መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ ኢያሪኮ ከተማ ገብቶ እያለፈ ሳለ፣
2ዘኬዎስ የሚባል አንድ የቀራጮች አለቃና ሀብታም ሰው ወዳለበት ስፍራ ደረሰ።
3ዘኬዎስ ኢየሱስ የትኛው እንደ ሆነ ለማየት ይሞክር ነበር፣
4ነገር ግን አጭር ስለ ነበረ፣ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ አሻግሮ ማየት አልቻለም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በዚያ መንገድ ያልፍ ስለነበር፣ ከሕዝቡ ቀድሞ ሮጠና ሊያየው በእንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ።
5ኢየሱስ ወደ ስፍራው በደረሰ ጊዜ፣ ቀና ብሎ ተመለከተና፣ “ዘኬዎስ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ቤትህ መሄድ እፈልጋለሁና ቶሎ ውረድ” አለው።
6ስለዚህ ዘኬዎስ በፍጥነት ወርዶ በደስታ በቤቱ ተቀበለው።
7ይህን የተመለከቱት ሰዎች ሁሉ፣ “በኃጢአተኛ ሰው ቤት ገባ” በማለት አጒረመረሙ።
8ዘኬዎስ ተነሥቶ ቆመና ጌታን፣ “ጌታ ሆይ፣ የሀብቴን ግማሽ ለድሆች እሰጣለሁ፣ ያታለልሁት ሰው ካለ፣ የወሰድሁበትን አራት ዕጥፍ እመልስለታለሁ” አለው።
9ኢየሱስ እንዲህ አለው፣ "ዛሬ ድነት ለዚህ ቤት መጥቷል። ምክንያቱም፣ እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነው።
10የሰው ልጅ የመጣው የጠፉትን ሰዎች ሊፈልግና ሊያድን ነውና” አለ።
11እነርሱ እነዚህን ነገሮች እንደ ሰሙ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየተቃረበ ስለ ነበር ሕዝቡ የእግዚአብሔር መንግሥት ወዲያው የሚገለጥ መሰላቸው።
12ስለዚህ ኢየሱስ ንግግሩን በምሳሌ በመቀጠል እንዲህ አለ፣ “አንድ መኰንን የመንግሥት ሹመት ተቀብሎ ሊመጣ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ነበር።
13ከዚያም፣ ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና፣ “እስክመጣ ድረስ ይህን ነግዱበት” አላቸው።
14ነገር ግን የአገሩ ሰዎች ይጠሉት ስለ ነበር፣ 'ይህ ሰው ተመልሶ በእኛ ላይ ገዥ እንዲሆን አንፈልግም' በማለት ተወካዮቻቸውን ከኋላው ላኩበት።
15መኰንኑም ሹመቱን ተቀብሎ ሲመለስ፣ ነግደው ያተረፉትን ትርፍ ለመተሳሰብ ገንዘቡን የሰጣቸው አገልጋዮቹ እንዲጠሩለት አዘዘ።
16የመጀመሪያው አገልጋይ ወደፊቱ ቀረበና፣ 'ጌታ ሆይ፣ ምናንህ ተጨማሪ ዐሥር ምናን አትርፎልሃል' አለው።
17ጌታውም፣ “ደግ አድርገሃል፣ አንተ ታታሪ አገልጋይ። በጥቂቱ ስለ ታመንህ፣ በዐሥር ከተሞች ላይ ገዥ ትሆናለህ' አለው።
18ሁለተኛውም ቀርቦ፣ 'ጌታ ሆይ፣ ምናንህ ዐምስት አትርፏል' አለው።
19ጌታውም፣ 'በዐምስት ከተሞች ላይ ገዥ ሁን' አለው።
20ሌላኛውም መጣና፣ 'ጌታ ሆይ፣ በደንብ አድርጌ በጨርቅ ጠቅለዬ ያስቀመጥሁት ምናንህ ይኸውልህ፣
21ይህን ያደረግሁት አንተ ጨካኝ ሰው መሆንህን ስላወቅሁ ፈርቼ ነው። አንተ ያላስቀመጥኸውን የምትጠይቅ ያልዘራኸውን የምታጭድ ነህ' አለው።
22ጌታውም፣ እንዲህ አለው፤ 'አንተ ክፉ አገልጋይ፣ በአፍህ ቃል እፈርድብሃለሁ። ካላስቀመጥሁበት የምፈልግ፣ ካልዘራሁበት የማጭድ ጨካኝ ሰው መሆኔን ያወቅህ ከሆነ፣
23ታዲያ ስመለስ ገንዘቤን ከነትርፉ እንዳገኝ ለምን በባንክ አላስቀመጥኸውም?”
24ከዚያም ጌታው በዚያ ለቆሙት ሰዎች፣ “ምናኑን ውሰዱበት፣ ዐሥር ላለውም ጨምሩለት' አላቸው፤
25እነርሱም፣ 'ጌታ ሆይ፣ አስር ምናን አለው እኮ' አሉት።
26ጌትየውም፣ 'ላለው ይጨምርለታል፣ ከሌለው ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
27በእነርሱ ላይ ገዥ እንዳልሆን የተቃወሙትን እነዚህን ጠላቶቼን ግን አምጡና በፊቴ ግደሏቸው' አለ።
28ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም በማቅናት መንገዱን ቀጠለ።
29ደብረ ዘይት በሚባለው ተራራ አጠገብ ወደሚገኝ ቤተ ፋጌና ቢታንያ በተቃረበ ጊዜ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን
30እንዲህ ብሎ ላካቸው፤ "ወደሚቀጥለው መንደር ሂዱ። ስትገቡ፣ ማንም ያልተቀመጠበትን አንድ የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ። ፍቱትና አምጡልኝ።
31ማንም፣ 'ለምን ትፈቱታላችሁ?' ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ 'ለጌታ ያስፈልገዋል' በሉት" አላቸው።
32የተላኩትም ወደ ስፍራው በደረሱ ጊዜ፣ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው፣ የአህያውን ውርንጫ ታስሮ አገኙት።
33ውርንጫውን እየፈቱ እያለ ባለቤቶቹ፣ 'ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?' አሉ።
34እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” ብለው መለሱለት።
35ወደ ኢየሱስ አመጡትና ልብሳቸውን በውርንጫው ጀርባ ላይ አንጥፈው ኢየሱስ እንዲቀመጥበት አደረጉ።
36ኢየሱስ በሚሄድበት ጊዜ፣ ከፊቱ ባለው መንገድ ላይ ልብሶቻቸውን ያነጥፉለት ነበር።
37ከደብረ ዘይት ተራራ ቁልቁል ወደሚወስደው መንገድ በቀረበ ጊዜ፣ ቊጥራቸው ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት፣ ስላዩአቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ደስ እያላቸው፣ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው! በሰማይ ሰላም፣
38ክብርም በአርያም ይሁንለት!” እያሉ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
39በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” አሉ።
40ኢየሱስም፣ “ልንገራችሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮችም እንኳ ይጮኻሉ” አላቸው።
41ኢየሱስ ወደ ከተማይቱ በተቃረበ ጊዜ እንዲህ በማለት አለቀሰላት፤
42“ለአንቺ ሰላም የሚያመጣልሽን ነገር ምነው ዛሬ ባወቅሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሮብሻል።
43ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው የሚከቡሽና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁሽ ጊዜያት ይመጣሉ።
44አንቺንና ልጆችሽንም በምድር ላይ ይፈጠፍጣሉ። እነርሱም ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይተዉም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊያድንሽ መፈለጉን አላወቅሽምና።”
45ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባና በዚያ ይሸጡ የነበሩትን ያባርራቸው ጀመር፣
46ከዚያም፣ “የአባቴ ቤት 'የጸሎት ቤት ይሆናል' ተብሎ ተጽፏል፣ እናንተ ግን የወንበዴዎች መሸሸጊያ አደረጋችሁት” አለ።
47ስለዚህ ኢየሱስ በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር። ታዲያ የካህናት አለቆች፣ የሕግ መምህራንና የሕዝቡ መሪዎች ሊገድሉት ፈለጉ።
48ነገር ግን ሕዝቡ ከልብ ያደምጡት ስለ ነበር መንገድ አላገኙም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።