መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 20

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፣ ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያስተምርና ወንጌልን ይሰብክ በነበረ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ መጡ።
2"እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይም ይህን ሥልጣን የሰጠህ እርሱ ማን ነው?" አሉት።
3እርሱም እንዲህ በማለት መለሰላቸው፤ "እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፣ እስቲ መልሱልኝ።
4የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰዎች?"
5እርስ በርሳቸው ተመካከሩና፣ "'ከሰማይ ነው ብንል፣ 'ታዲያ ለምን አላመናችሁትም ይለናል።
6ነገር ግን 'ከሰው ነው ብንል' ሕዝቡ ዮሐንስን ነቢይ አድርገው ስለሚቆጥሩ ይወግሩናል" አሉ።
7ስለዚህ ከየት እንደ ሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት።
8ኢየሱስ፣ "እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም" አላቸው።
9ለሕዝቡ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፣ "አንድ ሰው ያዘጋጀውን የወይን ዕርሻ ለወይን ገበሬዎች አከራይቶ ረጅም ጊዜ ሊቆይ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
10ምርቱ የሚሰበሰብበት ጊዜ ሲደርስ ከወይኑ የሚገባውን ፍሬ ለማግኘት ወደ ገበሬዎቹ አንድ አገልጋይ ላከ። ነገር ግን የወይኑ ገበሬዎች አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን መልሰው ላኩት።
11እርሱም አሁንም ሌላ አገልጋይ ላከባቸው፣ ይህንም ደብድበውና አዋርደው ባዶ እጁን መልሰው ላኩት።
12እንደ ገና ሦስተኛ አገልጋይ ቢልክባቸው፣ እርሱንም አቈሳስለው አውጥተው ጣሉት።
13ስለዚህ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት፣ 'ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልከዋለሁ። ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል' አለ።
14ነገር ግን የወይኑ ገበሬዎች ባዩት ጊዜ፣ 'ወራሹ ይህ ነው። ዕርሻው የእኛ እንዲሆን እንግድለው' ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ።
15ከዕርሻው ቦታ አወጡትና ገደሉት። እንግዲህ የዕርሻው ባለቤት ምን ያደርግባቸዋል? መጥቶ እነዚህን የወይን ገበሬዎች ይደመስሳቸዋል፣
16ዕርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል" አላቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ "እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ነገር ያርቀው!" አሉ።
17ኢየሱስ ግን ተመለከታቸውና፣ 'ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነ' "የሚለው ይህ የመጽሐፍ ቃል ምን ማለት ነው?
18በዚህ ድንጋይ የሚደናቀፍ ሁሉ ይሰባበራል። ነገር ግን ድንጋዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቃል" አለ።
19ስለዚህ፣ የሕግ መምህራንና የካህናት አለቆች በዚያን ሰዓት ሊይዙት ፈለጉ፣ ምክንያቱም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ እንደ ሆነ አውቀዋልና።
20ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። በዐይነ ቁራኛ እየተከታተሉት፣ ለፍርድና ለገዢው ሥልጣን የሚዳርገውን ስሕተት ከንግግሩ ሊያገኙበት ራሳቸውን ጻድቃን አስመስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት።
21እነርሱ እንዲህ በማለት ጠየቁት፤ "መምህር ሆይ፣ አንተ በትክክል እንደምትናገርና እንደምታስተምር፣ ደግሞም በማንም እንደማትመራ፣ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንገድ እውነቱን እንደምታስተምር እናውቃለን።
22ለቄሣር ግብር መክፈል ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?"
23ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ተረዳ፣ እንዲህም አላቸው፣
24"አንድ ዲናር አሳዩኝ። በላዩ ያለው የማን ጽሑፍና ምስል ነው?" እነርሱም፣ "የቄሣር ነው" አሉት።
25"እንግዲያውስ የቄሣር የሆኑትን ነገሮች ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርን ነገሮች ለእግዚአብሔር ስጡ" አላቸው።
26የሕግ መምህራንና የካህናት አለቆች በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም። ምንም እስከማይናገሩ ድረስ በመልሱ ተደነቁ።
27የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ አንዳንድ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ፣
28እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ "መምህር ሆይ፣ ሙሴ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የዚያን ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ለእርሱ እንዲወልድለት ጽፎልናል።
29ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አገባና ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤
30ሁለተኛውም እንደዚሁ አግብቷት ልጅ ሳይወልድ ሞተ።
31ሦስተኛውም አገባት፤ በዚህ ዓይነት ሰባቱም ሴቲቱን አግብተው ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ።
32በመጨረሻ ሴቲቱም ሞተች።
33ታዲያ በትንሣኤ ቀን ይህች ሴት የማንኛቸው ሚስት ትሆናለች? ምክንያቱም ሰባቱም አግብተዋታልና።"
34ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ "የዚህ ዓለም ሰዎች ያገባሉ፣ ይጋባሉም።
35ነገር ግን የሙታን ትንሣኤንና የዘላለም ሕይወትን ለመቀበል የተገባቸው አያገቡም፣ አይጋቡምም።
36እንደ መላእክት ስለ ሆኑ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ሊሞቱ አይችሉም። የትንሣኤ ልጆች እንደ መሆናቸው መጠን የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።"
37ነገር ግን ሙታን ስለ መነሣታቸው ሙሴ እንኳ በቊጥቋጦው ስፍራ፣ጌታን የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ብሎ በመጥራቱ አሳይቷል።
38አሁን እርሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፣ ምክንያቱም ለእርሱ ሁሉም ሕያዋን ናቸው።"
39ከሕግ መምህራን አንዳንዶች፣ "መምህር ሆይ፣ ጥሩ አድርገህ መልሰሃል" አሉት።
40ደግሞም ተጨማሪ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ማንም አልደፈሩም።
41ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፣ "እንግዲህ ሰዎች ክርስቶስን የዳዊት ልጅ ነው የሚሉት እንዴት ነው?
42ዳዊት ራሱ በመዝሙር መጽሐፍ፣ "ጌታ ለጌታዬ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ
43እስከማደርግልህ ድረስ 'በቀኜ ተቀመጥ' ይላልና።
44ስለዚህ ዳዊት ክርስቶስን ጌታ ይለዋል፣ታዲያ የዳዊት ልጅ እንዴት ይሆናል?"
45ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፣
46"ረጅም ቀሚስ ለብሰው መመላለስ ከሚፈልጉ፣ በገበያ ቦታዎችም ልዩ ሰላምታ፣ በምኲራቦች ከፍተኛ ስፍራ፣ በግብዣ ቦታዎችም የከበሬታ መቀመጫ እንዲሰጣቸው ከሚወዱ የሕግ መምህራን ተጠንቀቁ።
47ደግሞም እነርሱ ረጅም የሆኑ የማስመሰል ጸሎቶችን እየጸለዩ የመበለቶችን ቤት አለአግባብ ይበዘብዛሉ። እነዚህ የባሰ ቅጣት ይቀበላሉ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።