1አሁንም፣ እናንተ ካህናት ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2“የማትሰሙና ለስሜ ክብር ለመስጠት በልባችሁም የማታኖኑት ከሆነ” ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ፣ “መርገም እልክባችኋለሁ፤ በረከታችሁን እረግማለሁ። ትእዛዜን በልባችሁ አላኖራችሁምና በእርግጥ ረግሜአችኋለሁ።
3ዘራችሁን እገሥጻለሁ፤ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ ፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር ትጠፋላችሁ።
4ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ያዘዝሁ እኔ መሆኔንም ታውቃላችሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ።
5“ከእርሱ ጋር ያደረግሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነዚህን ለእርሱ ሰጠሁት፤ አከበርኩት፤ እርሱ አከበረኝ፤ በስሜ ፊት በፍርሃት በመንቀጥቀጥ ቆመ።
6እውነተኛ ትምህርት በአንደበቱ ነበር፤ በከንፈሮቹ ምንም ሐሰት አልተገኘም። በሰላምና በጽድቅ ከእኔ ጋር ተመላለሰ፤ ብዙዎችንም ከኅጢአት መለሰ።
7የካህኑ ከንፈሮች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤ እርሱ የሠራዊት ጌታ የያህዌ መልዕክተኛ ስለሆነ ሰዎች ከአፉ ትምህርት መፈለግ ይኖርባቸዋል።
8እናንተ ግን ከእውነተኛው መንገድ ወጥታችኋል። ሕጉን በተመለከተም ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊን ኪዳን አፍርሳችኋል።” ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ።
9“መንገዴን አልጠበቃችሁም፤ ትምሕርቱን በተመለከተ አድልዎ አድርጋችኋል፤ ስለዚህ እኔም በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትዋረዱና እንድትናቁ አደርጋለሁ።”
10ለሁላችንም ያለን አንድ አባት አይደለምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ፣ እያንዳንዱ ሰው ለወንድሙ ታማኝ ባለመሆን የአባቶቻችንን ኪዳን ያረከስነው ለምንድንው?
11ይሁዳ አልታመነም። በእስራኤልና በኢየሩሳሌም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሞአል።
12እንዲህ የሚያደርገውን ሰው፣ ሌላው ቀርቶ ለሠራዊት ጌታ ለያህዌ መሥዋዕት የሚያመጣ እንኳ ቢሆን፣ ያህዌ ከያዕቆብ ድንኳኖች ያስወግደው።
13እናንተ ይህንንም አድርጋችኋል፣ የያህዌን መሠዊያ በእንባ አጥለቅልቃችኋል፤ እርሱ ቁርባናችሁን ስለማይመለከት ወይ በደስታ ከእጃችሁ ስለማይቀበለው ትጮኻላችሁ ታለቅሳላችሁም።
14እናንተም፣ “ይህ ለምን ሆነ?” በማለት ትጠይቃላችሁ። እንዲህ የሆነው ያህዌ በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለሆነ ነው፤ የቃል ኪዳን ጓደኝህና ሚስትህ ብትሆን እንኳ አንተ ለእርሷ ታማኝ አልነበርክም።
15በመንፈሱ ክፋይ እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? እርሱ አንድ ያደረጋችሁ ለመንድነው? ምክንያቱም ለእግዚአብሔር የሚሆን መሥዋዕት ስለፈለገ ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁ ጋር ያላችሁንም ታማኝነት አታጉድሉ።
16“እኔ መፋታትን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ ያህዌ፤ “ልብሱን በግፍ ሥራ የሚሸፍነውንውም ሰው እጠላለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ያህዌ። “ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ታማኝነታችሁንም አታጉድሉ።”
17በቃላችሁ ያህዌን አታክታችኋል። እናንተ ግን፣ “እርሱን ያታከትነው በምንድነው?” ብላችኋል። “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ በያህዌ ፊት መልካም ነው፤ እርሱም በክፉዎች ደስ ይለዋል፤ ወይም፣ “የፍትህ አምላክ ወዴት ነው?” በመለታችሁ ነው።