መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል በሚያልፍበት ጊዜ ደቀመዛሙርቱ እሸት እየቀጠፉና በእጆቻቸው እያሹ እህሉን ይቅሙ ነበር፡፡
2ገር ግን ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “በሰንበት ቀን ማድረግ ያልተፈቀደውን የምታደርጉት ለምንድን ነው?” አሏቸው፡፡
3ኢየሱስም ለእነርሱ፣ “ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ያደረጉትን እንኳ አላነበባችሁምን?
4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከተቀደሰው ኅብስት ጥቂት ወሰደ፤ ካህናትም ብቻ ይበሉ ዘንድ የተፈቀደላቸውን ለራሱ በላ። አብረውት ከነበሩትም ለአንዳንዶቸ ይበሉ ዘንድ ሰጣቸው” አላቸው፡፡
5ከዚያ በኋላም፣ “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው” አላቸው፡፡
6በሌላም ሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገብቶ በዚያ የነበሩትን ሰዎች አስተማራቸው፡፡ በዚያም የቀኝ እጁ የሰለለች አንድ ሰው ነበረ፡፡
7አንድ የተሳሳተ ነገር ሲያደርግ ተመልክተው ለመክሰስ ምክንያት ያገኙ ዘንድ በሰንበት ቀን አንድን ሰው ይፈውስ እንደሆነ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት በትኩረት ይመለከቱት ነበር፡፡
8እርሱ ግን ምን እንደሚያስቡ አውቆ፣ እጁ የሰለለችበትን ሰውዬ፣ “ተነሣና በሰዎች ሁሉ መካከል ቁም” አለው፡፡ ስለዚህም ሰውዬው ተነሣና በዚያ ስፍራ ቆመ፡፡
9ኢየሱስም፣ “ እኔም እናንተን እጠይቃችኋለሁ፡- በሰንበት ሕጋዊ የሚሆነው መልካም ማድረግ ነው ክፉ፣ ሕይወት ማድን ነው ወይስ ማጥፋት?”
10ከዚያም ዞር ብሎ ሁሉንም ተመለከታቸውና ለሰውዬው፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ዘረጋውም፣ እጁም ዳነለት፡፡
11ከዚያ በኋላም በቁጣ ተሞልተው፣ በኢየሱስ ላይ ምን እንደሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፡፡
12በዚያም ወቅት ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፣ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መጸለዩን ቀጠለ፡፡
13በነጋም ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፣ ከእነርሱም ‘ሐዋርያት’ ብሎ የሰየማቸውን አሥራ ሁለቱን መረጠ፡፡
14የሐዋርያቱም ስም፣ ስምዖን (ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው) ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሚዎስ፣
15ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ ያዕቆብ የእልፍዮስ ልጅ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፣
16የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ከዳተኛ የሆነው ይሁዳ አስቆሮቱ ናቸው፡፡
17ከዚያ በኋላም ኢየሱስ ከተራራው ወረደና በደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፡፡ ከደቀመዛሙርቱ በርከት ያሉት፣ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርቻ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፡፡
18ወደዚያ የመጡት እርሱን ሊያዳምጡትና ከበሽታዎቻቸው ሊፈወሱ ነበር፡፡ በርኩሳን መናፍስት ሲጨነቁ የነበሩም ሰዎች ተፈወሱ፡፡
19የሚፈውስ ኃይል ከእርሱ ይወጣ ስለነበረ፣ በሕዝቡ መካከል ያለ እያንዳንዱ ሰው እርሱን ለመንካት ጥረት ያደርግ ነበር፤ እርሱም ሁሉንም ፈወሳቸ.
20ከዚያ በኋላም ወደ ደቀመዛሙርቱ ተመለከተና፣ እንደዚህ አላቸው፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት ለእናንተ ናትና፣ እናንተ ድሆች የተባረካችሁ ናችሁ፡፡
21አሁን የምትራቡ የተባረካችሁ ናችሁ፣ ትጠግባላችሁና፡፡ አሁን የምታለቅሱ የተባረካችሁ ናችሁ፣ ትስቃላችሁና፡፡
22ሰዎች በሚጠሏችሁና በሚያገሏችሁ ጊዜ እንደዚሁም በሰው ልጅ ምክንያት ስማችሁን በክፉ ሲያነሱ የተባረካችሁ ናችሁ፡፡
23አባቶቻቸው ነቢያትን እንደዚሁ አድርገውባቸው ነበርና ፣ በዚያን ቀን ሐሴት አድርጉ፣ በደስታም ዝለሉ፣ ምክንያቱም በሰማይ በእርግጥ ታላቅ ብድራት ይኖራችኋል፡፡
24እናንተ አሁኑኑ መጽናናትን ተቀብላችኋልና፣ ነገር ግን እናንተ ባለጠጎች ወዮላችሁ!
25በኋላ ትራባላችሁና፣ እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! በኋላ ስለምታለቅሱና ዋይ፣ ዋይ ስለምትሉ፣ እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ!
26ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም በሚናገሩላችሁ ጊዜ ወዮላችሁ! ምክንያቱም አባቶቻቸው ለሐሰተኛ ነቢያት እንደዚያ ያደርጉላቸው ነበርና፡፡
27ለእናንተ ለምታደምጡ ግን እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉላቸው፡፡
28የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚያንገላቷችሁም ጸልዩላቸው።
29አንድ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውንም ጉንጭህን አዙርለት፡፡ አንድ ሰው ነጠላህን የሚወስድብህ ከሆነ፣ እጀ ጠባብህን አትከልክለው፡፡
30ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፣ አንድ ሰው የአንተ የሆነውን የሚወስድብህ ከሆነ፣ እንዲመልስልህ አትጠይቀው፡፡
31ሰዎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን ሁሉ አንተም ለእነርሱ ልታደርግላቸው ይገባሃል፡፡
32ኃጢአተኞችም እንኳን የሚወዷቸውን ይወዳሉና የሚወዷችሁን የምትወዱ ከሆነ፣ ምን ምስጋና ትቀበላላችሁ?
33ኃጢአተኞችም እንደዚያው ያደርጋሉና መልካም ለሚያደርጉላችሁ ብቻ መልካም የምታደርጉ ከሆናችሁ፣ ምን ምስጋና ትቀበላላችሁ?
34እንደሚመልሱላችሁ ለምትጠብቋቸው ብቻ የምታበድሩ ከሆናችሁ፣ ምን ምስጋና አላችሁ? የሰጡትን ያንኑ ያህል ለመቀበል ተስፋ አድርገው፣ ኃጢአተኞችም እንኳን ለኃጢአተኞች ያበድራሉ፡፡
35ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ መልካምም አድርጉላቸው፤ ምንም ነገር ስለመቀበል ሳትጨነቁ አበድሯቸው፣ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፡፡ እርሱ ራሱ ለማያመሰግኑና ለክፉ ሰዎች ቸር ነውና፣ እናንተም የልዑል ልጆች ትባላላችሁ፡፡
36አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ፡፡
37አትፍረዱ አይፈርድባችሁም፤ አትኮንኑ አትኮነኑምም፤ ሌሎችን ይቅር በሉ፣ እናንተም ይቅር ትባላላችሁ፡፡
38ለሌሎች ስጡ፣ ለእናንተም የተጠቀጠቀ፣ የተነቀነቀ፣ በእቅፎቻችሁም ተርፎ የሚፈስ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ ይሰጣችኋል፡፡ ለሌሎች ለመስፈር በምትጠቀሙበት በዚያው መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፡፡"
39ከዚያም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፣ በኋላም፣ “አንድ ዕውር ሌላውን ዕውር ሊመራው ይችላልን? እንደዚያ ቢያደርግ፣ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይገቡ የለምን?
40ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን አንድ ሰው ፈጽሞ ከተማረ እንደ መምህሩ ይሆናል፡፡
41በወንድምህ ዓይን ያለውን ትንሽ ጉድፍ ለምን ትመለከታለህ? ለምንስ በራስህ ዓይን ያለውን ግንድ አትመለከትም? በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣
42ለወንድምህ፣ ‘ወንድሜ ሆይ፣ ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! በመጀመሪያ በዓይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፣ ከዘያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ፡፡
43የተበላሸ ፍሬ የሚያፈራ መልካም ዛፍ የለምና፣ መልካም ፍሬም የሚያፈራ የተበላሸ ዛፍ የለም፡፡
44እያንዳንዱ ዛፍ የሚታወቀው በሚያፈራው ፍሬ ነውና፤ ከእሾህ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፣ ከቀጋ ቁጥቋጦም የወይን ፍሬ አይቆረጥም፡፡
45መልካሙ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ሀብት መልካም የሆነውን ነገር ያወጣል፤ ክፉም ሰው በልቡ ካከማቸው ክፉ ክምችት ክፉ የሆነውን ያወጣል፡፡ በልቡ ሞልቶ ከተረፈው በአፉ ይናገራልና፡፡
46ለምንስ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ? ለምናገራቸውስ ነገሮች ለምን አትታዘዙም?
47ወደ እኔ የሚመጣና ለቃሌ የሚታዘዝ ምን እንደሚመስል እነግራችኋለሁ እነግራችኋለሁ፣
48መሬቱን በጥልቁ ከቆፈረ በኋላ መሠረቱን በዓለት ላይ በማድረግ ቤቱን እንደሚገነባ ሰው ነው፡፡ ጎርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፣ ሆኖም በሚገባ ተገንብቶ ነበርና አልነቀነቀውም፡፡
49ነገር ግን ቃሌን ሰምቶ የማይታዘዘው ሰው ቤቱን ያለ መሠረት በመሬቱ አፈር ላይ እንደ ሠራው ሰው ነው፤ ጎርፉ በመጣ ጊዜ ቤቱን መታው፣ ወዲያውኑም ፈረሰ፣ ውድም ብሎም ጠፋ፡፡”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።