1ሕዝቡ ከበውት የእግዚአብሔርን ቃል እያዳመጡ ሳሉ፣ ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ሐይቅ ዳር ቆሞ ነበር፡፡
2ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ጥግ በኩል ሲጎተቱ ተመለከተ፡፡ ዓሣ አጥማጆቹ ከጀልባዎቹ ወርደው መረቦቻቸውን እያጠቡ ነበር፡፡
3ኢየሱስ የስምዖን ወደ ነበረችው ከጀልባዎቹ ወደ አንዲቱ ገባና ከምድር ጥቂት ፈቀቅ አድርጎ ወደ ውሃ ውስጥ እንዲያስገባት ጠየቀው፡፡ ከዚያ በኋላም በጀልባዋ ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን ማስተማር ጀመረ፡፡
4ንግግሩንም በጨረሰ ጊዜ ለስምዖን፣ “ጀልባይቱን ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ አድርጋትና ዓሣ ለማጥመድ መረቦቻችሁን ጣሉ፡፡” አለው፡፡
5ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፣ ሌሊቱን ሁሉ ስንሠራ አደርን ምንም አላጠመድንም፣ ነገር ግን በቃልህ መረቡን እጥላለሁ፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
6ይህንን ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፣ መረቦቻቸውም ሊቀደዱ ደረሱ፡፡
7ስለዚህ እንዲመጡና እንዲረዷቸው በሌላ ጀልባ የነበሩትን ጓደኞቻቸውን በጥቅሻ ጠሩ፡፡ እነርሱም መጥተው ሁለቱንም ጀልባዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው፡፡
8ስምዖን ጴጥሮስ ግን ይህንን በተመለከተ ጊዜ በኢየሱስ ጉልበት ሥር ዝቅ ብሎ በመንበርከክ፣ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው፡፡
9እንደዚህም ያለው ስላጠመዷቸው ዓሣዎች እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተደንቀው ስለነበረ ነው፡፡
10በዚያም ከነበሩት መካከል የዘብዴዎስ ልጆች ዮሐንስና ያዕቆብ አብረውት ነበሩ፡፡ ኢየሱስም ለስምዖን፣ “ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህና፣ አትፍራ፡፡” አለው፡፡
11ጀልባቸውን ወደ ምድር ባመጧት ጊዜ ሁሉንም ትተው ተከተሉት፡፡
12ከከተማዎቹ በአንዲቱ በነበረ ጊዜ፣ መላ ሰውነቱ በለምጽ የተመታ ሰው በዚያ ነበረ፡፡ ኢየሱስንም ባየ ጊዜ በፊቱ ወድቆ፣ “ብትፈቅድስ፣ ልታነጻኝ ትችላለህ፡፡” ብሎ ለመነው፡፡
13በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ለምጹ ከእርሱ ተወገደ፡፡
14ለማንም እንዳይነግር አስጠነቀቀው፣ ነገር ግን፣ “ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ፣ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ለእነርሱ ምስክር ይሆን ዘንድ ለመንጻትህ መሥዋዕት አቅርብ፡፡” አለው፡
15ነገር ግን ስለ እርሱ ያለው ዝና ከዚያም ርቆ ወጣ፤ ብዙም የሕዝብ አጀብ ሲያስተምር ለመስማትና ከሕመሞቻቸው ለመፈወስ በአንድነት ወደ እርሱ መጡ፡፡
16እርሱ ግን ወደ ገለልተኛ ስፍራዎች ሄዶ በዚያ ይጸልይ ነበር፡፡
17ያስተምር ከነበረባቸውም ከእነዚያ በአንዱ ቀን ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችና አውራጃዎች እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ከተማ መጥተው በዚያ የተቀመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ነበሩ፡፡ ይፈውስም ዘንድ የእግዚአብሔር ኃይል በእርሱ ላይ ነበረ፡፡
18በዚያን ጊዜ ጥቂት ሰዎች ሰውነቱ የደነዘዘ ሰው በቃሬዛ ይዘው መጡ፤ በኢየሱስ ፊትም ያደርጉት ዘንድ ወደ ውስጥ የሚያስገቡበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፡፡
19ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያስገቡ የሚችሉበትን መንገድ አላገኙም፤ ስለዚህ ወደ ቤቱ ጣሪያ ላይ ወጥተው፣ ሰውዬውን በቃሬዛው ላይ እንዳለ በጣሪያው አሳልፈው በሰዎቹ መካከል ከኢየሱስ ፊት አወረዱት፡፡
20ኢየሱስ እምነታቸውን ተመልክቶ፣ “አንተ ሰው፣ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው፡፡
21ፈሪሳውያንና ጸሐፍት፣ “የስድብ ቃል የሚናገር ይህ ማን ነው? እግዚአብሔር ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣ ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል ማን ነው?” በማለት መጠየቅ ጀመሩ፡፡
22ነገር ግን ኢየሱስ ምን እንዳሰቡ አውቆ፣ “በልባችሁ ይህንን ለምን ትጠይቃላችሁ?
23የትኛውን ማለት ይቀላል፡- ‘ኃጢአትህ ተሰረየችልህ’ ማለት ወይስ ‘ተነሣና ሂድ’ ማለት?
24ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፣ ለአንተ፣ ‘ተነሣና ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ’ ብዬ እናገራለሁ፡፡"
25ከዚያ በኋላ በእነርሱ ፊት ተነሣ፣ ተኝቶበት የነበረውንም ቃሬዛ ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያከበረ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
26ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፣ እግዚአብሔርንም አከበሩ፡፡ “በዛሬው ዕለት ያልተለመደ ነገር አየን” እያሉ በፍርሃት ተሞሉ፡፡
27እነዚህ ነገሮች ከሆኑ በኋላ፣ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ በቀረጥ መሰብሰቢያው ስፍራ ተቀምጦ የነበረውን ሌዊ የተባለውን ቀረጥ ሰብሳቢ ተመለከተ፡፡ እርሱንም፣ “ተከተለኝ” አለው፡፡
28ስለዚህ ሌዊ ሁሉንም ትቶ ተነሥቶ ተከተለው፡፡
29ከዚያ በኋላ፣ ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፣ በዚያም ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና በማዕድ ቀርበው ከእነርሱ ጋር የሚመገቡ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ፡፡
30ነገር ግን ፈሪሳውያንና ጻሐፍት በደቀመዛሙርቱ ላይ፣ “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከሌሎች ኃጢአተኛ ሰዎች ጋር ለምን ትበላላችሁ ትጠጣላችሁም?” እያሉ ያጉረመርሙባቸው ነበር፡፡
31ኢየሱስም እንደዚህ በማለት መለሰላቸው፣ “በመልካም ጤንነት ላይ ያሉ ሐኪም አያስፈልጋቸውም፣ ሐኪም የሚያስፈልጋቸው የታመሙ ብቻ ናቸው፡፡
32እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ለንስሐ ለመጥራት ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ለመጥራት ነው፡፡”
33እነርሱም ፣ “የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ይጾማሉ ይጸልያሉም፣ የፈሪሳውያን ደቀመዛሙርትም እንደዚሁ ያደርጋሉ፡፡ የአንተ ደቀመዛሙርት ግን ይበላሉ፣ ይጠጣሉም፡፡” አሉት፡፡
34ኢየሱስም ፣ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎቹን እንዲጾሙ ሊያደርጋቸው የሚችል አለን?
35ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወቅት ይመጣል በእነዚያ ቀናት ይጾማሉ፡፡”
36ከዚያ በኋላ ኢየሱስ በምሳሌ ተናገራቸው፣ “ማንም ሰው ከአዲስ ልብስ ላይ እራፊ ቀዶ አሮጌ ልብስ አይጥፍም፡፡ እንደዚህ የሚያደርግ ከሆነ፣ ከአዲሱ ልብስ ላይ እራፊ ይቀዳል፣ ነገር ግን ከአዲሱ ልብስ ላይ የተቀደደው እራፊ ከአሮጌው ልብስ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡
37እንደዚሁም፣ ማንም ሰው በአሮጌው አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አያስቀምጥም፡፡ እንደዚህ ቢያደርግ፣ አዲሱ ወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፣ ወይን ጠጁም ይፈሳል፣ አቁማዳውም ይበላሻል፡፡
38ነገር ግን አዲስ ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ይቀመጣል፡፡
39ማንም ሰው አሮጌውን ወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ አዲሱን የወይን ጠጅ አይፈልግም፣ ‘አሮጌው ይሻላል’ ይላልና፡፡”