1በዚያን ጊዜ አውግስጦስ ቄሣር በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይቆጠሩ ዘንድ ዐዋጅ አወጣ፡፡
2ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዥ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ ነበር፡፡
3ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለሕዝብ ቆጠራው ወደየራሱ ከተማ ሄደ፡፡
4ዮሴፍም የዳዊት ቤተሰብ ዝርያ ስለነበረ በገሊላ ከነበረችው ከናዝሬት ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደምትባለው የይሁዳ ከተማ ወደ ነበረችው ወደ ቤተ ልሔም ተጓዘ፡፡
5ይመዘገብ ዘንድ ለእርሱ ታጭታ ከነበረችውና የመውለጃዋን ቀን እየተጠባበቀች ከነበረችው ከማርያም ጋር ወደዚያ ስፍራ ሄደ፡፡
6እዚያም በነበሩበት ጊዜ የምትወልድበት ወቅት ደረሰ፡፡
7የበኩር ልጅዋ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፣ በመታቀፊያ ጨርቅም በሚገባ ጠቀለለችው፡፡ በእንግዳ መቀበያውም ስፍራ ስላልነበረ በእንስሳት መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛቸው፡፡
8በዚያው አካባቢ በሌሊት የበግ መንጎቻቸውን እየጠበቁ በመስክ የነበሩ እረኞች ነበሩ፡፡
9በድንገትም የእግዚአብሔር መልአክ ለእነርሱ ተገለጠላቸው፣ የእግዚአብሔርም ክብር በእነርሱ ዙሪያ አበራላቸው፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፡፡
10ከዚያ በኋላ መልአኩ፣ “ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች ይዤላችሁ መጥቻለሁና አትፍሩ፡፡
11ዛሬ በዳዊት ከተማ፣ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ክርስቶስ ጌታ ነው፡፡
12ለእናንተም ይህ ምልክት ይሰጣችኋል፣ ሕፃን በመታቀፊያ ጨርቅ ተጠቅልሎ፣ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡”
13በድንገትም ከመልአኩ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣
14“ከፍ ባለ ስፍራ ለሚኖረው ለእግዚአብሔር ክብር፣ በምድርም እርሱ ደስ በሚሰኝባቸው ሕዝቦች መካከል ሰላም ይሁን፡፡” ይሉ ነበር፡፡
15መላእክቱም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በሄዱ ጊዜ፣ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፣ “ወደ ቤተልሔም እንሂድና፣ እግዚአብሔር ለእኛ የገለጠልንን ይህንን የሆነውን ነገር እንመልከት፡፡” ተባባሉ፡፡
16በችኮላ ወደዚያ ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኝዋቸው፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ ተመለከቱት፡፡
17ይህንን ከተመለከቱ በኋላ ስለዚህ ልጅ የተባለውን ለሕዝቡ አስታወቁ፡፡
18ያዳመጡአቸውም ከእረኞቹ በተነገራቸው ነገር ተደነቁ፡፡
19ስለሰማችው ነገር ሁሉ ማርያም እያሰላሰለች በልብዋ ትጠብቀው ነበር፡፡
20ልክ እንደ ተነገራቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ስለ ማንኛውም ነገር እረኞቹ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ፡፡
21ሕፃኑ የሚገረዝበት ስምንተኛው ቀን በደረሰ ጊዜ በማሕፀን ከመፀነሱ በፊት በመልአኩ በተሰጠው ስም ኢየሱስ ብለው ጠሩት፡፡
22በሙሴ ሕግ መሠረት የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርቡት ዘንድ በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ቤተ መቅደሱ
23ይህም፣ “ማሕፀንን የሚከፍት ማንኛውም ወንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ በሕጉ እንደ ተጻፈው ነው፡፡
24በእግዚአብሔር ሕግም በተነገረው መሠረት መሥዋዕት ማለትም ‘ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች’ ያቀርቡ ዘንድ መጡ፡፡
25በኢየሩሳሌምም የሚኖር ስሙ ስምዖን የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ጻድቅና የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚያከብር ነበር፤ ለእስራኤል መጽናኛም የሚሆነውን ይጠባበቅ ነበር፣ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር፡፡
26እግዚአብሔር የቀባውን ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፡፡
27የሕጉ ሥርዓት የሚጠይቀውን ሊያደርጉለት ወላጆቹ ሕፃኑ ኢየሱስን ይዘው በመጡበት ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ፡፡
28ከዚያም ስምዖን በእጆቹ አቅፎት፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነ፣
29“ጌታ ሆይ፣ እንግዲህ፣ ባሪያህን እንደ ቃልህ በሰላም አሰናብተው፣
30ዓይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና
31ይህም ድነት አንተ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፡፡
32እርሱም ለአሕዛብ መገለጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው፡፡”
33የልጁም አባትና እናት ስለ እርሱ እየተነገረ ባለው ነገር ተደነቁ፡፡
34ከዚያ በኋላ ስምዖን ባረካቸውና እናቱን ማርያምን፣ “በጥንቃቄ አድምጪ! ይህ ልጅ በእስራኤል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ምክንያት፣ ክፉም ለተናገሩበት ምልክት የሚሆን ነው፡፡
35የብዙዎች የልባቸው ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ የአንቺም የራስሽ ልብ በሰይፍ የሚወጋ ይሆናል፡፡”
36ሐና የተባለች ነቢይትም በዚያ ነበረች፤ እርሷም ከአሴር ነገድ የሆነ የፋኑኤል ልጅ ነበረች፡፡ ዕድሜዋ እጅግ የገፋ ሲሆን ከጋብቻዋ በኋላ ከባልዋ ጋር ለሰባት ዓመታት ቆይታለች፡፡
37ከዚያ በኋላ ለሰማንያ አራት ዓመታት መበለት ሆና ኖራለች፡፡ ከቤተ መቅደስ በፍጹም ሳትለይ ቀንና ሌሊት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ታመልክ ነበር፡፡
38ልክ በዚያን ሰዓት ወደ እነርሱ መጥታ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመረች፡፡ የኢየሩሳሌምን መቤዠት ለሚጠባበቁ ለማንኛዎቹም ሰዎች ስለ ልጁ ትናገር ነበር፡፡
39እንደ እግዚአብሔር ሕግ እንዲያደርጉ የሚፈለግባቸውን ማንኛውንም ነገር ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ገሊላ ወደ ራሳቸው ከተማ ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡
40ልጁ አደገ፣ ጠነከረ፣ በጥበብም ጨመረ፤ የእግዚአብሔር ጸጋም በ እርሱ ላይ ነበረ፡፡
41ወላጆቹም ለፋሲካ በዓል በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር፡፡
42አሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ በተለመደው ጊዜ እንደገና በዓሉን ለማክበር ሄዱ፡፡
43ለበዓሉ መቆየት ያለባቸውን ሁሉንም ቀናት ከቆዩ በኋላ ወደ ቤታቸው መመለስ ጀመሩ፡፡ ልጁ ኢየሱስ ግን በኢየሩሳሌም ቀረ፣ ወላጆቹም ይህንን አላወቁም ነበር፡፡
44ከእነርሱ ጋር ይጓዙ ከነበሩት መንገደኞች ጋር የነበረ መስሏቸው ስለነበረ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፡፡ ከዚያ በኋላም በዘመዶቻቸውና በወዳጆቻቸው ዘንድ ፈለጉት፡፡
45ባላገኙትም ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው በዚያ ሊፈልጉት ጀመሩ፡፡
46ከሦስት ቀን በኋላ እያዳመጣቸውና ጥያቄዎችን እየጠየቃቸው በመምህራን መካከል ተቀምጦ በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፡፡
47ያዳመጡት ሁሉ በማስተዋሉና በሚሰጣቸው መልሶች ተገረሙ፡፡
48ባዩትም ጊዜ ተደነቁ፡፡ እናቱም እርሱን፣ “ልጄ ሆይ፣ ለምን እንደዚህ አደረግኸን? አድምጠኝ፣ እኔና አባትህ ተጨንቀን አንተን ስንፈልግህ ነበርን” አለችው።
49እርሱም፣ “ለምን ነበር የፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንደሚገባኝ አታውቁምን?”
50ነገር ግን እንደዚያ ሲል ምን ማለቱ እንደነበረ አልገባቸውም፡፡
51ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ጋር ወደ ናዝሬት ተመለሰ፣ ይታዘዝላቸውም ነበር፡፡ እናቱም ይህንን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር፡፡
52ኢየሱስ ግን በጥበብና በሰውነት ቁመና ማደጉን ቀጠለ፣ በእግዚአብሔርና በሰዎችም ፊት ያለው ሞገስ እየጨመረ ሄደ፡፡