1ከዚህ በኋላ ጌታ፣ ሌሎች ሰባ ሰዎችን ሾመ፤ እርሱ ራሱ ሊሄድባቸው ወዳሰባቸው ከተማዎችና ስፍራዎች ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤
2እንዲህም አላቸው፣ "መከሩ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲክ የመከሩን ጌታ በአስቸኳይ ለምኑት።
3እንግዲህ ሂዱ፣ እነሆ፣ በተኲላዎች መካከል እንደ በጎች እልካችኋለሁ፡፡
4ለመንገዳችሁ ምንም አትያዙ፤ የገንዘብ ቦርሳም ቢሆን የመንገደኛ ሻንጣም ቢሆን፣ ጫማም ቢሆን አትያዙ፣ በመንገድም ላይ ለማንም ሰላምታ አትስጡ፡፡
5ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ፣ በቅድሚያ 'ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን' በሉ፡፡
6በዚያ ቤት ያለው ሰው የሰላም ሰው ከሆነ ሰላማችሁ ያርፍበታል፣ የሰላም ሰው ካልሆነ ደግሞ ሰላማችሁ ይመለስላችኋል፡፡
7ያቀረቡላችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ በገባችሁበት በዚያው ቤት ቆዩ፣ ምክንያቱም ሠራተኛ ደመወዙን ማግኘት ይገባዋል፡፡ ከቤት ወደ ቤት ግን አትዘዋወሩ፡፡
8ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡና እነርሱም ሲቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ፡፡
9በዚያም ያሉትን ሕመምተኞች ፈውሱ፣ 'የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች' ብላችሁም ንገሩአቸው፡፡
10ነገር ግን ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ እነርሱ ባይቀበሏችሁ፣ ወደ ጐዳናዎቻቸው ውጡና፣
11'በጫማችን ላይ የተጣበቀውን የከተማችሁን አቧራ እንኳ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆንባችሁ ዘንድ እናራግፈዋለን! የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበ ግን ይህንን እወቁ' በሏቸው፡፡
12እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ይቀልላቸዋል፡፡
13ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ ዘንድ የተደረጉት ታላላቅ ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ የሐዘን ልብስ ለብሰውና ራሳቸውን አዋርደው ከረጅም ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር፡፡
14ነገር ግን በፍርድ ወቅት ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።
15አንቺስ ቅፍርናሆም፣ እስከ ሰማይ ከፍ እንዳልሽ ታስቢ ይሆን? እንደዚያ አታስቢ፣ እስከ ሲዖል ድረስ ትወርጃለሽ።
16እናንተን የሚሰማችሁ እኔን ይሰማኛል፣ እናንተንም የማይቀበል እኔን አይቀበለኝም፣ እኔን የማይቀበል ደግሞ የላከኝን አይቀበልም፡፡
17ሰባዎቹም ደስ እያላቸው ተመለሱና፣ ጌታ ሆይ፣ አጋንንት እንኳ በስምህ ታዘዙልን" አሉት፡፡
18ኢየሱስ፣ "ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ
19እነሆ፣ እባቦችንና ጊንጦችን እንድትረግጡ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ምንም አይጐዳችሁም፡፡
20የሆነ ሆኖ መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ብቻ ደስ አይበላችሁ፤ ነገር ግን ስማችሁ በሰማይ ስለ ተጻፈ የላቀ ደስታ ይሰማችሁ።"
21በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እጅግ ሐሤት አደረገና፣ "የሰማይና የምድር ጌታ፣ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከሚያስተወሉ ሰውረህ እንደ ሕፃናት ለሆኑት ላልተማሩት ለእነዚህ ስለ ገለጽህላቸው አመሰግንሃለሁ፡፡ አዎ፣ አባት ሆይ፣ ይህ በፊትህ ዘንድ መልካም ሆኖአልና።
22ሁሉም ነገር ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፣ ከአባትም በቀር ልጁ ማን እንደ ሆነ የሚያውቅ የለም፣ አባትም ማን እንደ ሆነ ከልጁ ወይም ልጁ ሊገልጥለት ከፈለገው ሰው በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።"
23ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መለስ ብሎ፣ ለእነርሱ ብቻ፣ "እናንተ የምታዩትን የሚያዩ የተባረኩ ናቸው፡፡
24ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ ያያችሁትን ለማየት ፈልገው ሳያዩ፣ እናንተም የሰማችሁትን ሊሰሙ ፈልገው ሳይሰሙ ቀርተዋል" አለ።
25እነሆ፣ አንድ የአይሁድ የሕግ መምህር ሊፈትነው ፈልጎ ብድግ አለና፣ "መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል?" በማለት ጠየቀው፡፡
26ኢየሱስ፣ "በሕጉ የተጻፈው ምንድን ነው? የተረዳኸው እንዴት ነው?" አለው።
27እርሱም፣ "ጌታ አምላክህን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ኃይልህ፣ በሙሉ ዐሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ" ብሎ መለሰ፡፡
28ኢየሱስም፣ "በትክክል መልሰሃል፡፡ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ" አለው።
29መምህሩ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወዶ፣ ኢየሱስን፣ "ባልንጀራዬ ማን ነው?" ብሎ ጠየቀው፡፡
30ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፤ "አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ እየሄደ ሳለ ወንበዴዎች አግኝተውት ንብረቱን ዘረፉት፣ ደበደቡት፣ በሞት አፋፍ ላይ እያለም ጥለውት ሄዱ።
31እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲሄድ ሰውዬውን ተመለከተውና በሌላ በኩል አድርጎ አልፎት ሄደ።
32በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ሌዋዊም ወደዚያ ስፍራ መጥቶ በሌላ በኩል አድርጎ አልፎ ሄደ።
33አንድ ሳምራዊ ግን እየተጓዘ ሳለ ሰውዬው ወደነበረበት መጣ። ባየውም ጊዜ በርኅራኄ ልቡ ተነካ።
34ወደ እርሱም ጠጋ ብሎ መድኃኒት ካደረገለት በኋላ ቊስሉን በጨርቅ አሰረለት። እርሱ ይጓጓዝበት በነበረበትም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማረፊያ አመጣው፣ እንክብካቤም አደረገለት።
35በማግስቱ ሁለት ዲናር ከኪሱ አውጥቶ ለእንግዳ ማረፊያው ኅላፊ ሰጠውና፣ "ተንከባከበው፣ ከዚህ በላይ ወጪ የሚያስወጣህ ከሆነ በምመለስበት ጊዜ ያወጣኸውን ትርፍ ወጪ እመልስልሃለሁ" አለው።
36"ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል?" አለው።
37መምህሩም፣ "የራራለቱ ነው" አለ። ኢየሱስም፣ "አንተም ሂድና ይህንኑ አድርግ" አለው።
38እየተጓዙ ሳሉም ወደ አንድ መንደር ገባ፤ ማርታ የምትባልም አንዲት ሴት በቤትዋ ተቀበለችው"
39እርሷም ማርያም የተባለች በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ ቃሉን የምትሰማ እኅት ነበረቻት"
40ማርታ ግን ምግብ ለማዘጋጀት ባደረገችው ጥረት በጣም ውጥረት በዛባት። ወደ ኢየሱስም ዘንድ መጥታ፣ "ጌታ ሆይ፣ እኔ ብቻዬን ሥራ ስሠራ፣ እኅቴ እኔን ሳትረዳኝና ስትተወኝ አንተ ዝም ትላለህን? እንግዲያውስ እንድታግዘኝ ንገራት" አለችው።
41ጌታ ግን፣ "ማርታ፣ ማርታ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፣
42የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ነው፡፡ ማርያም በጣም ትክክል የሆነውን ምርጫ መርጣለች፣ ይህም ደግሞ ከእርሷ አይወሰድባትም›› ብሎ መለሰላት፡፡