መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 3

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ የአራተኛው ክፍል ገዥ፣ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፈል ገዥ
2እንደዚሁም ሐናና ቀያፋ ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ለዘካርያስ ልጅ ለዮሐንስ በምድረ-በዳ መጣ፡፡
3ለኃጢአት ይቅርታ የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አውራጃ ሁሉ ተመላለሰ፡፡
4ይህም በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ፣ “በምድረ-በዳ የሚጣራ ሰው ድምፅ፣ ‘የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፣ ጎዳናውንም አቅኑ፡፡
5ሸለቆ ሁሉ ይሞላል፣ ተራራውና ኮረብታው ደልዳላ ይሆናል፣ ጠማማው መንገድ ቀና ይሆናል፣ ሸካራውም መንገድ የተመቸ ይሆናል፡፡
6ሰዎችም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያሉ፡፡’”
7ስለዚህ በእርሱ ለመጠመቅ ይመጣ ለነበረው ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ ዮሐንስ እንደዚህ አላቸው፣ “እናንተ የመርዘኛ እባብ ልጆች፣ ሊመጣ ካለው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አስጠነቀቃችሁ?
8ለንስሓ የሚሆን ፍሬ አፍሩ፣ እርስ በርሳችሁም፣ ‘አባታችን አብርሃም አለን’ አትበሉ፣ ምክንያቱም ከእነዚህ ድንጋዮች እንኳን እግዚአብሔር ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት ይችላል፡፡
9መጥረቢያ በዛፎች ግንድ ሥር ተቀምጦአል፤ ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ውስጥ ያጣላል፡፡”
10ከዚያ በኋላ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች እንደዚህ ብለው ጠየቁት፣ “እንግዲህ ምን እናድርግ?”
11እርሱም እንደዚህ ብሎ መለሰላቸው፣ “አንድ ሰው ሁለት ልብስ ካለው ምንም ለሌለው ለሌላ ሰው ይስጠው፤ ትርፍ ምግብ ያለውም እንደዚሁ ያድርግ፡፡”
12ከዚያ በኋላም አንዳንድ ቀረጥ ሰብሳቢዎች ለመጠመቅ መጡና እንደዚህ አሉት፣ “መምህር ሆይ፣ እኛስ ምን ማድረግ ይገባናል?”
13እርሱም እንደዚህ አላቸው፣ “መሰብሰብ ከሚገባችሁ ገንዘብ በላይ አትሰብስቡ፡፡”
14አንዳንድ ወታደሮችም እንደዚህ ብለው ጠየቁት፣ “እኛስ፣ ምን ማድረግ ይገባናል?” እርሱም እንደዚህ አላቸው፣ “ከማንም ላይ አስገድዳችሁ ገንዘብ አትውሰዱ፣ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፡፡ የምታገኙትም ደመወዝ ይብቃችሁ፡፡”
15ሕዝቡ የክርስቶስን መምጣት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ ሰዎች ሁሉ በልባቸው እርሱ ክርስቶስ ይሆን እያሉ ስለ ዮሐንስ ይደነቁ ነበር፡፡
16እንደዚህ በማለት ዮሐንስ ለሁሉም መልስ ሰጣቸው፣ “እኔ በበኩሌ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፣ የጫማውን ማሠሪያ መፍታት እንኳን የማይገባኝ ከእኔ ይልቅ ብርቱ የሆነ ይመጣል፡፡ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡
17አውድማውን ፈጽሞ ያጠራውና ስንዴውን ወደ ጎተራ ያስገባ ዘንድ የሚያበራይበት መንሽ በእጁ ነው፡፡ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፡፡”
18ሌሎች ብዙ ምክሮችንም በመምከር፣ የምሥራቹን ቃል ለሕዝቡ ሰበከላቸው፡፡
19የወንድሙን ሚስት ሄሮዳይዳን ስላገባና ስላደረጋቸውም ሌሎች ክፉ ሥራዎች የአራተኛው ክፍል ገዥ የነበረውን ሄሮድስንም ገሰጸው፡፡
20ሄሮድስ ግን ከዚህም የባሰ ክፉ ሥራ ሠራ፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶ ቆለፈበት፡፡
21ሰዎች ሁሉ በዮሐንስ እየተጠመቁ ሳሉ፣ ኢየሱስም ደግሞ ተጠመቀ፡፡ እየጸለየም ሳለ ሰማያት ተከፈቱ፡፡
22መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በአካል በእርሱ ላይ አረፈ፣ በዚህም ጊዜ ከሰማይ፣ “አንተ፣ ውድ ልጄ ነህ፤ በአንተ እጅግ ደስ ይለኛል፡፡” የሚል ድምፅ መጣ፡፡
23በዚህን ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ማስተማር ሲጀምር ዕድሜው ሰላሳ ዓመት ገደማ ነበር፡፡ (ይገመት እንደነበረው) እርሱ የኤሊ ልጅ የነበረው የዮሴፍ ልጅ
24ኤሊም የማቲ ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣ የሚልኪ ልጅ፣ የዮና ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣
25የማታትዩ ልጅ፣ የአሞጽ ልጅ፣ የናሆም ልጅ፣ የኤሲሊም ልጅ፣ የናጌ ልጅ፣
26የማኦት ልጅ፣ የማታትዩ ልጅ፣ የሰሜይ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዮዳ ልጅ፣
27የዮናን ልጅ፣ የሬስ ልጅ፣ የዘሩባቤል ልጅ፣ የሰላትያል ልጅ፣ የኔር ልጅ፣
28የሚልኪ ልጅ፣ የሐዲ ልጅ፣ የዮሳስ ልጅ፣ የቆሳም ልጅ፣ የኤልሞዳም ልጅ፣ የኤር ልጅ፣
29የዮሴዕ ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ፣ የዮራም ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣
30የስምዖን ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዮናም ልጅ፣ የኤልያቄም ልጅ፣
31የሜልያ ልጅ፣ የማይናን ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣ የናታን ልጅ፣ የዳዊት ልጅ፣
32የእሴይ ልጅ፣ የኢዮቤድ ልጅ፣ የቦዔዝ ልጅ፣ የሰልሞን ልጅ፣ የነአሶን ልጅ፣
33የአሚናዳብ ልጅ፣ የአራም ልጅ፣ የአሮኒ ልጅ፣ የኤስሮም ልጅ፣ የፋሬስ ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣
34የያዕቆብ ልጅ፣ የይስሐቅ ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣ የታራ ልጅ፣ የናኮር ልጅ፣
35የሴሮህ ልጅ፣ የራጋው ልጅ፣ የፋሌቅ ልጅ፣ የአቤር ልጅ፣ የሳላ ልጅ፣
36የቃይንም ልጅ፣ የአርፋክስድ ልጅ፣ የሴም ልጅ፣ የኖኅ ልጅ፣ የላሜህ ልጅ፣
37የማቱሳላ ልጅ፣ የሄኖክ ልጅ፣ የያሬድ ልጅ፣ የመላልኤል ልጅ፣ የቃይናን ልጅ፣
38የሄኖስ ልጅ፣ የሴት ልጅ፣ የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።