መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 17

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤ "ወደ ኅጢአት የሚያመሩ ነገሮች መምጣታቸው የማይቀር ነው። ነገር ግን ለኅጢአት ምክንያት ለሚሆነው ሰው ወዮለት።
2በእምነት ደካማ ከሆኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከማስናከል ይልቅ ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።
3ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤ ተመልሶ ከተጸጸተ ይቅር በለው፤ በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ ተመላልሶ፤
4'ስለ ሠራሁት ኅጢአት ተጸጸትሁ' እያለ ወደ አንተ ቢመለስ ይቅር ልትለው ይገባል።"
5ሐዋርያት ጌታን፣ "እምነት ጨምርልን" አሉት።
6ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ "የሰናፍጭን ዘር ያህል እምነት ቢኖራችሁ፤ ይህን የሾላ ዛፍ፣ 'ከመሬት ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል' ብትሉት ይታዘዝላችኋል።
7"በዕርሻ ወይም በበጎች እረኝነት የተሰማራ አገልጋይ ካላችሁ፣ አገልጋዩ ከሥራ ደክሞ ሲመለስ፣ ወዲያውኑ "ና ተቀመጥና እራትህን ብላ የሚለው ከእናንተ ማን ነው?"
8"እራቴን አዘጋጅልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣም ወገብህን ታጥቀህ ቆመህ አስተናግደኝ፤ ከዚያ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ ትጠጣለህም አይለውምን?"
9ታዲያ አገልጋዩ የታዘዘውን ስለ ፈጸመ ጌታው ያመሰግነዋልን?
10እንዲሁም እናንተም የታዘዛችሁትን ሁሉ ከፈጸማችሁ በኋላ የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ 'የፈጸምነውም የታዘዝንውን ግዳጃችንን ብቻ ነው' ማለት አለባችሁ።"
11ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ ሳለ፣ ሰማርያንና ገሊላን በሚያዋስነው መንገድ ያልፉ ነበር።
12ኢየሱስም ወደ አንዲት መንደር በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች አገኙት። እነርሱም ከእርሱ ርቀው ቆሙና
13ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ "ኢየሱስ ሆይ፣ መምህር ሆይ፣ እባክህ ማረን" እያሉ ጮኹ።
14ኢየሱስ ባያቸው ጊዜ፣ "ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ" አላቸው። እነርሱም እየሄዱ ሳሉ፣ ከለምጻቸው ነጹ።
15ከእነርሱ አንዱ ከለምጹ መፈወሱን ባየ ጊዜ፣ ጮክ ብሎ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ።
16በኢየሱስ እግር ሥር በግንባሩ ተደፍቶ አመሰገነው። እርሱም የሰማርያ ሰው ነበር።
17ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፣ "ዐሥሩም ለምጻሞች ተፈውሰው አልነበረምን? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ?
18ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር እግዚአብርሔን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ሌላ የለምን?"
19ኢየሱስ ሰውየውን፣ "ተነሥና ሂድ እምነትህ አድኖሃል" አለው።
20ፈሪሳውያን ኢየሱስን፣ "የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?" ብለው ለጠየቁት ጥያቄ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ "የእግዚአብሔር መንግሥት የምትታይ አይደለችም።" ወይም'እነሆ፣ እዚህ ናት'
21ወይም 'እነሆ፣እዚያ ናት' የምትባል አይደለችም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት።"
22ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤" ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትናፍቁበት ቀን ይመጣል። ነገር ግን አታዩትም።
23ሰዎች፣ 'እነሆ፣ ክርስቶስ እዚህ ነው! ወይም እዚያ ነው!' ይሉአችኋል። ነገር ግን እነርሱን ሰምታችሁ አትፈልጉ፤ አትከተሉአቸውም።
24መብረቅ በሰማይ ላይ ሲበርቅ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።
25ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል ይገባል። በዚህ ዘመን ሰዎችም ሊናቅና ሊነቀፍ ግድ ነው።
26በኖኅ ዘመን እንደሆነው፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንዲሁ ይሆናል።
27ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡና ነበር። ነገር ግን በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።
28እንደዚሁም በሎጥ ዘመን ሰዎች ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይሸጡ ይገዙ፣ አትክልት ይተክሉና ቤትም ይሠሩ እንደ ነበረ ይሆናል።
29ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋ።
30የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል።
31በዚያ ቀን በቤቱ ጣሪያ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ። በዕርሻም ቦታ ያለ ሰው ወደ ቤቱ አይመለስ።
32የሎጥን ሚስት አስታውሱአት። ሕይወቱን ሊያድን በራሱ መንገድ ለመሄድ የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል።
33ነገር ግን ሕይወቱን ለጌታ አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ያድናታል።
34ይህን እላችሏለሁ፣ "በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ላይ ይተኛሉ።
35ከእነርሱም አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። እንዲሁም ሁለት ሴቶች በአንድ ቦታ አብረው ይፈጫሉ፤
36አንድዋ ትወሰዳለች ሌላዋ ትቀራለች። ሁለት ሰዎች በአንድ ዕርሻ ቦታ ያርሳሉ፤አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።"
37ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን፦ 'ጌታ ሆይ፤ ወዴት?' ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ "በድን ባለበት አሞራዎች ይሰበባሉ።" ሲል መለሰላቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።