መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያ በኋላ፣ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተመለሰ፤ መንፈስም ወደ ምድረ-በዳ መራው፡፡
2በዚያም ለአርባ ቀናት በዲያብሎስ ተፈተነ፡፡ በእነዚያም ቀናት ምንም አልበላም፣ ያም ወቅት በተጠናቀቀ ጊዜ ተራበ፡፡
3ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው፡፡
4ኢየሱስም፣ “’ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
5ከዚያ በኋላም ዲያብሎስ ከፍ ወዳለ ስፍራ ወሰደውና፣ በቅጽበት የዓለም መንግሥታትን ሁሉ አሳየው፡፡
6ዲያብሎስም ለእርሱ፣ “እነዚህን ሁሉ መንግሥታት ከክብራቸው ሁሉ ጋር እንድትገዛ እኔ ሥልጣን እሰጥሃለሁ፤ ይህንን ማድረግ የምችለው እገዛቸው ዘንድ ለእኔ ስለተሰጡኝ ነው፣ እኔም ለምፈልገው ለማንኛውም ሰው ልሰጣቸው እችላለሁ፡፡
7ስለዚህ በፊቴ ብትሰግድልኝና ብታመልከኝ፣ ይሄ ሁሉ የአንተ ይሆናል አለው።
8ኢየሱስ ግን እንደዚህ ብሎ መለሰለት፣ “’እግዚአብሔር አምላክህን አምልክ፣ እርሱንም ብቻ አገልግል’ ተብሎ ተጽፎአል፡፡”
9ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደሱ ሕንፃ እጅግ ከፍተኛ ስፍራ አቆመውና፣
10“’ይጠብቁህና ይንከባከቡህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል’
11ደግሞም፣ ‘እግርህም ከድንጋይ ጋር እንዳይጋጭ በእጆቻቸው ወደ ላይ ይይዙሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ራስህን ከዚህ ላይ ወርውር፡፡” አለው፡፡
12ኢየሱስም፣ “’እግዚአብሔር አምላክህን መፈታተን የለብህም’ ተብሎአል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
13ዲያብሎስም ኢየሱስን መፈተኑን ባበቃ ጊዜ፣ እስከ ሌላ ጊዜ ድረስ ትቶት ሄደ፡፡
14ከዚያ በኋላ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ በዚያ አካባቢ በነበሩት ስፍራዎች ሁሉ የእርሱ ዝና ተሰራጨ፡፡
15በምኩራቦቻቸው አስተማረ፣ ሰዎችም ሁሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡
16አንድ ቀንም ወዳደገበት ከተማ ወደ ናዝሬት መጣ፡፡ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል ያነብ ዘንድ ቆመ፡፡
17የነቢዩ የኢሳይያስ የመጽሐፍ ጥቅልል ተሰጥቶት ስለነበረ፣ ጥቅልሉን ሲከፍተው፣
18“ለድሆች የምሥራቹን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለምርኮኞች ነፃነትን፣ ለዕውሮች ብርሃናቸው እንደሚመለስላቸው ፣ የተጨቆኑትም መፈታትን እንደሚያገኙ
19የእግዚአብሔርን የሞገስ ዓመት ዐውጅ ዘንድ ልኮኛል፡፡” የሚለውን ስፍራ አገኘ፡፡
20ከዚያ በኋላ የመጽሐፉን ጥቅልል ዘጋና ለምኩራቡ አገልጋይ ሰጥቶ ተቀመጠ፡፡
21“እናንተ እየሰማችሁ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ተፈጸመ፡፡” እያለ ሊነግራቸው ጀመረ፡፡
22በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ የተናገረውን አስተዋሉ፣ ከአንደበቱም በሚወጣው የጸጋ ቃል ሁሉም ተገረሙ፡፡ እነርሱም፣ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ነው፣ አይደለም እንዴ?” ይሉ ነበር፡
23ኢየሱስም፣ “በእርግጥ ‘ሐኪም ሆይ፣ ራስህን አድን፤ በቅፍርናሆም እንደምታደርግ የሰማነውን በዚህም በትውልድ ከተማህ አድርግ’ የሚለውን ይህንን ምሳሌ ትመስሉብኛላችሁ፡፡”
24ደግሞም እንደዚህ አላቸው፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ማንኛውም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም፡፡
25ነገር ግን እኔ እውነት እላችኋለሁ፣ ለሦስት ዓመታት ተኩል ሰማይ ተዘግቶ ዝናብ ባልነበረበትና በምድሪቱም ሁሉ ረሃብ በነበረበት በኤልያስ ዘመን በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፡፡
26ነገር ግን ኤልያስ በሲዶና አጠገብ በሰራፕታ ትኖር ወደነበረችው መበለት ብቻ እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱም አልተላከም፡፡
27በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፣ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንዳቸውም አልተፈወሱም፡፡”
28በምኩራብ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ በቁጣ ተሞሉ፡፡
29ተነሥተው ከከተማይቱ እንዲወጣ አስገደዱት፣ ከገደል ጫፍም ገፍትረው ይጥሉት ዘንድ ከተማይቱ ወደ ተመሠረተችበት ወደ ኮረብታው ጫፍ ገፍተው ወሰዱት።
30ነገር ግን በመካከላቸው አልፎ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
31ከዚያ በኋላም በገሊላ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሄደ፡፡
32በሥልጣን ይናገር ስለነበረ፣ በትምህርቱ ተገረሙ፡፡
33በዚያን ቀን በምኩራብ ውስጥ ርኩስ መንፈስ የነበረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡
34“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፣ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንክ አውቄሃለሁ፣ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፡፡”
35ኢየሱስም ጋኔኑን፣ “ፀጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው፡፡ ጋኔኑ በሰዎቹ መካከል በጣለው ጊዜ፣ ምንም ጉዳት ሳያደርስበት ከእርሱ ወጣ፡፡
36ሰዎች ሁሉ በጣም ተደነቁ፣ እርስ በርሳቸውም ስለሆነው ነገር መነጋገር ቀጠሉ፡፡ እነርሱም፣ “እነዚህ እንዴት ያሉ ቃላት ናቸው? ርኩሳን መናፍስትን በሥልጣንና በኃይል ያዛቸዋል፣ እነርሱም ይወጣሉ፡፡”
37የእርሱም ዝና በአካባቢው ባሉት አውራጃዎች በማንኛውም ስፍራ ወጣ፡፡
38ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከምኩራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ፡፡ በዚያን ጊዜ የስምዖን አማት በከፍተኛ ትኩሳት ታማ ነበር፣ እነርሱም ስለ እርሷ ተማፀኑት፡፡
39ስለዚህ በአጠገብዋ ቆሞ ትኩሳቱን ገሠጸው፣ ትኩሳቱም ቆመ፡፡ ወዲያውኑም ተነሥታ ልታገለግላቸው ጀመረች፡፡
40ፀሐይም በጠለቀች ጊዜ ሰዎች በተለያዩ ደዌዎች የተያዙትን በሽተኞች ወደ እርሱ አመጡ፡፡ እርሱም እጆቹን በእያንዳንዳቸው ላይ ጭኖ ፈወሳቸው፡፡
41አጋንንትም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” እያሉ በመጮኽ ከብዙዎች ወጡ፡፡ ኢየሱስ አጋንንትን ገሠጻቸው፣ እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፣ ምክንያቱም እርሱ ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና፡፡
42ንጋትም በሆነ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ሄደ፡፡ ብዙ የሕዝብ አጀብ እየፈለጉት ነበርና፣ እርሱ ወደነበረበት ስፍራ መጡ፡፡ እነርሱንም ትቷቸው እንዳይሄድ ሊያስቀሩት ሞከሩ፡፡
43እርሱ ግን እንደዚህ አላቸው፣ “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ለብዙ ከተሞች መስበክ ይገባኛል፣ ምክንያቱም ወደዚህ የተላክሁት ለዚህ ነው፡፡”
44ከዚያ በኋላ በመላው ይሁዳ ባሉት ምኩራቦች መስበኩን ቀጠለ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።