሣበት ጊዜ፣ ወዲያውኑ ይሰናከላል።
22በእሾኽ ተክሎች መካከል የተዘራው፣ ቃሉን የሚሰማ ሆኖ የዓለም ዐሳብ፣ የብልጥግናም አሳሳችነት ቃሉን ያንቁታል፣ ፍሬ ቢስም ይሆናል።
23በመልካም መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን የሚሰማና የሚረዳ ነው፤ በርግጥ የሚያድገውና ፍሬ የሚሰጠውም ይህኛው ነው፤ አንዱ መቶ፣ አንዱም ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሣ እጥፍ ያፈራል።
24ኢየሱስ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህ አለ፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ላይ መልካም ዘር የዘራ ሰው ትመስላለች።
25ሰዎቹ በተኙ ጊዜ ግን፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ።
26ቅጠሉም በለመለመና ፍሬ ማፍራት በጀመረ ጊዜ፣ እንክርዳዱ ደግሞ አለ።
27የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮች መጥተው፣ "ጌታ ሆይ፣ በዕርሻው ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳድ የበቀለው እንዴት ነው?"አሉት።
28እርሱም፣ “ጠላት ይህን አደረገ" አላቸው። አገልጋዮቹም መልሰው፣"ስለዚህ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?" አሉት።
29የዕርሻውም ባለቤት፣ 'አይሆንም፣ እንክርዳዱን በምትነቅሉበት ጊዜ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉት ትችላላችሁ 'አላቸው።
30እስከ መከር ድረስ አብረው ይደጉ። በመከሩ ጊዜ ለኣጫጆቹ፣ "መጀመሪያ እንክርዳዱን ነቅላችሁ እንዲቃጠል አንድ ላይ ሰብስቡ። ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡት እላቸዋለሁ" አላቸው።
31ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ ነገራቸው። እንዲህም አለ፤ “መንግሥተ ሰማይ ሰው ወስዶ በዕርሻው ላይ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች።
32በርግጥ ይህች ዘር ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ታንሳለች። በምታድግበት ጊዜ ግን የሰማይ ወፎች በቅርንጫፎቿ እስኪሰፍሩባት ድረስ፣ ከሌሎች ዛፎች ትበልጣለች፡፡
33ከዚያም ኢየሱስ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ኩፍ እስኪል ድረስ ከሦስት እጅ ዱቄት ጋር የደባለቀችውን እርሾ ትመስላለች።”
34ኢየሱስም ለሕዝቡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፣ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም።
35ይህም ፦ "አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፣ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ የተሰወረውን እገልጣለሁ" ተብሎ በነቢዩ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።
36ኢየሱስ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጥተው "በዕርሻው የነበረውን የእንክርዳዱን ምሳሌ አስረዳን" አሉት።
37ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አለ፤ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው።
38ዕርሻው ይህ ዓለም ነው፣ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው። እንክርዳዱ የክፉው ልጆች ናቸው፤
39ዘሩን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው። መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ አጫጆቹም መላእክት ናቸው።
40ስለዚህ እንክርዳዱ ተሰብስቦ በእሳት እንደሚቃጠል፣ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል።
41የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፣ ከመንግሥቱ ለኅጢአት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ሁሉና፣ ክፉ አድራጊዎችን ይሰበስቧቸዋል፣
42ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት፣ ወደ እቶን እሳትም ይጥሏቸዋል።
43ከዚያም ፃድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። ጆሮ ያለው ይስማ።
44መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፣ አንድ ሰውም አግኝቶ ደበቃት፤ ከደስታውም የተነሳ ያለውን ንብረት ሁሉ ሸጦ ያንን ዕርሻ ገዛው።
45ደግሞም፣ መንግሥተ ሰማይ የከበሩ ዕንቈች የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች።
46በጣም ትልቅ ዋጋ ያለው ዕንቊ ባገኘ ጊዜ፣ ሄዶ ያለውን ንበረት ሁሉ ሸጠና ገዛው።
47እንዲሁም፣መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለችና ሁሉም ዓይነት ፍጥረታት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች።
48መረቡዋ ስትሞላ፣ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ዳር አወጡት። ተቀምጠውም መልካም መልካሙን ሰብስበው በዕቃ አደረጉ፣ የማይጠቅመውን ግን አውጥተው ጣሉት።
49በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፣ መላእክት መጥተው ከጻድቃን መካከል ክፉዎችን ይለያሉ።
50ከዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት፣ ወደሚነደው እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።
51ይህን ሁሉ ተረድታችኋል?" አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “አዎን” አሉት።
52ከዚያም ኢየሱስ፣ “ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማይ ደቀ መዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ፣ ከሀብቱ መካከል አሮጌውንና ዐዲሱን ያወጣ የቤት ጌታን ይመስላል አላቸው"።
53ከዚያም ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች በጨረሰ ጊዜ፣ ከዚያ ስፍራ ሄደ።
54ኢየሱስ ወደ ራሱ አገር መጥቶ፣ በምኲራቦቻቸው ሕዝቡን አስተማረ፣ ከዚህም የተነሣ ተገርመው፣ "ይህ ሰው ይህን ጥበቡንና እነዚህን ተአምራት ከየት አገኘ?
55ይህ ሰው የአናጢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም አይደለችም ወይ? ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳስ ወንድሞቹ አይደሉም ወይ?
56እኅቶቹስ ከእኛው ጋር አይደሉም ወይ? ታዲያ ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከየት አገኛቸው?" አሉ።
57በእርሱም ተሰናከሉበት። ኢየሱስ ግን፣ "ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤተ ሰቡ በቀር መከበሩ አይቀርም" አላቸው።
58በአለማናቸውም ምክንያት ፣በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።