1ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር።
2የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተመካከሩ።
3ሰይጣን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ በሆነው በአስቆሮቱ ይሁዳ ገባበት።
4አርሱም ኢየሱስን እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ መሪዎች ጋር ተነጋገረ።
5እነርሱም ደስ አላቸው፣ ገንዘብም ሊሰጡት ተስማሙ።
6እርሱም ኢየሱስን ለእነርሱ አሳልፎ ለመስጠት ሕዝብ የሌሉበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
7የፋሲካ በግ መሥዋዕት የሚደረግበት የቂጣ በዓል ደረሰ።
8ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን፣ “ሂዱና የፋሲካ ምግብ እንድንበላ አዘጋጁልን” ብሎ ላካቸው።
9እነርሱም፣ “የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ብለው ጠየቁት።
10እንዲህም ብሎ መለሰላቸው፣ “አድምጡ፣ ወደ ከተማው በገባችሁ ጊዜ የውሃ እንስራ ተሸክሞ የሚመጣ ሰው ያገኛችኋል። ይህን ሰው ወደሚገባበት ቤት ተከትላችሁ ግቡ።
11ከዚያም ለቤቱ ባለቤት፣ 'መምህሩ እንዲህ ይልሃል፤" የፋሲካን እራት ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የምበላበት የእንግዳ ክፍል የት ነው?' በሉት።”
12እርሱም በፎቁ ላይ ሰፊና በሚገባ የተሰናዳ ክፍል ያሳያችኋል። ዝግጅቱንም በዚያ አድርጉ።
13ስለዚህ ወጥተው ሲሄዱ፣ ሁሉም ነገር እርሱ እንደተናገረው ሆኖ አገኙት። ከዚያም የፋሲካውን ምግብ አዘጋጁ።
14ሰዓቱ ሲደርስ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዐብሮ ተቀመጠ።
15ከዚያም እንዲህ አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን የፋሲካ እራት ከእናንተ ጋር ለመብላት በእጅጉ እጓጓ ነበር።
16በእግዚአብሔር መንግሥት እስከሚፈጸም ድረስ ከዚህ ምግብ ዳግመኛ እንደማልበላ እነግራችኋለሁና።"
17ከዚያም ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነና እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ውሰዱና ተካፈሉት።
18እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ዳግመኛ አልጠጣም።”
19እንጀራውን ወሰደ፣ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ በማለት ቈርሶ ሰጣቸው፣ “ይህ ለእናንተ የተሰጠው ሥጋዬ ነው። እኔን እያሰባችሁ ተመገቡት።”
20በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ከእራት በኋላ ጽዋውን አነሣና እንዲህ አለ፣ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ የፈሰሰ በደሜ የሚሆን ዐዲስ ኪዳን ነው።
21ነገር ግን እኔን አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር በማዕድ እየበላ መሆኑን ልብ በሉ።
22የሰው ልጅስ እንደተወሰነለት ይሆናል። ነገር ግን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!"
23በዚህ ጊዜ እርስ በርሳቸው ይህን ነገር የሚያደርግ ማን እንደ ሆነ ተጠያየቁ።
24ከዚያም ከሁሉም የሚበልጥ ማን ሊሆን እንደሚገባው በመካከላቸው ጠብ ተነሣ። እርሱ እንዲህ አላቸው፣
25“የአሕዛብ ነገሥታት በሕዝብ ላይ ይገዛሉ፣ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውንም የተከበሩ ገዦች ይሏቸዋል።
26ነገር ግን በእናንተ ዘንድ እንዲህ አይሁን። ይልቅ ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ ይሁን። እጅግ ተፈላጊ የሆነ እንደሚያገለግል ሰው ይሁን።
27በማዕድ ከተቀመጠውና ከሚያገለግለው የትኛው ታላቅ ነው? በማዕድ የተቀመጠ አይደለምን? እኔ ግን በእናንተ መካከል እንደሚያገለግል ሰው ነኝ።
28ነገር ግን እናንተ በፈተናዬ ከእኔ ጋር ጸንታችኋል። አብ ለእኔ መንግሥትን እንደ ሰጠኝ፣
29በመንግሥቴ በእኔ ማዕድ እንድትበሉና እንድትጠጡ መንግሥትን እሰጣችኋለሁ።
30ደግሞም በዙፋን ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።
31ስምዖን ሆይ፣ ስምዖን ሆይ፣ ተጠንቀቅ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥርህ ፈልጎ ጠይቋል።
32ነገር ግን እኔ እምነትህ እንዳይጠፋ ጸለይሁልህ። ዳግመኛ ከተመለስህ በኋላ ወንድሞችህን አበርታቸው።”
33ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፣ ወደ እስር ቤትም ይሁን ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ” አለው።
34ኢየሱስ፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ እንደምትክደኝ እነግርሃለሁ” ብሎ መለሰለት።
35ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ገንዘብ ቦርሣ፣ ወይም ያለ ስንቅ ወይም ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ ያጣችሁት ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱ፣ “ምንም አላጣንም" ብለው መለሱለት።
36ከዚያም እንዲህ አላቸው፣ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሣ ያለው ቦርሣውን፣ ደግሞም ስንቁን ይያዝ። ጎራዴ የሌለው ልብሱን ሽጦ ጎራዴ ይግዛ።
37እላችኋለሁ፣ 'ከወንበዴዎች እንደ አንዱ ተቈጠረ' ተብሎ ስለ እኔ የተጻፈው መፈጸም አለበት። ይህ ስለ እኔ የተነገረው አሁን እየተፈጸመ ነው።"
38ከዚያም እነርሱ፣ “ጌታ ሆይ፣ ተመልከት፣ እዚህ ሁለት ጎራዴዎች አሉ” አሉት። እርሱም “ይበቃል” አላቸው።
39ከእራት በኋላ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርገው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
40እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው።
41ከእነርሱ የድንጋይ ውርወራ ያህል ራቅ ብሎ ሄደና ተንበርክኮ፣
42“አባት ሆይ፣ ብትወድ ይህን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፣ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን” በማለት ጸለየ።
43የሚያበረታታው መልአክም ከሰማይ መጣለት።
44በጣር ውስጥ ሆኖ በጣም እየቃተተ ጸለየ፣ ላቡም እንደ ትልልቅ የደም ጠብታዎች ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር።
45ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመጣ ጊዜ ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣
46“ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ” አላቸው።
47ገና እየተናገረ እያለ ብዙ ሰዎች ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ እየመራቸው መጡ። ይሁዳም ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ፤
48ነገር ግን ኢየሱስ፣ “ይሁዳ ሆይ፣ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።
49በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩት እየሆነ ያለውን ነገር ባዩ ጊዜ፣
50“በጎራዴ እንምታቸውን?” አሉ። ከዚያም ከመካከላቸው አንዱ በጎራዴ የሊቀ ካህኑን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ መታና ቈረጠው።
51ኢየሱስ፣ “ይህ ይብቃ” አለ። የአገልጋዩንም ጆሮ ዳሰሰ፣ ፈወሰውም።
52ኢየሱስ ሊያጠቁት ለመጡ የካህናት አለቆችና የቤተ መቅደስ መሪዎች እንዲሁም ሽማግሌዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴን እንደሚይዝ ሰው ጐራዴና ዱላ ይዛችሁ ትመጡብኛላችሁን?
53በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ የእናንተና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።”
54ያዙትና ወሰዱት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤትም አመጡት። ጴጥሮስ ግን ከርቀት ተከተለው።
55በግቢው መሓል እሳት ካቀጣጠሉና ዐብረው ከተቀመጡ ጴጥሮስ መጥቶ በመካከላቸው ተቀመጠ።
56በእሳቱ ብርሃን እንደተቀመጠም አንዲት ገረድ አየችውና በቀጥታ ተመልክታው፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበር” አለች።
57ጴጥሮስ ግን፣ “ሴትዮ፣ የምትዪውን ሰው አላውቀውም” ብሎ ካደ።
58ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ፣ ሌላ ሰው አየውና፣ “አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው። ነገር ግን ጴጥሮስ፣ “አንተ ሰው፣ እኔ አይደለሁም” አለ።
59ከአንድ ሰዓት ያህል ጊዜ በኋላ፣ ሌላ ሰው፣ “በእውነት ይህ ሰው ደግሞ ገሊላዊ ስለ ሆነ ከእርሱ ጋር ነበረ” በማለት በጥብቅ ተናገረ።
60ነገር ግን ጴጥሮስ፣ “አንተ ሰው የምትለውን አላውቅም” አለ። ይህን እየተናገረ እያለ ወዲያው ዶሮ ጮኸ።
61ጌታም ዞር አለና ጴጥሮስን ተመለከተው። ጴጥሮስም፣ ጌታ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለውን ቃል አስታወሰ።
62ጴጥሮስ ወደ ውጭ ወጣና መራራ ልቅሶ አለቀሰ።
63ከዚያም ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች እያላገጡበት ደበደቡት። ዐይኖቹን ከሸፈኑ በኋላ፣
64“እስቲ ትንቢት ተናገር። አሁን የመታህ ሰው ማን ነው?” በማለት ጠየቁት።
65እየተሳደቡ፣ ሌሎች ብዙ ነገሮችን በኢየሱስ ላይ ተናገሩ።
66እንደነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎች፣ ከካህናት አለቆችና ከሕግ መምህራን ጋር ዐብረው ተሰበሰቡ። ከዚያም ኢየሱስን ወደ ሸንጎው ፊት አቀረቡትና፣
67“ክርስቶስ ከሆንህ ንገረን” አሉት። እርሱ ግን፣ “እኔ ብነግራችሁ አታምኑም፣
68ደግሞም ብጠይቃችሁ አትመልሱም።
69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኅይል ቀኝ ይቀመጣል” አላቸው።
70ሁሉም በአንድነት፣ “እንግዲህ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነሃ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትናገራላችሁ” አላቸው። እነርሱ፣
71“እንግዲህ ለምን ምስክር እንፈልጋለን? ሲናገር እኛ ራሳችን ከአፉ ሰምተነዋል” አሉ።