1ከዚያም ኢየሱስ ሳይታክቱ ዘወትር መጸለይ እንደሚገባቸው እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፤
2"በአንድ ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ፤ ሰውንም የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ።
3አንዲት ባል የሞተባት ሴትም በዚያ ከተማ ነበረች። እርስዋም ዘወትር ወደ ዳኛው እየመጣች፣ 'ከባላጋራዬ ጋር ስላለኝ ክርክር ፍረድልኝ' ትለው ነበር።
4ዳኛውም ለረጅም ጊዜ ሊረዳት ፈቃደኛ አልነበረም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ወደ ልቡ ተመልሶ እንዲህ ብሎ አሰበ፤
5'ምንም እንኳ እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣ ይህች ባል የሞተባት ሴት አዘውትራ በመምጣት እንዳታታክተኝ እፈርድላታለሁ።' "
6ከዚያም ጌታ እንዲህ አለ፤ "ቅንነት የሌለው ዳኛ የሚናገረውን ስሙ።
7ታዲያ እግዚአብሔር ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹት ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?
8ደግሞስ አይታገሣቸውምን? እላችኋለሁ በቶሎ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆን?"
9ከዚያም ኢየሱስ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚመኩና ሌሎችንም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ተናገረ፤
10"ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሲሆን፣ ሌላው ቀራጭ ነበረ።
11ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ በማለት ስለ ራሱ ጸለየ፤ 'እግዚአብሔር ሆይ፣ እኔ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ወይም እንደዚህ ቀራጭ እንኳ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ።
12በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።'
13"ቀራጩ ግን ከርቀት ቆሞ ዐይኑን ወደ ሰማይ ሳያነሣ ደረቱን እየመታ፣ 'አምላኬ ሆይ፣ እኔን ኅጢአተኛውን ማረኝ!' ይል ነበር። እላችኋለሁ፣
14"ከሌላው ይልቅ ጻድቅ ሆኖ ይህ ሰው ወደ ቤቱ ተመለሰ ፤ ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን የሚያዋርድ ከፍ ከፍ ይላል።"
15እንዲዳስሳቸው ሰዎች ልጆቻቸውን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጹአቸው።
16ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠራቸውና፣ "ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተውአቸው አትከልክሏቸውም። የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።
17እውነት እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን በየዋህነት ያልተቀበላት ፈጽሞ አይገባባትም" አለው።
18ከአለቆች አንዱ ኢየሱስን፣ "ቸር መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?" ብሎ ጠየቀው።
19ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ "ለምን ቸር ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስቀር ቸር የለም።
20ትእዛዛትን ሁሉ ታውቃቸዋለህ፤ እነርሱም፣ 'አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ እናትህንና አባትህን አክብር የሚሉ ናቸው።"
21አለቃውም ፣ "እነዚህንማ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአቸዋለሁ።"
22ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰውየውን፣ "እንግዲያውስ ገና አንድ ነገር ማድረግ ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድኾች ስጣቸው፤ በመንግሥተ ሰማያት ሀብት ይኖርሃል። ከዚያም በኋላ መጥተህ ተከተለኝ" አለው።
23ሀብታሙ ሰውዬ ግን በጣም ባለጠጋ ስለ ነበረ፣ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ።
24ከዚያም ኢየሱስ ሰውየው እንዳዘነ አይቶ፣ "ሀብታም ለሆኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!
25ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አለ።
26የሰሙትም ሰዎች፣ "እንግዲያውስ ማን ሊድን ይችላል?" አሉ።
27ኢየሱስ፣ "በሰው ዘንድ የማይቻል ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል" ብሎ መለሰ።
28ጴጥሮስ፣ "እነሆ፣ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል" አለው።
29ከዚያም ኢየሱስ፣ "እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን፣ ወይም ወንድሞቹን፣ ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ
30በዚህ ዓለም ብዙ ዕጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማያገኝ ማንም የለም" አላቸው።
31ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ከሰበሰበ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ "አሁን ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ ስለ ሰው ልጅ በነቢያት አስቀድሞ የተነገሩት ሁሉ ይፈጸማሉ።
32እርሱ ለአሕዛብ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ያላግጡበታል፤ ያዋርዱታል፤ ይተፉበታልም።
33ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።"
34ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ ከተናገራቸው ነገሮች አንዱንም አልተረዱም። ይህ ቃልም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለተባሉትም ነገሮች ምንም አልተረዱም።
35ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ፣ አንድ ዐይነ ስውር ምጽዋት እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር፤
36ሕዝብ ሲያልፉ ሰምቶም እየሆነ የነበረውን ነገር ጠየቀ።
37እነርሱም፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ በኩል እያለፈ መሆኑን ነገሩት።
38ስለዚህ ዐይነ ስውሩ፣ "የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እባክህ ማረኝ" እያለ ጮኸ።
39እፊት እፊት ይሄዱ የነበሩት፣ "ዝም በል!" ብለው ዐይነ ስውሩን ገሠጹት። እርሱ ግን ድምፁን የበለጠ ከፍ አድርጎ፣ "የዳዊት ልጅ ሆይ፣ እባክህ ማረኝ" ብሎ ጮኸ።
40ኢየሱስ ቆሞ ሰውየውን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዛቸው ። ከዚያም ዐይነ ስውሩ ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ፣ ኢየሱስ፣
41"ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?" ብሎ ጠየቀው። "ጌታ ሆይ፣ ማየት እፈልጋለሁ" አለ።
42ኢየሱስም፣ "እይ። እምነትህም አድኖሃል" አለው። ዐይነ ስውሩም ወዲያውኑ ማየት ቻለ።
43እግዚአብሔርን እያመሰገነ ኢየሱስን ተከተለ። ሕዝቡ ሁሉ ይህን አይተው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።