1እንዲህም ሆነ፣ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት አዝዞ ከጨረሰ በኋላ፣ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ ሄደ፡፡
2ዮሐንስ በወህኒ ቤት ሆኖ የክርስቶስን ሥራዎች በሰማ ጊዜ፣ በደቀ መዛሙርቱ መልእክት ላከበት፡፡
3እንዲህም አለው፣ "የሚመጣው አንተ ነህ፣ ወይስ መጠበቅ ያለብን ሌላ ሰው አለ?"
4ኢየሱስም መለሰ እንዲህም አላቸው፤ “ሂዱና፣ ለዮሐንስ የምታዩትንና የምትሰሙትን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤
5ዕውሮች ብርሃናቸውን እያገኙ፣ አንካሶች እየተራመዱ፣ ለምጻሞች እየነጹ፣ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ፣ ሙታን እየተነሡ፣ ድኾችም የምሥራች እየሰሙ ነው፡፡
6በማንኛውም ሁኔታ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ የተባረከ ነው" ።
7እነዚህ ሰዎች እንደ ሄዱ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ መናገር ጀመረ፣ እንዲህም አለ፣ "ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆን?
8ግን ምን ልታዩ ወጣችሁ? የሚያምር ልብስ የለበሰውን? በርግጥ፣ ጥሩ ልብስ የሚለብሱ የሚኖሩት በቤተ መንግሥት ነው፡፡
9ግን ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ነውን? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጠውን ነው፡፡
10እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ስለ እርሱ ነው፦ 'መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡'
11እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም። በመንግሥተ ሰማይ ግን፣ ታናሹ ሰው ከእርሱ ይበልጣል፡፡
12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በዐመፅ ትቸገራለች፣ ዐመጸፀኞች ግን በኅይል ይወስዷታል፡፡
13እስከ ዮሐንስ ዘመን ድረስ ሕጉም፣ ነቢያቱም ሁሉ ትንቢት ሲናገሩ ነበርና፡፡
14እንግዲህ ልትቀበሉት ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ የሚመጣው ኤልያስ እርሱ ነው፡፡
15የሚሰማ ጆሮ ያለው፣ ይስማ።
16ይህን ትውልድ ከምን ጋር ላነጻጽረው? በገበያ ተቀምጠው፣ እየተቀባበሉ እንደሚዘፍኑ ልጆች ነው፡፡
17'ዋሽንት ነፋንላችሁ፣ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ እናንተም አላለቀሳችሁም' ይላሉ።
18ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ በመምጣቱ፣'ጋኔን አለበት' አሉት።
19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ በመምጣቱ፣ 'ተመልከቱ ይህ ሰው በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና፣ የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው!' አሉት ነገር ግን ጥበብ በሥራዋ ትክክል ሆነች፡፡
20ኢየሱስም ብዙ ታላላቅ ሥራዎች ያደረገባቸውን ከተማዎች፣ ንስሓ ባለመግባታቸው ይገሥጻቸው ጀመር፡፡
21ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ታላላቅ ሥራዎች በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ማቅ ለብሰውና፥ ዐመድ ነስንሰው ድሮ ንስሓ በገቡ ነበር፡፡
22ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ፣ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል፡፡
23አንቺ ቅፍርናሆም፣ እስከ ሰማይ የወጣሽ ይመስልሻልን? በፍጹም፤ ወደ ሲኦል ትወርጂያለሽ፡፡ ለአንቺ እንደተደረጉት ትልልቅ ነገሮች በሰዶም ተደርገው ቢሆን ፣ እስከ አሁን በኖረች ነበር፡፡
24ነገር ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን፣ ከእናንተ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል፡፡
25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ ይህን ከዐዋቂዎችና ከአስተዋዮች ሰውረህ እንደ ሕፃናት ላልተማሩት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።”
26አዎ፣ አባት ሆይ፣ በፊትህ እጅግ ደስ የሚያሰኝህ ይህ ሆኖአልና፡፡
27ከአባቴ ሁሉ ተሰጥቶኛል፣ ከአባት በቀር ማንም ልጅን የሚያውቀው የለም፤ ከልጅም በቀር፣ ልጁም ሊገልጥለት ከሚፈልገው በቀር፣ አባትን የሚያውቅ ማንም የለም፡፡
28እናንተ ደካሞች፣ ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋላሁ፡፡
29ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህና በልቤ ትሁት ነኝ፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፡፡
30ቀንበሬ ቀላል፣ ሸክሜም የማይከብድ ነው፡፡