መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ብዙዎች በእኛ ዘንድ ስለተፈጸሙት ጉዳዮች ታሪኩን በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ሞክረዋል፣
2ይህም የዓይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት በመጀመሪያ ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት ነበር፡፡
3ስለሆነም፣ እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፣ እኔም የእነዚህን ነገሮች ሂደት ከመጀመሪያው በትክክል ከመረመርኩ በኋላ፣ በቅደም ተከተላቸው መጻፍ መልካም መስሎ ታየኝ፡፡
4ይህንንም ያደረግሁት ስለ ተማርኸው ነገር እውነቱን ታውቅ ዘንድ ነው፡፡
5በይሁዳ ገዢ፣ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፡፡ ሚስቱም ከአሮን ልጆች የነበረችና ስሟም ኤልሳቤጥ የሚባል ነበር፡፡
6ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፣ የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ትእዛዛት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየጠበቁ ይኖሩ ነበር፡፡
7ነገር ግን ኤልሳቤጥ መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራቸውም፣ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሁለቱም አርጅተው ነበር፡፡
8በዚህን ጊዜ፣ ዘካርያስ በክፍሉ ተራ የክህነት አገልግሎቱን እየፈጸመ በእግዚአብሔር ፊት የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ፡፡
9የትኛው ካህን እንደሚያገለግል ለመምረጥ በሚፈጸመው ልምድ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ዕጣ ደረሰው፡፡
10እርሱ ዕጣን በሚያጥንበት ወቅት፣ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ይጸልይ ነበር፡፡
11በዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና በዕጣኑ መሠዊያ በስተቀኝ ቆመ፡፡
12ዘካርያስ በተመለከተው ጊዜ ደነገጠ፣ ፍርሃትም በእርሱ ላይ ወደቀ፡፡
13ነገር ግን መልአኩ፣ “ጸሎትህ ተሰምቶአልና ዘካርያስ ሆይ፣ አትፍራ፡፡ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፡፡
14ሐሴትና ደስታ ይሆንልሃል፣ ብዙዎችም በእርሱ መወለድ ሐሴት ያደርጋሉ፡፡
15በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና፣ ወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል፡፡
16ከእስራኤል ሕዝብም ብዙዎቹ ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመለሳሉ፡፡
17በእግዚአብሔርም ፊት በኤልያስ መንፈስና ኃይል ይመላለሳል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው የማይታዘዙት በጻድቃን ጥበብ ይሄዱ ዘንድ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች ለመመለስና የተዘጋጁትን ሕዝብ ለእግዚአብሔር ያዘጋጅ ዘንድ ነው” አለው፡፡
18ዘካርያስም፣ “እኔ ያረጀሁ በመሆኔና ሚስቴም ዕድሜዋ የገፋ በመሆኑ፣ ይህንን እንዴት ማወቅ እችላለሁ?” አለ፤
19መልአኩም፣ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንን የምሥራች እነግርህ ዘንድ ተልኬያለሁ፡፡
20እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች እስኪፈጸሙ ድረስ ጸጥ ትላለህ፣ መናገርም አትችልም፡፡ ይህም የሚሆነው በትክክለኛው ጊዜ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንክ ነው፡፡”
21በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስን እየተጠባበቁ ነበር፣ ለረጅም ጊዜ በቤተ መቅደስ በመቆየቱም ተደነቁ፡፡
22በወጣ ጊዜ ግን ሊያነጋግራቸው አልቻለም፤ እነርሱም በቤተ መቅደስ በነበረበት ጊዜ ራእይ እንደ ተገለጠለት ተገነዘቡ፡፡ ለእነርሱ ምልክት ብቻ እየሰጣቸው ጸጥ ብሎ ቆየ፡፡
23የአገልግሎቱም ወቅት እንዳበቃ ወደ ቤቱ ለመመለስ ተነሣ፡፡
24ከዚህም ወቅት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፣ እንደዚህም አለች፣
25“በሕዝብ ዘንድ የነበረብኝን ነቀፌታ ለማስወገድ ብሎ በሞገስ ተመልክቶኝ እግዚአብሔር ለእኔ ያደረገልኝ ይህንን ነው፡፡”
26ስድስት ወሯ በነበረ ጊዜ መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደተባለች የገሊላ ከተማ ተላከ፡፡
27የተላከውም ዮሴፍ ለተባለ ከዳዊት ነገድ ለሆነ ሰው ወደ ታጨች አንዲት ድንግል ነበር፡፡ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር፡፡
28ወደ እርሷም መጣና እንደዚህ አላት፣ “እጅግ የተከበርሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፡፡”
29እርሷ ግን በንግግሩ በጣም ግራ ተጋባች፣ ምን ዓይነት ሰላምታ ሊሆን እንደሚችልም በማሰብ ተደነቀች፡፡
30መልአኩም፣ “ማርያም ሆይ፤ አትፍሪ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻል፤
31እነሆ፣ ፅንስ በማሕፀንሽ ውስጥ ይፀነሳል፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ ስሙንም ‘ኢየሱስ’ ትይዋለሽ፡፡
32እርሱም ታላቅ ይሆናል፣ የልዑልም ልጅ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡
33በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፡፡"
34ማርያምም ለመልአኩ፣ “ከማንም ወንድ ጋር ተኝቼ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው፡፡
35መልአኩም እንደዚህ በማለት መለሰላት፣ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑል ኃይልም በአንቺ ላይ ያርፋል፤ ከዚህ የተነሣም የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡
36እነሆ፣ ዘመድሽም ኤልሳቤጥ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷ ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፡፡
37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር የለምና፡፡”
38ማርያምም፣ “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፡፡” ከዚያ በኋላም መልአኩ ትቷት ሄደ፡፡
39ከዚያ በኋላ፣ ማርያም ተነሥታ በእነዚያ ቀናት በኮረብታማው አገር በይሁዳ ወዳለች ወደ አንዲት ከተማ በፍጥነት ሄደች፡፡
40ወደ ዘካርያስም ቤት ሄደችና ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበችላት፡፡
41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ እንደዚህ ሆነ፣ በማሕፀኗ ያለው ፅንስ ዘለለ፣ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፡፡
42ድምፅዋን ከፍ በማድረግ ጮክ ብላ፣ “ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ፣ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡
43የጌታዬ እናት ወደ እኔ እንድትመጣ ይህ ለምን ሆነ?
44እነሆ፣ የሰላምታሽ ድምፅ ወደ ጆሮዬ በመጣ ጊዜ በማሕፀኔ ውስጥ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ፡፡
45ከጌታ የተነገሩላት ነገሮች እንደሚፈጸሙ የምታምን እነሆ እርሷ የተባረከች ናት፡፡”
46ከጌታ የተነገሩላት ነገሮች እንደሚፈጸሙ የምታምን እነሆ እርሷ የተባረከች ናት፡፡” 46. ማርያምም፣ “ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፣
47መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ሐሴት ታደርጋለች፡፡
48የሴት ባሪያውን ውርደት ተመልክቶአልና፡፡ እነሆ፣ ከዚህ በኋላ ትውልድ ሁሉ የተባረከች ይሉኛል፡፡
49ብርቱ የሆነ እርሱ ለእኔ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፣ ስሙም ቅዱስ ነው፡፡
50ለሚያከብሩት ምሕረቱ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው፡፡
51በክንዱ ብርታትን ገልጾአል፣ ስለ ልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፡፡
52ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፣ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓቸዋል፡፡
53የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቧቸዋል፣ ባለጠጎችን ግን ባዶአቸውን ሰድዷቸዋል፡፡
54ምሕረት ማድረጉን ያስታውስ ዘንድ ለባሪያው ለእስራኤል ረድኤቱን ልኮለታል፣
55ይህንንም ያደረገው (ለአባቶቻችን እንደተናገረው) ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም፡፡”
56ማርያም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወራት ያህል ተቀመጠች፣ ከዚያ በኋላም ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
57በዚያን ጊዜ ኤልሳቤጥ የምትወልድበት ወቅት ደረሰ፣ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡
58ጎረቤቶቿና ዘመዶቿ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዳበዛላት ሰሙ፣ ከእርሷም ጋር ደስ አላቸው፡፡
59ልጁን የሚገርዙበት ስምንተኛው ቀን በመጣ ጊዜ፣ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊሰይሙት ፈልገው ነበር፡፡
60እናትዬዋ ግን መልስ ሰጠቻቸው፣ “አይሆንም፣ ስሙ ዮሐንስ ይሆናል” አለች፡፡
61እነርሱም ለእርሷ፣ “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ የለም” አሏት፡፡
62በምን ስም እንዲጠራ እንደሚፈልግ አባቱን በምልክት ጠየቁት፡፡
63አባቱም ሰሌዳ እንዲያቀርቡለት ጠየቀና፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፡፡ በዚህም ሁሉም ተደነቁ፡
64ወዲያውኑም አንደበቱ ተከፈተ፣ ምላሱም ተፈትቶ ተናገረ፣ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፡፡
65በዙሪያቸውም በሚኖሩት ሰዎች ዘንድ ፍርሃት መጣባቸው፣ የእነዚህም ነገሮች ዜና በኮረብታማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተሠራጨ፡፡
66ዜናውን የሰሙትም ሁሉ፣ የእግዚአብሔር እጅ ከእርሱ ጋር ነበርና “እንግዲህ ይህ ልጅ ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ጠበቁት፡፡
67አባቱም ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣
68“የእስራኤል አምላክ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ የመቤዠት ሥራ በመሥራት ሕዝቡን ረድቶታልና፡፡
69ከባሪያው ከዳዊት ዝርያዎች መካከል ለባሪያው ለዳዊት ቤት የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፡፡
70ይህም በጥንት ዘመን በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ እንደ ተናገረው ነው፡፡
71ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ ያድነናል፡፡
72ይህንን የሚያደርገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየትና ቅዱስ ኪዳኑን፣
73ማለትም ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማስታወስ ነው፡፡
74መሐላውን የማለውም እኛ ከጠላቶቻችን ድነን በዘመኖቻችን ሁሉ በእርሱ ፊት በመሆን ያለ ፍርሃት፣
75በቅድስናና በጽድቅ እርሱን እንድናገለግለው ነው፡፡
76አዎን፣ አንተም ሕፃን የእርሱን መንገድን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ስለምትሄድና ሕዝብንም ለመምጣቱ ስለምታሰናዳ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፡፡
77ለኃጢአቶቻቸው ይቅርታ የሚያገኙትን የድነት ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡
78ይህም ከእግዚአብሔር አምላካችን መልካም ምሕረት የተነሣ ከእርሱ የተነሣ የፀሐይ ብርሃን በእኛ ላይ እንዲያርፍብንና
79በጨለማና በሞት ጥላ ላሉት እናበራላቸው ዘንድ ነው፡፡ ይህንንም እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ይመራው ዘንድ ያደርገዋል፡፡”
80ልጁም አደገ፣ በመንፈሱም ጠነከረ፣ ለእስራኤልም እስኪገለጥ ድረስ በምድረ በዳ ኖረ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።