1ደግሞም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ "አንድ ሀብታም ሰው ነበረ፤ እርሱም በንብረቱ ሁሉ ላይ የሾመው አስተዳዳሪ ነበረው። ይህ አስተዳዳሪ ሀብተ ያባክናል ተብሎ ለሀብታሙ ተነገረው።
2ስለዚህ ሀብታሙ ሰው አስተዳዳሪውን ጠርቶ፣ 'ይህ ስለ አንተ የምሰማው ነገር ምንድን ነው? ከዚህ በኋላ ለእኔ አስተዳዳሪ ልትሆን ስለማትችል ንብረቴን አስረክበኝ' አለው።
3አስተዳዳሪው እንዲህ ብሎ አሰበ፤ 'እንግዲህ ጌታዬ ከአስተዳደር ሥራዬ ስለሚያሰናብተኝ፣ ምን ባደርግ ይሻለኛል? ዓቅም ስለሌለኝ፣ ከእንግዲህ መሬት በመቈፈር ለመተዳደር አልችልም፤ መለመንም ያሳፍረኛል።
4ከአስተዳዳሪነት ሥራዬ ስሰናበት፣ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ ካሁኑ ምን እንደማደርግ ዐውቃለሁ።'
5ከዚያም አስተዳዳሪው የጌታውን ተበዳሪዎች አንድ በአንድ ጠርቶ፣ የመጀመሪያውን ሰው 'ያለብህ ዕዳ ምን ያህል ነው?' ብሎ ጠየቀው።
6እርሱም፣ 'አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ' አለ። አስተዳዳሪውም፣ 'በፈረምኸው ውል ላይ ዐምሳ ማድጋ ብለህ ጻፍ' አለው።
7ሌላውንም፣ 'አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?' ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ 'መቶ ኩንታል ስንዴ አለብኝ' አለ፤ በፈረምኸው ውል ላይ ሰማንያ ኩንታል ብለህ ጻፍ' አለው።
8ጌታውም እምነት ያጎደው አስተዳዳሪ ያደረገውን ሰምቶ፤ በብልኅነቱ በመደነቅ እንዲህ አለ፤ 'በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች እግዚአብሔርን ከሚያውቁ ሰዎች ይልቅ በዓለማዊ ሥራቸው ብልኆች ናቸው።
9ስለዚህ እላችኋለሁ፣ በዓለም ባላችሁ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆችን አፍሩበት፤ ምክንያቱም ሀብታችሁ ባለቀ ጊዜ በዘላለም ቤቶች ይቀበሉአችኋል።
10በጥቂቱ የታመነ ሰው በብዙ ላይ የታመነ ይሆናል፤ በጥቂቱ የሚያምፅ በብዙም ዐመፀኛ ይሆናል።
11ስለዚህ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ እውነተኛውን ሀብትማ ማን አምኖ ይሰጣችኋል?
12እንደዚሁም በሌላ ሰው ሀብት ካልታመናችሁ የራሳችሁን ማን ይሰጣችኋል?
13ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ይተዋል፤ ሌላውን ይወዳል፤ አለበለዚያም ለአንዱ ራሱን የሰጠ ይሆናል፤ሌላውን ደግሞ ይንቃል። ስለሆነም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።
14ገንዘብን የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው፣ በኢየሱስ ላይ አፌዙበት።
15እርሱም እንዲህ አላቸው፤ "እናንተ በሰው ፊት ራሳችሁን እንደ ጻድቃን ትቈጥራላችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል። በሰዎች ፊት የከበረ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።"
16ሕግና ነቢያት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ሲሠራባቸው ኖረዋል። ከዚያ በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል ተሰብኳል። ሰው ሁሉ ወደዚህ ለመግባት ይጋፋል።
17ነገር ግን ከሕግ አንድ ነጥብ ዋጋ ከሚያጣ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል።
18ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ከባሏ የተፋታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል።
19ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ "ሐምራዊና ቀጭን የሐር ልብስ የለበሰ በየቀኑም በምቾትና በደስታ የሚኖር ሀብታም ሰው ነበረ።
20ሰውነቱ በቊስል የተወረረ አልዓዛር የሚባል ለማኝም በሀብታሙ ሰው ደጅ ይተኛ ነበር።
21አልዓዛርም ከሀብታሙ ማዕድ የተረፈውን ፍርፋሪ ሊመገብ ይመኝ ነበር። ውሾች እንኳ እየመጡ ቊስሉን ይልሱ ነበር።
22ከጊዜ በኋላ ለማኙ ሞተ፤መላእክትም መጥተው ወደ አብርሃም አጠገብ ወሰዱት። ሀብታሙም ሞተ፤ ተቀበረም።
23ሀብታሙ በሲኦል እየተሠቃየ ሳለ፣ ቀና ብሎ አብርሃም አልዓዛርን በዕቅፉ ይዞት አየ።
24እርሱም፣ 'አብርሃም አባት ሆይ፣ ራራልኝ በዚህ ነበልባል እየተሠቃየሁ ስለ ሆነ፣ አልዓዛር የጣቱን ጫፍ በውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ እባክህ አልዓዛርን' ላክልኝ ብሎ ጮኸ።
25አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ "ልጄ ሆይ፣ አንተ በምድር የሕይወት ዘመንህ መልካም ነገሮችን እንደተቀበልህና በደስታ እንደ ኖርህ፤ አልዓዛርም ክፉ ነገሮችን ሲቀበል እንደ ኖረ አስታውስ። አሁን ግን አልዓዛር እዚህ በምቾት ሲኖር፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ።
26ከሁሉ በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ለማለፍ የሚፈልጉ እንዳይሻገሩ እዚያ ያሉትም ወደ እኛ እንዳይመጡ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል አለ።'
27ሀብታሙ ሰው እንዲህ አለ፤ 'አባት ሆይ፣ እንግዲያውስ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤተ ሰብ እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤
28ምክንያቱም አምስት ወንድሞች አሉኝና እነርሱ ወደዚህ ሥቃይ ቦታ እንዳይመጡ ያስጠንቅቃቸው።'
29አብርሃም ግን፣ 'ወንድሞችህ ሙሴና ነቢያት አሏቸው፤ እነርሱንም ይስሙአቸው' ብሎ መለሰለት። ነገር ግን
30ሀብታሙ ሰው፣ 'አብርሃም አባት ሆይ፣ እንደዚህ አይደለም፤ አንድ ሰው ከሙታን ተነሥቶ ሄዶ ቢነግራቸው ንስሓ ይገባሉ' አለ።
31አብርሃም ግን ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ፣ አንድ ሰው ከሙታን ተነሥቶ ቢነግራቸው እንኳ አያምኑም' አለው።