መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ወንጌል እየሰበከና እያወጀ ወደ ልዩ ልዩ ከተሞችና መደሮች መጓዝ ጀመረ። በጒዞውም ወቅት ዐሥራ ሁለቱ፣
2እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከሕመማቸው የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች ዐብረውት ሄዱ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት ማርያም፣
3እንደ የሄሮድስ ቤተ መንግሥት አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት የነበረችው ዮሐና፣ ሶስና ሌሎችም ብዙ ሴቶች ነበሩ፤ እነዚህ ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በገንዘባቸው ያገለግሉ ነበር።
4ከብዙ የተለያዩ ከተሞች የመጡትን ጨምሮ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ በምሳሌ ተጠቅሞ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፤
5“አንድ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ።እንደ ዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፣ የሰማይ ወፎችም መጥተው በሉት።
6ሌላው ዘርም በጭንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥብ አፈር ስላልነበረው ወዲያው ደረቀ።
7ሌላውም ዘር በእሾህ መካከል ወደቀ እሾሁም ከዘሩ ጋር ዐብሮት አደገና አነቀው።
8ከዘሩ አንዳንዱ ግን በመልካም ዐፈር ላይ ወደቀ መቶ እጥፍ ፍሬም አፈራ።" ኢየሱስ ይህንን ከተናገረ በኋላ ጮኽ ብሎ፣ "ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
9ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ይህ ምሳሌ ምን ማለት እንደ ሆነ ጠየቁት፤
10ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ "ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር የማወቅ ዕድል ተሰጥቷችኋል፣ ለተቀሩት ሕዝብ ግን 'እያዩ ስለማያዩ፣ እየሰሙም ስለማያስተውሉ' የሚማሩት በምሳሌ ነው።
11ትርጕም እንደዚህ ነው፣ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
12በመንገድ ዳር የወደቁት ሰምተው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ የሰሙትን ቃል ከልባቸው የሚወሰድባቸው ናቸው።
13በድንጋይ መካከል የወደቁትም ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉትና መስማት እንጂ፣ በቃሉ ሥር ስላልሰደዱ ለጊዜው አምነው ፈተና በመጣባቸው ጊዜ፣ እምነታቸውን የሚክዱ ናቸው።
14በእሾኽ መካከል የወደቀው ዘር ቃሉን የሰሙ ሰዎች ሲሆኑ፣ በኑሮ ሂደታቸው ወቅት በምድራዊ ሕይወት ዐሳብና በባለጠግነት ምቾት የሚታነቁ በመሆናቸው ፍሬ ወደ ማፍራት የማይመጡ ናቸው።
15ነገር ግን በመልካሙ ዐፈር ላይ የወደቁት በመልካምና በቅን ልብ ካደመጡ በኋላ ቃሉን አጥብቀው የሚይዙ በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
16እንግዲህ፣ አንድ ሰው መብራት ካበራ በኋላ ጎድጓዳ ነገር ውስጥ ወይም ከአልጋ ሥር አያደርገውም። ከዚያ ይልቅ ሁሉም ሰው ብርሃኑን ማየት ይችል ዘንድ ከፍ ባለ ስፍራ ላይ ያስቀምጠዋል።
17ምክንያቱም የሚታወቅ እንጂ የሚደበቅ፣ ታውቆ ወደ ብርሃን የሚወጣ እንጂ ምሥጢር የሚሆን ነገር የለም።
18ስለዚህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፣ ምክንያቱም ላለው ሁሉ የበለጠ ይሰጠዋል፣ ከሌለው ደግሞ እንዳለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።"
19ከዚያም የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፣ ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ መቅረብ አልቻሉም።
20ስለሆነም፣ ‘እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው እየጠበቁህ ናቸው’ የሚል መልእክት አመጡለት።
21ነገር ግን ኢየሱስ መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።
22ከዕለታት አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ሲሳፈሩ ኢየሱስ፣ "ሐይቁ ማዶ እንሻገር" አላቸው። ከዚያም እነርሱ መቅዘፍ ጀመሩ።
23ነገር ግን እየቀዘፉ ሳሉ ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደውና በታላቅ ነፋስ የታጀበ ማዕበል በሐይቁ ላይ ስለተነሣ ጀልባቸው ውስጥ ውሃ መግባት ጀመረ'፤ታላቅ አደጋም በፊታቸው ተደቀነ።
24ከዚያም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ መጥተው፣ "መምህር ሆይ፣ መምህር ሆይ፣ መሞታችን ነው" በማለት ቀሰቀሱት። እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ ነፋሱንና የሚናወጠውን ማዕበል ገሰጸ ጸጥ አደረጋቸው።
25ከዚያም ኢየሱስ፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። ፍርሃት ይዟቸውና በጣም ተደንቀው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሳትንና ባሕርን የሚያዝ እነርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?" ተባባሉ።
26ከገሊላ ባሕር በስተ ማዶ በሌላው አንጻር ወደ ነበረው ወደ ጌርጌሴኖን ክልል ደረሱ።
27ኢየሱስ ከጀልባው ወርዶ ወደ ምድር በተሻገረ ጊዜ፣ አጋንንት የነበሩበት አንድ ሰው አገኘው። ይህ ሰው ለረጅም ጊዜ ልብስ ለብሶ አያውቅም፤ በመቃብር ስፍራ እንጂ፣ በቤትም ውስጥ አልኖረም።
28ኢየሱስን ባየው ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅም ድምፅ፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! እኔ ከአንተ ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለው።
29እንደዚህም ያለበት ምክንያት ብዙ ጊዜ ይይዘውና ያሠቃየው የነበረውን ርኩስ መንፈስ ከእርሱ እንዲወጣ ኢየሱስ አዞት ስለነበር ነው። ምንም እንኳ በብረት ሰንሰለት የታሰረና በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገ ቢሆንም፣ እስራቱን ይበጥስ፣ በአጋንንቱም ግፊት ወደ በረሐ እየሄደ ይንከራተት ነበር።
30ከዚያም ጊዜም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ነበርና ስሜ፣ "ጭፍራ" ነው ብሎ መለሰ።
31በውስጡ የነበሩት አጋንንት ወደ ጥልቁ እንዲሄዱ እንዳያዛቸው መለመናቸውን ቀጠሉ።
32በዚያም ብዙ ዐሳማዎች በኮረብታው ላይ ለግጦሽ ተሰማርተው ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሳማዎቹ ይገቡ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት። ኢየሱስ የለመኑትን እንዲያደርጉ ፈቀደላቸው።
33ስለዚህ አጋንንቱ ከሰውዬው ወጥተው ዐሳማዎቹ ውስጥ ገቡ። ዐሣማዎቹን ከኮረብታው ተጣድፈው ቁልቁል ወረዱ፣ ወደ ሐይቁም ውስጥ ገብተው ሰጠሙ።
34ዐሳማዎቹን ሲያሰማሩ የነበሩት ሰዎች ይህን በተመለከቱ ጊዜ ወደ ከተማውና ወደ ገጠሮች ሁሉ ሸሽተው በመሄድ ዜናውን አሠራጩ።
35ስለዚህ ይህንን የሰሙት ሰዎች የሆነውን ለማየት ወጡ፤ ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ አጋንንት የወጡለትን ሰው አገኙት። ሰውዬውም ልብስ ለብሶ ወደ አእምሮውም ተመልሶ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ ሲያዩት፣ ፍርሃት ያዛቸው።
36ከዚያም የሆነውን ነገር ያዩ ሰዎች በአጋንንት ቁጥጥር ሥር የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ ለሌሎች ተናገሩ።
37የጌርጌሴኖን ክልልና የዚያ አካባቢ ሰዎች ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዟቸው ስለ ነበረ፣ ኢየሱስ ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት፤ እርሱም ከዚያ ስፍራ ወደ መጣበት ለመመለስ ወደ ጀልባይቱ ገባ።
38አጋንንት የወጡለት ሰው ዐብሮት ለመሄድ ኢየሱስን ለመነው።
39ኢየሱስ ግን፣ “ወደ ቤተ ሰብህ ተመልሰህ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ተርክላቸው” ብሎ አሰናበተው። ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ታላላቅ ነገሮች በከተማው ሁሉ እየመሰከረ ጒዞውን ቀጠለ።
40ሁሉም ይጠብቁት ነበርና ኢየሱስ ሲመለስ ሕዝቡ ተቀበሉት።
41እነሆም ከምኲራብ መሪዎች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው መጣ፤ እርሱም በኢየሱስ እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ ይመጣ ዘንድ ለመነው።
42ወደ ቤቱ እንዲመጣ የፈለገው ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆናት እንድያ ልጁ በሞት አፋፍ ላይ ስለነበርች ነው። ነገር ግን ወደዚያ እየሄደ በነበረበት ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በመጨናነቅ ይጋፉት ነበር።
43በዚያም ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረች፣ ገንዘቧን ሁሉ ለሐኪሞች ብትከፍልም አንዳቸውም ያልፈወሷት አንዲት ሴት ነበረች።
44እርሷ ከኢየሱስ በስተኋላ መጥታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ የፈሳት የነበረው ደምም ወዲያው ቆመ።
45ኢየሱስ፣ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም አልነካንህም ብለው በተናገሩ ጊዜ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፣ ሕዝቡ እኮ እየገፋፉህና እያጨናነቁህ ነው” አለው።
46ኢየሱስ ግን፣ “ከእኔ ኅይል እንደ ወጣ ዐውቄአለሁና አንድ ሰው ነክቶኛል” አለ።
47ሴቲቱ ያደረገችውን መደበቅ እንዳልቻለች ባስተዋለች ጊዜ፣ ሴቲቱ እየተንቀጠቀጠች መጣችና በኢየሱስ እግር ሥር ወድቃ በሰዎች ሁሉ ፊት እርሱን ለምን እንደነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች ተናገረች። ከዚያም ኢየሱስ ሴቲቱን፥
48“ልጄ ሆይ እምነትሽ አድኖሻል በሰላም ሂጂ” አላት።
49እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ ከምኲራብ አለቃው ቤት አንድ ሰው መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች። መምህሩን አታድክመው” አለ።
50ኢየሱስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፣ እርሷም ትድናለች” አለው።
51ከዚያም እርሱ ወደዚያ ቤት በመጣ ጊዜ፣ ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስ፣ ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና ከእናትዋ በስተቀር ማንም ዐብሮት እንዲገባ አልፈቀደም።
52በዚያ ስፍራ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ያለቅሱ ዋይ ዋይም ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ ልጅትዋ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አለ።
53እነርሱ ግን መሞቷን ዐውቀው ስለ ነበር፣ በንቀት ሳቁበት።
54እርሱ ግን የልጅቱን እጅ ይዞ፣ “አንቺ ልጅ ተነሽ” አላት።
55ነፍስዋም ተመለሰች፣ ወዲያውኑም ብድግ አለች። እርሱም የምትበላው እንዲሰጧት አዘዘ።
56ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን ስለሆነው ነገር ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።