መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ ለሕዝቡ የሚናገረውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።
2እጅግ የሚወደውና ሞት አፋፍ ላይ የደረሰ አገልጋይ የነበረው አንድ የመቶ አለቃ ነበረ።
3ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ መጥቶ አገልጋዩን ከመሞት እንዲያድንለት እንዲለምኑት የአይሁድ ሽማግሌዎችን ወደ እርሱ ላካቸው።
4እነርሱ ወደ ኢየሱስ በቀረቡ ጊዜ፣ "ለእርሱ ይህን ልታደርግለት የተገባ ነው፣
5ምክንያቱም ሕዝባችንን ይወዳል፣ ምኩራብ የሠራልንም እርሱ ነው" በማለት አጥብቀው ለመኑት።
6ስለዚህ ኢየሱስ ዐብሮአቸው መንገዱን ቀጠለ። ነገር ግን ወደ ቤቱ ለመድረስ ጥቂት በቀረው ጊዜ፣ የመቶ አለቃው፣ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት ወዳጆቹን ወደ ኢየሱስ ላካቸው፤ “ጌታ ሆይ፣ አትድከም፣ ምክንያቱም አንተ ወደ ቤቴ ልትገባ የተገባሁ አይደለሁም፤
7ከዚህ የተነሣ እኔም ራሴ ወደ አንተ ለመምጣት የምገባ አድርጌ እንኳ ራሴን አልቈጥረውም። ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር አገልጋዬ ይፈወሳል፤
8እኔም ደግሞ ባለ ሥልጣን ነኝና፤ በእኔ ሥር ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን 'ሂድ' ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን 'ና' ስለው ይመጣል።
9ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ በመቶ አለቃው ተደንቀ፣ ይከተሉት ወደነበሩት ሰዎችም ዞር ብሎ፣ “በእስራኤልም እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው ሰው አላገኘሁም” አላቸው።
10ከዚያም የተላኩት ሰዎች ወደ መቶ አለቃው ቤት ተመልሰው፣ አገልጋዩን ጤናማ ሆኖ አገኙት።
11ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ናይን ወደ ምትባል ከተማ እየተጓዘ ነበር። ከእርሱም ጋር ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብ ዐብረውት ይሄዱ ነበር።
12ወደ ከተማይቱም በቀረበ ጊዜ፣ እነሆ፣ ለእናቱ ብቸኛ ልጅ የነበረ ሰው ሞቶ አስከሬኑን ሰዎች ተሸክመው እየሄዱ ነበር። የልጁ እናት መበለት ነበረች፤ በርከት ያሉ ለቀስተኞችም ተከትለዋት ነበር።
13ጌታም ተመልክቷት እጅግ ዐዘነላትና፣ “አታልቅሺ” አላት።
14ከዚያም ወደ ቃሬዛው ተጠግቶ ነካው ቃሬዛውን የተሸከሙትም ቆሙ። ኢየሱስ፣ “አንተ ወጣት ተነሥ እልሃለሁ” አለ።
15ወጣቱም ተነሥቶ መናገር ጀመረ፤ ከዚያም ኢየሱስ ልጁን ለእናትዮዋ ሰጣት።
16ከዚያም ሁሉንም ፍርሀት ያዛቸው። “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነሥቶአል" "ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጎበኝቶአል” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
17ይህ የኢየሱስ ዝና በመላው ይሁዳና በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተሰማ።
18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አወሩለት።
19ከዚያም ዮሐንስ፣ “የምትመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው እንዲጠይቁት ከእነርሱ ሁለቱን ወደ ኢየሱስ ላካቸው።
20ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ "'የምትመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌ እንጠብቅ?' ብለን እንድንጠይቅህ መጥምቁ ዮሐንስ ልኮናል" አሉ።
21በዚያኑ ሰዓት ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከተለያየ ደዌና በሽታ ፈወሰ። በአጋንንት የተያዙትን ነጻ አወጣ፣ ዐይነ ስውራንም ማየት እንዲችሉ አደረገ።
22ኢየሱስ መልእክተኞቹን፣ “ወደ ዮሐንስ ተመልሳችሁ ሂዱና ያያችሁትንና የሰማችሁትን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፣ ዐይነ ስውራን ያያሉ፣ ሽባዎች ይራመዳሉ፣ ለምጻሞች ይነጻሉ፣ መስማት የተሳናቸው ይሰማሉ፣ ሙታን ይነሣሉ፣ ለድኾችም ወንጌል እየተሰበከ ነው።
23በማደርጋቸው ነገሮች በእኔ ሳይሰናከል በእምነቱ የሚጸና ሰው የተመሰገነ ነው” አላቸው።
24የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ እንዲህ ይላቸው ጀመር፣ “ምን ልታዩ ወደ በረሐ ወጣችሁ በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን?
25ወይስ የወጣችሁት የሚያማምሩ ልብሶች የለበሱትን ለማየት ነውን? እነሆ፣ የሚያማምሩ ልብሶችን ለብሰው በድሎት የሚኖሩ ሰዎች የሚገኙት በአብያተ መንግሥታት ነው።
26ልታዩ የወጣችሁት ግን ነቢይን ከሆነ፣ እንግዲያውስ ያያችሁት ነቢይን ብቻ ሳይሆን ከነቢያትም የበለጠውን ነው።
27ስለ እርሱ፣ ‘እነሆ፣ በፊታችሁ መንገድን የሚጠርግ መልእክተኛዬን እልካለሁ’ ተብሎ ተጽፏል።
28እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ ቢሆንም በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉም የሚያንሰው ይበልጠዋል።
29ይህን በሰሙ ጊዜ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔር ጻድቅ እንደ ሆነ ተናገሩ፤ ምክንያቱም እነርሱን ያጠመቃቸው ዮሐንስ ነበር።
30በዮሐንስ ያልተጠመቁት ፈሪሳውያንና የአይሁድ የሕግ ዐዋቂዎች ግን በራሳቸው ፈቃድ የእግዚአብሔርን ጥበብ ተቃወሙ።
31እንግዲያውስ የዚህን ትውልድ ሰዎች ከምን ጋር አመሳስላቸዋለሁ? ምንስ ይመስላሉ?
32እርስ በርሳቸው በገበያ እየተጠራሩ፥ ‘እንቢልታ ነፋንላችሁ እናንተም አልዘፈናችሁም፣ ሙሾ አወጣንላችሁ እናንተም አላለቀሳችሁም’ እንደሚባባሉ ልጆች ናቸው።
33መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላና ወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ‘ጋኔን አለበት’ አላችሁት፣
34የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፦ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ!’ አላችሁት።
35ጥበብ ግን በልጆቿ ሁሉ ትክክል እንደ ሆነች ታወቀች።
36አንድ ፈሪሳዊም በቤቱ ዐብሮት እንዲመገብ ኢየሱስን ጋበዘው ኢየሱስ ግብዣውን ተቀብሎ ወደ ማዕዱ ቀረበ።
37እነሆ፣ በዚያ ከተማ በመጥፎ ምግባሯ የታወቀች እንዲት ሴት ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት ተጋብዞ በማዕድ እንደ ተቀመጠ ተረድታ የአልባስጥሮስ ሽቱ ብልቃጥ ይዛ ወደ ቤቱ ገባችና
38ከኢየሱስ በስተኋላ ከእግሩ አጠገብ ቆማ ማልቀስ ጀመረች። ከዚያም በእንባዋ እግሩን ማራስና በፀጉሯም ማበስ ቀጠለች፣ እግሩንም ትስመው በሽቱም ትቀባው ነበር።
39ኢየሱስን የጋበዘው ፈሪሳዊ ይህንን ባየ ጊዜ፣ "ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ ቢሆን ኖሮ እየነካችው ያለችው ሴት ምን ዓይነት ሴት እንደ ሆነች ባወቀም ነበር" ብሎ በልቡ ዐሰበ።
40ኢየሱስም መልሶ ፈሪሳዊውን፣ “አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። ፈሪሳዊውም፣ “መምህር ሆይ፣ ተናገር” አለው።
41ኢየሱስ፣ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፣ አንደኛው የአምስት መቶ ዲናር ሌላኛው ደግሞ የሃምሳ ዲናር ዕዳ ነበረባቸው፤
42የሚከፍሉት ስላልነበራቸው ሁለቱንም ዕዳቸውን ማራቸው። ስለዚህ ዕዳቸው ከተማረላቸው ከእነዚህ ከሁለቱ ማንኛቸው አብዳሪውን የበለጠ የሚወደው ይመስልሃል? አለው።
43ስምዖንም መልሶ፣ “ብዙ የተተወለቱ ይመስለኛል” አለው። ኢየሱስ፣ “በትክክል መልሰሃል” አለው።
44ኢየሱስም ወደ ሴትዮይቱ ዞር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፣ “ይህችን ሴት ትመለከታታለህ? እኔ ወደ ቤትህ ገብቼ ለእግሬ ውሃ እንኳን አላቀረብህልኝም፣ እርሷ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፣ በፀጉሯም አበሰችው፤
45አንተ አልሳምኸኝም፣ እርሷ ግን ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።
46አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፣ እርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች፣
47ስለዚህ ለበዛው ኃጢአቷ ብዙ ምሕረትን አግኝታለችና አብዝታ ወዳለች። ጥቂት ኃጢአቱ ይቅር የተባለለት ግን ጥቂት ይወዳል” አለው።
48ከዚያም ወደ ሴቱቱ ዞር ብሎ፣ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት።
49በዚያም ተቀምጠው የነበሩት እርስ በርሳቸው፣ “ኃጢአትን ይቅር የሚል ይህ ማን ነው?” አሉ።
50ከዚያም ኢየሱስ ሴቲቱን፣ “እምነትሽ አድኖሻል። በስላም ሂጂ” አላት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።