መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይና በሽታዎችን የመፈወስ ሥልጣን ሰጣቸው።
2የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና በሽተኞችን እንዲፈውሱ ላካቸው።
3እንዲህም አላቸው፤ “ለጒዞአችሁ በትርም ቢሆን፣ የገንዘብም ቦርሳ ቢሆን፣ ስንቅም ቢሆን፣ ገንዘብ ወይም ቅያሬ ልብስ፣ ምንም ነገር አትያዙ።
4ከዚያ ስፍራ እስከምትወጡ በገባችሁበት ቤት በዚያ ቆዩ።
5“የማይቀበሏችሁ ቢኖሩ ከዚያ ከተማ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግሮቻችሁ ጫማ ላይ አቧራውን አራግፉ።”
6ከዚያም እነርሱ ከዚያ ተነሥተው የምሥራቹን ወንጌል እየሰበኩ፣ በሄዱባቸውም ስፍራዎች ሁሉ በሽተኞችን እየፈወሱ ያልፉ ነበር።
7የአራተኛው ክፍል ገዢ ሄሮድስ እየተደረገ የነበረውን ሁሉ በሰማ ጊዜ፣ በጣም ተሸበረ፣ ምክንያቱም ‘አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቷል፤
8በሌሎች ዘንድ ደግሞ ኤልያስ ተገልጧል፤ እንደ ገና ሌሎች ከጥንት ነቢያት አንዱ ሕያው ሆኖ ተነሥቷል’ ይሉ ነበር።
9ሄሮድስም “የዮሐንስን ራስ እኔ አስቈርጬዋለሁ፣ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ይህ ማን ነው?” አለ። ሄሮድስም ኢየሱስን ለማየት ጥረት ያደርግ ነበር።
10የተላኩት በተመለሱ ጊዜ፣ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ኢየሱስ ራሱ ሐዋርያቱን አስከትሎ ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ ሄደ።
11ነገር ግን፣ ሕዝቡ ስለዚህ ጉዳይ ሰሙና ተከተሉት፣ እርሱም ተቀብሏቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው፣ መፈወሰ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።
12ቀኑ ወደ መገባደድ ተቃረበ፣ ዐሥራ ሁለቱም ወደ እርሱ መጡና “ያለንበት ቦታ ምንም የሌለበት ምድረ በዳ በመሆኑ ሕዝቡ በአካባቢው ወዳሉት መንደሮችና ገጠሮች ሄደው ማረፊያ ቦታና ምግብ እንዲያገኙ አሰናብታቸው” አሉት።
13እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተ ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ወጣ ብለን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በስተቀር አሁን ያለን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዐሣ የበለጠ አይደለም” አሉት።
14በዚያ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሃምሳ ሃምሳ ሆነው በቡድን እንዲቀመጡ አድርጓቸው” አላቸው።
15ስለዚህ እርሱ እንዳላቸው አደረጉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ተቀመጡ።
16እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዐሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ ከተመለከተ በኋላ ባርኮ፣ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው።
17ሁሉም በልተው ጠገቡ፣ የተራረፈውም የምግብ ፍርፋሪ ተሰበሰበና ዐሥራ ሁለት ቅርጫት ሙሉ ሆነ።
18ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ በነበረበት አንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና፣ “ሕዝቡ እኔ ማን እንደሆንሁ ነው የሚናገሩት?” ብሎ ጠየቃቸው።
19እነርሱም፣ “አጥማቂው ዮሐንስ ፣ ሌሎች ደግሞ ኤልያስ፣ እንደ ገና ሌሎች ጥንት ከነበሩት ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቶ ነው ይላሉ” አሉት።
20“እናንተ ግን እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር የመጣህ ክርስቶስ ነህ” ብሎ መለሰ።
21ነገር ግን ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይነግሩ በማስጠንቀቅ አዘዛቸው።
22በተጨማሪም የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል እንደሚገባው በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በሕግ መምሕራን ተቀባይነት እንደማያገኝ፣ እንደሚሞትና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ በቅድሚያ አስታወቃቸው።
23ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ "እኔን መከተል የሚፈልግ ራሱን ይካድ ዕለት ዕለትም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ።
24ሕይወቱን ሊያድን ጥረት የሚያደርግ ሰው ካለ ያጠፋታል፣ ስለ እኔ ብሎ ሕይወቱን የሚጥል ደግሞ ያድናታል።
25አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ የራሱን ሕይወት ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?
26በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ በራሱ፣ በአባቱ፣ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ ያፍርበታል።
27እኔ ግን በእውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆማችሁት መካከል አንዳንዶቻችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እስከምታዩ ድረስ ሞትን አትቀምሱም።
28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ገደማ በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን፣ እንዲሁም ያዕቆብን ይዞ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ።
29እየጸለየም ሳለ የፊቱ መልክ ተለወጠ ልብሱም በጣም ከመንጣቱ የተነሣ አንፀባረቀ።
30እነሆ፣ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር!
31እነርሱም በክብር የተገለጡት ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ከዚህ ሕይወት ስለ መለየቱ ይነጋገሩ ነበር።
32ጴጥሮስና ዐብረውት የነበሩት እንቅልፍ ከብዶባቸው ነበር። ሙሉ በሙሉ በነቁ ጊዜ ግን የኢየሱስን ክብርና ዐብረውት የነበሩትን ሁለቱን ሰዎች አዩ።
33እነርሱ ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፣ ለእኛ በዚህ መሆን መልካም ነው፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ደግሞ ለኤልያስ ሦስት ዳሶችን ልንሠራ ይገባናል” አለው። ስለ ምን እየተናገረ እንደ ነበረ አላስተዋለም።
34ከዚያም እርሱ ይህን እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ በዙሪያቸው ከነበረው ደመና የተነሣ ፈሩ።
35ከደመናው ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።
36የድምፁ መሰማት ባበቃ ጊዜ፣ ኢየሱስ ብቻውን ነበረ። እነርሱም ዝም አሉ፤ በነዚያ ቀናት ስላዩአቸው ስለ እነዚያ ነገሮች ምንም ነገር ለማንም አልተናገሩም።
37ከተራራው በወረዱ ማግስት ብዙ ሕዝብ ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ።
38እነሆም፣ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፣ ብቸኛ የሆነውን አንድ ልጄን ትመለከትልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
39ክፉ መንፈስ በላዩ ሲመጣበት በድንገት ይጮኻል፣ እየጣለ ያንፈራግጠዋል፤ አረፋም በአፉ ይደፍቃል። በጭንቅ ለቅቆት ይሄዳል፣ በሚሄድበት ጊዜ ክፉኛ ያቈስለዋል።
40ክፉውን መንፈስ እንዲያወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ለመንኋቸው፣ እነርሱ ግን አልቻሉም” በማለት ጮኸ።
41ኢየሱስ እንደዚህ በማለት መልስ ሰጠ፣ “ክፉና ጠማማ ትውልድ፣ ከእናንተ ጋር የምኖረውና የምታገሣችሁ እስክ መቼ ነው? ልጅህን ወደዚህ አምጣው።”
42ልጁ እየመጣ ሳለ ጋኔኑ ጣለው፣ እጅግም አንፈራገጠው። ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሠጸውና ልጁን ፈወሰው፣ ለአባቱም መልሶ ሰጠው።
43ሁሉም በእግዚአብሔር ታላቅነት ተደነቁ። ነገር ግን ሁሉም እርሱ ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እየተደነቁ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣
44"የነገርኋችሁን እነዚህን ነገሮች በጥልቀት አስተውሉ፤ ምክንያቱም የሰውን ልጅ በሰዎች እጅ አሳልፈው ይሰጡታል" አላቸው።
45ነገር ግን ተሰውሮባቸው ስለ ነበረ፣ ይህ አባባሉ ምን እንደ ሆነ ስላልተረዱት ሊገባቸው አልቻለም። ስለዚያ አባባል እርሱን መጠየቅ ፈሩ።
46ከዚያም ከእነርሱ መካከል ከሁሉም እጅግ ታላቅ የሆነው ማን ነው የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት ክርክር ተነሣ።
47ኢየሱስ ግን በልባቸው ምን እያሰላሰሉ እንደ ነበሩ ባወቀ ጊዜ፣ አንድ ትንሽ ልጅ ይዞ በአጠገቡ አቆመው፣ እንዲህም አላቸው፤
48"እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል፣ እኔን ይቀበላል። እኔን የሚቀበል ከሆነ ደግሞ የላከኝን ይቀበላል። ስለሆነም፣ በመካከላችሁ ከሁላችሁም የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና።”
49ዮሐንስ መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፣ ከእኛ ጋር ስላልሆነ ከለከልነው።"
50ኢየሱስ ግን፣ “አትከልክሉት፣ ምክንያቱም የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነው” አላቸው።
51ወደ ሰማይ የሚሄድበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ።
52ከእርሱ ቀደም ብለው እንዲሄዱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ሊያዘጋጁለት ዘንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ።
53ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አንቅቶ ስለ ነበር፣ በዚያ የነበሩት ሕዝብ አልተቀበሉትም።
54ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ባዩ ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፣ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትወዳለህን?” አሉት።
55እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሰጻቸው።
56ከዚያም ወደ ሌላ መንደር ሄዱ።
57እየሄዱ ሳሉም አንድ ሰው፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።
58ኢየሱስ፣ “ቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት መጠለያ የለውም” አለው።
59ከዚያም ለሌላውን ሰው፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውዬው ግን፣ “ጌታ ሆይ፣ በቅድሚያ እንድሄድና አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።
60እርሱ ግን፣ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፣ አንተ ግን በየስፍራው ሁሉ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አውጅ” አለው።
61ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፣ እከተልሃለሁ ነገር ግን በቅድሚያ የቤተ ሰቤን አባላት እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው።
62ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።