1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት በእርሻ መካከል ሄደ። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ስለ ነበር፣ እሸቱን እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር፡፡
2ፈሪሳውያንም ያንን ባዩ ጊዜ፣ “ኢየሱስን፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት የሚያደርጉትን የማይገባ ነገር ተመልከት” አሉት፡፡
3ኢየሱስ ግን፣ "ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን?
4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ለካህናት ብቻ እንጂ ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ እንጀራ እንዴት እንደበላ?" አላቸው።
5በሰንበት ካህናት በቤተ በመቀደስ ሥራ እንድሚሠሩና፣ ሰንበትን እንደሚያረክሱ፣ በደልም እንደማይሆንባቸው ከሕጉ አላነበባችሁምን?
6እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ከቤተ መቅደስ የሚበልጠው እዚህ አለ፡፡
7“መሥዋዕትን ሳይሆን ምሕረትን እፈልጋለሁ” የሚለውን ብታውቁ ኖሮ፣ በደል የሌለባቸውን አትፈርዱባቸውም ነበር፡፡
8የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።"
9ከዚያም ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ፣ ወደ ምኲራባቸው ገባ።
10እነሆ፣ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን በኅጢአት ለመክሰስ፣ "ሕጉ በሰንበት መፈወስን ይፈቅዳልን?" ብለው ጠየቁት፡፡
11ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ብቻ ብትኖረውና፣ ያቺም በግ ጉድጓድ ውስጥ ብትገባበት፣ በሰንበት የማያወጣት ማን ነው?
12ታዲያ ሰውማ ፣ ከበግ ይልቅ ምን ያህል ዋጋ ይኖረዋል! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል ፡፡"
13ከዚያም ኢየሱስ፣ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፡፡ እጁንም ዘረጋ፣ እንደ ሌላውም እጅ ጤነኛ ሆነ፡፡
14ነገር ግን ፈሪሳውያን ሄደው አሤሩበት፣ እርሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፡፡
15ኢየሱስ ይህን እንዳወቀ፣ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እርሱም ሁሉንም ፈወሳቸው፡፡
16ሰዎቹን ስለ እርሱ ለሌሎች እንዳይገልጹ አዘዛቸው፣
17ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤
18እነሆ፣ እኔ የመረጥኩት አገልጋዬ፤ የምወደው ነፍሴም ደስ የተሰኘችበት። መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ፍትሕን ለአሕዛብ ያውጃል።
19አይጨቃጨቅም ወይም አይጮህም፤ ወይም ማንም ድምፁን በጐዳናዎች ላይ አይሰማም።
20ፍርድን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፤ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፣ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም፣
21አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ።"
22ከዚያም በአጋንንት የተያዘን ዐይነ ስውርና ዲዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ዲዳውም ተናገረ፣ አየም።
23ሕዝቡም በመገረም፣ "ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆን እንዴ?" አሉ፡፡
24ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን ተአምር በሰሙ ጊዜ “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በቀር አጋንንቱን አያወጣም ነበር" አሉ፡፡
25ኢየሱስም ዐሳባቸውን ዐውቆ ፣“እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ይወድቃል፤ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማ ወይም ቤት ሁሉ አይጸናም፡፡
26ሰይጣን ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል፣ መንግሥቱስ እንዴት ይቆማል?
27እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ተከታዮቻችሁ በማን ሊያወጡ ነው? ከዚህ የተነሣ እነርሱው ይፈርዱባችኋል፡፡
28ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆነ፣ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች፡፡
29ማንም ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ቤቱ ገብቶ ንብረቱን እንዴት መዝረፍ ይችላል?፡፡ ካሰረው በኋላ ግን፣ ንብረቱን ይዘርፋል።
30ከእኔ ጋር ያልሆነ ተቃዋሚዬ ነው፣ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል፡፡
31ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ማንኛውም ኅጢአትና ስድብ ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል ፤መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን ይቅር አይባልም፡፡
32በሰው ልጅ ላይ ማንኛውንም ቃል የሚናገር ይቅር ይባልለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገር ግን፣ በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ይቅር አይባልም።
33እንግዲህ ዛፍ የሚታወቀው በፍሬው ስለ ሆነ ዛፉን መልካም አድርጉ፤ ፍሬውም መልካም ይሆናል፣ ወይም ዛፉን መጥፎ አድርጉ ፍሬውም መጥፎ ይሆናል፡፡
34እናንተ የእባብ ልጆች ክፉዎች ስለ ሆናችሁ፣ እንዴት መልካም ልትናገሩ ትችላላችሁ? ምክንያቱም በልብ ውስጥ የሞላውን አፍ ይናገረዋል፡፡
35. መልካም ሰው በልቡ ውስጥ ካለው መልካም መዝገብ፣ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ልቡ ውስጥ ካለው ክፉ መዝገብ ክፉውን ይወጣል።
36ለእናንተም እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ሰዎች ስለ ተናገሯቸው ከንቱ ንግግሮች መልስ ይሰጣሉ፡፡
37ምትናገሩት ትጸድቃላችሁ፣ በምትናገሩትም ይፈረድባችኋልና፡፡
38አንዳንድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን መልሰው ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ ምልክት እንድታሳየን እንፈልጋለን" አሉት።
39ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፣ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምንም አይሰጠውም፡፡
40ዮናስ በትልቅ ዐሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ የሰው ልጅም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ይሆናል፡፡
41የነነዌ ሰዎች በዮናስ ስብከት ንስሓ በመግባታቸው፣ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፡፡ ደግሞም ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ፡፡
42የደቡብ ንግሥት፣ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻዎች መጥታለችና፣ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፡፡ደግሞም ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ፡፡
43ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ፣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለባቸው ቦታዎች ያልፋል፣ ነገር ግን አያገኝም።
44ከዚያም፣ 'ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ' ይላል። ሲመለስም ቤቱ ጸድቶ ተዘጋጅቶ ያገኘዋል፡፡
45ከዚያም ይሄድና ከእርሱ ይልቅ የከፉትን ሰባት ሌሎች መናፍስትን ይዞ ይመጣል፣ ሁሉም በዚያ ለመኖር ይመጣሉ፡፡ የዚያም ሰው የመጨረሻው ሁኔታ ከመጀመሪያው የከፋ ይሆናል፡፡ በዚህ ክፉ ትውልድ ላይ የሚሆነውም እንደዚሁ ነው፡፡
46ኢየሱስም ለሕዝቡ እየተናገረ እያለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያናግሩት ፈልገው፣ በውጭ ቆመው ነበር።
47አንድ ሰውም፣ "እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ በውጭ ቆመዋል" አለው።
48ኢየሱስም መልሶ ለነገረው ሰው፣ "እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?" አለው።
49ከዚያም እጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፣ "እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!
50በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴ እናቴም ነውና" አለ።